የሱዳን ፍርድ ቤት በሄሜቲና ሌሎች 13 ሰዎች ላይ በሌሉበት የሞት ፍርድ አስተላልፏል።
የሱዳን ፍርድ ቤት በአገሪቱ የእርስ በርስ ጦርነት ወቅት የሕክምና አቅርቦት ተቋማትን በመዝረፍና በማውደም ወንጀል የፈጥኖ ደራሽ ኃይሎች (RSF) አዛዥ መሐመድ ሐምዳን ዳጋሎን (ሄሜቲ) እና ሌሎች 13 ተከሳሾች በሞት እንዲቀጡ በሌሉበት ውሳኔ መስጠቱ ተዘገበ።
በፖርት ሱዳን የሚገኘው የጸረ-ሽብርና የመንግሥት ደኅንነት ወንጀሎች ፍርድ ቤት በሄሜቲ፣ በወንድሞቻቸው አብደል ራሂምና አል-ቁኒ ዳጋሎ እንዲሁም በሌሎች 11 ተከሳሾች ላይ የሞት ቅጣት መወሰኑን አናዶሉ ዘግቧል።
ተከሳሾቹ የሱዳን ብሔራዊ የሕክምና አቅርቦት ፈንድ ንብረት የሆኑ ሕንፃዎችን፣ መጋዘኖችንና ሌሎች ተቋማትን በመዝረፍና በማውደም ተከሰው ጥፋተኛ ተብለዋል።
ፍርድ ቤቱ በተጨማሪም ተከሳሾቹ በደረሰው ጉዳትና ኪሳራ ምክንያት ከ396 ሚሊዮን ዶላር በላይ ካሳ ለፈንዱ እንዲከፍሉ ማዘዙን ዘገባው አመልክቷል። የተከሳሾቹ ንብረቶች እንዲወረሱና እያንዳንዳቸውም 100 ሚሊዮን የሱዳን ፓውንድ (166 ሺህ ዶላር ገደማ) እንዲቀጡ ወስኗል።
ፍርድ ቤቱ በካርቱም፣ ሴናር፣ ኮርዶፋንና ዳርፉርን ጨምሮ በተለያዩ የሱዳን ክፍሎች በሚገኙ የሕክምና አቅርቦት ተቋማት ላይ የደረሰውን ጉዳት የሚመለከቱ ክሶችን መርምሯል። በተጨማሪም የተከሳሾቹ ፓስፖርትና ዜግነት እንዲሰረዝ ምክረ ሐሳብ አቅርቧል። 14ቱም ተከሳሾች በሌሉበት ነው የተዳኙት።
ሱዳን እጅግ በከፋ የእርስ በርስ ጦርነት ውስጥ የምትገኝ ሲሆን፤በጦርነቱ በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ሲገደሉ፣ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ተፈናቅለዋል።
የተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ መብቶች ጽሕፈት ቤት ማክሰኞ እንዳስታወቀው፣ ከጥር እስከ ጥቅምት 2026 በሱዳን ከ2,230 በላይ ሲቪሎች ተገድለዋል። ከእነዚህ ውስጥ ከ1,630 በላይ የሚሆኑት በድሮን ጥቃቶች የተገደሉ ናቸው።//
ጀነራል ሀምዳን ዳጋሎና ወንድሞቻቸው በሞት እንዲቀጡ ፍርድ ቤት ወሰነ

