ለራስ መታመን

ለራስ መታመን ራስን ጥርት አድርጎ መመልከት ማለት ነው፡፡ ምናልባት ለራሳችን በተናገርናቸው ታሪኮች ምክንያት ራሳችንን ባልተገባ መንገድ አስበነው ወይም ቦታ ሰጥተነው ሊሆን ይችላል፡፡ ማንነታችን ግን ለራሳችን ‹ይህ ነህ› ብለን የምንነግረው ሳይሆን በትክክል የሆነው ብቻ ነው፡፡ ቤተሰቦቻችን፣ መምህራኖቻችን፣ የዕድሜ እኩያ ጓደኞቻችን፣ የፍቅር ወይም የትዳር ጓደኞቻችን ስለራሳችን የሚነግሩን ነገሮችና እኛም ራሳችንን የምናስብበት መንገድ ‹እኔ እንዲህ ነኝ› የሚል ስዕል ይሰጠን ይሆናል፡፡ ዕውነታው ግን ይህ የማንነት ስዕል ሙሉ በሙሉ ልክ ላይሆን መቻሉ ነው፡፡ ምክንያቱም ለራስ በማድላት ምክንያት አምነን የማንቀበላቸው ብዙ እኩይ ጠባዮች ሊኖሩን ይችላሉና፡፡ ለምሳሌ ቀናተኛ ልንሆን እንችላለን፡፡ ቀናተኝነታችንን አምኖ መቀበል ግን እንደመሆን ግልጽ ሆኖ የሚታይና በቀላሉ አምነው የሚቀበሉት አይደለም፡፡

ስለዚህ ለራስ መታመን እንደ ጥንካሬ ሁሉ ደካማነትንም አምኖ መቀበልን ያካትታል፡፡ የዕለት ተዕለት ልምምድንም ይጠይቃል፡፡ ሌሎች ሰዎችን መዋሸት ተገቢ ባይሆንም ሊደግፉት የሚችሉ በርካታ ምክንያቶች ግን አሉት፡፡ ሰዎች ሥራቸውን ለመጠበቅ፣ ተጨማሪ ክርክሮችን ለማስወገድ፣ ስምና ክብራቸውን ጠብቀው ለመቆየት ወይም ሁሉም ሰው ስለ እነርሱ በጎ አስተሳሰብ እንዲኖረው በመሻት ይዋሻሉ፡፡ ራስን መዋሸት ግን ሌሎችን እንደመዋሸት አይቀልም፡፡ ምክንያቱም የነገሩን ትክክለኝነት በመናገር የሚሞግተን ሌላ የህሊና ክፍል አለና፡፡

‹ለመሆኑ ራሳችንን ለመዋሸት የምንሻው ለምን ይሆን?› የሚል ጥያቄ ያነሳችው የጤናማ አኗኗር ርዕሰ ጉዳዮች ጸሐፊዋ ሜሊሳ ቹ ሦስት ምክንያቶች አንስታለች፡፡

  1. ትክክል ለመሆን በመፈለግ

ትክክል ሆኖ መገኘት የሁሉም ሰው ፍላጎት ነው፡፡ ይሁን እንጂ መፈለግና ሆኖ መገኘት ይለያያሉ፡፡ በአስቸጋሪ ሁኔታዎች ውስጥ ሆነን ሁኔታውን አምኖ መቀበል ሲከብደን ‹እኔ ብቻ ኮ አይደለሁም፡፡ ሁሉም ሰው በዚህ ሁኔታ ውስጥ ያልፋል› ብለን ለራሳችን እንነግራለን፡፡ ይህ ውሸት ከእውነተኛው አስተሳሰብ ጋር ስለሚቃረን ለህሊናችን ምቾት አይሰጥም፡፡

  1. ለውጥን ላለመቀበል

አንድ ሰው በሁከት በተሞላ ግንኙነት ውስጥ ከሆነ አማራጩ ግልጽ ነው፤ መለያየት፡፡ ነገር ግን ነገሮች ይስተካከሉ በሚል ዕምነት ራሱን ለመደለል ይሞክራል፡፡ በሌላ በኩልም በሥራ ላይ የሚፈጠሩ ችግሮች ሲያሰቃዩት አዲስ ሥራ ወይም ሌላ ለውጥ ከመሻት ይልቅ ‹ነገሮች ይለወጡ ይሆናል› በሚል ተስፋ ህሊናውን እየዋሸ ይዘልቃል፡፡ ይህም ለራስ ያለመታመን ወይም ዕውነታውን ያለመቀበል ሌላው ገጽታ ነው፡፡

  1. ላለመጎዳት

ይህ የብዙዎች ጸባይ ነው፡፡ ራሳችንን ላለመጉዳት በማሰብ የተጣመሙትን እንዳልተጣመሙ፤ የተበላሹትን እንዳልተበላሹ አድርገን ለመመልከት እንጥራለን፡፡ ለምሳሌ ምግባረ ብልሹ አለቃ እንዳለን እያወቅን ከእርሱ ጋር ላለመጣላት በማሰብ ችግሩን ሳንነግረው መቆየት እንመርጣለን፡፡

ታዲያ ከእነኚህ መደለያዎች መውጣትና ለራሳችን መታመን የምንችለው መቼ ይሆን?

ራስን ማድመጥ

ሁሉም ሰው የተለያዩ ጸባዮች ያሉት እንደመሆኑ እኛም የራሳችን ጸባይ ያለን የተለየን ሰዎች ነን፡፡ ለምሳሌ ከስዕል ይልቅ ዋና መዋኘት፣ ከጉዞ ይልቅ አንድ ቦታ መቀመጥ፣ ከጩኸት ይልቅ ዝምታ፣ ከሰዎች ጋር ከመቀላቀል ይልቅ ብቸኝነት መውደዳችን ከሌሎች መለየታችንን ብቻ ሳይሆን ዕውነተኛውን የራሳችንን ማንነት የሚያሳይ ነው፡፡ ስለዚህ ራስን ማድመጥ የራስን ማንነት ጠንቅቆ በመረዳት ራስን ላለመዋሸት ይረዳል፡፡

ከዚህ በተጨማሪ ለሰዎችም ይሁን ለራስ መታመን ጥንካሬ ይሰጣል፡፡ ነፃም ያወጣል፡፡ በመታመን የሚያምን ሰው የራሱም ሆነ የሌሎች ባለዕዳ አይሆንም፡፡ የሚሠራት እያንዳንዷ ነገር ትክክለኛ መሆኗን ስለሚገነዘብ በራስ መተማመኑም ከፍተኛ ነው፡፡ ይህ ደግሞ ወደ ስኬት የመምራት አቅሙ እጅግ ከፍተኛ ነው፡፡

ምንጭ፡- meaningfullife እና medium.com

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትስስር ይፍጠሩ

325,851FansLike
49,039FollowersFollow
13,194SubscribersSubscribe