ትዳርና ትምህርት

ትዳርና ትምህርት

ከትዳር አጋርዎ ጋር በትምህርት ደረጃ የሚኖራችሁ መለያየት ፍቅራችሁን የማቆም ዕድል ባይኖረውም የተወሰኑ አለመጣጣሞች ሊፈጥር ግን ይችላል፡፡ በመካከላችሁ ከፍተኛ የትምህርት ደረጃ ልዩነት ካለ አስቀድማችሁ በግልጽ መነጋገር ተገቢ ነው፡፡ በጋራ ጉዳዮች ላይ መግባባት የምትችሉትም ለልዩነቶቻችሁ ክብር ሰጥታችሁ ከተማመናችሁ በኋላ ነው፡፡

የመጀመርያው መፍትሔ በገንዘብ – ነክ ጉዳዮች ግልጽ ውይይት ማድረግ ነው፡፡ የእርስዎና የአጋርዎ ገቢ እንደ ትምህርት ደረጃችሁ ከፍተኛ ልዩነት ሊኖረው ስለሚችል ከፍተኛ ወጪ የሚያወጣው አካል አምኖበት ሊያደርገው ይገባል፡፡ ቁጥሮች ፍቅራችሁን እንዳይቆጣጠሩት አስቀድማችሁ ተቆጣጠሯቸው፡፡ እያንዳንዱን ወጪ ከውለታ ሳይሆን ከኃላፊነት ጋር ብቻ ማገናዘብ ትዳራችሁ ጤናማ ሆኖ እንዲቀጥል የሚኖረው አስተዋጽኦ እጅግ ከፍተኛ ነው፡፡

አንዳችሁ በሌላኛችሁ ላይ ከማማከር ያለፈ ጫና አይኑራችሁ፡፡ ለምሳሌ ባለቤትዎ ከእርስዎ ያነሰ የትምህርት ደረጃ ቢኖራቸውና ለመቀጠል ቢፈልጉ በገንዘብም ሆነ በዕውቀት ከመደገፍ ወደኋላ አይበሉ፡፡ በሌላ በኩል ግን ‹ከዚህ በኋላ መማር ሳይሆን ተጨማሪ ሥራዎች መሥራት ነው የምፈልገው› የሚል ሃሳብ ቢያመጡ ‹ለምን አትማርም/ሪም?› ብሎ ጸብ መግጠም አስፈላጊ አይደለም፡፡ እርስዎ ባለቤትዎን ያፈቀሩት በስብዕናቸውና ፍቅርን ሰጥቶ – በመቀበል አቅማቸው እንጂ በማስተርስ ወይም በዶክትሬታቸው አለመሆኑን ልብ ይበሉ፡፡

የትምህርት ልዩነት ካለ የአስተሳሰብ ልዩነት ሊፈጠር መቻሉ አጠያያቂ አይደለም፡፡ ስለዚህ የባለቤትዎን የአስተሳሰብ ውስንነት ለማስተናገድ ቻይ ይሁኑ፡፡ እርሳቸው በሚረዱት ቋንቋ ብቻ ያውሯቸው፡፡ ቅንጣት እንኳ የመበለጥ ስሜት እንዳይሰማቸው ያድርጉ፡፡ ‹በትምህርት ከፍተኛ ደረጃ ላይ በመድረሴ ባለቤቴን መምራት ያለብኝ እኔ ብቻ ነኝ› ከሚል መታበይ መውጣት እንዳለብዎም አይዘንጉ፡፡

በተቃራኒው በትምህርት ዝቅ ያሉት እርስዎ ከሆኑ ደግሞ በመበለጥ ስሜት ቅናት እንዳይሰማዎ ከፍተኛ ጥንቃቄ ያድርጉ፡፡ በትምህርት አለመግፋት ያለመቻል ሳይሆን የምርጫና የአጋጣሚ ጉዳይ መሆኑን ብቻ ይመኑ፡፡ ስለዚህ ከባለቤትዎ ጋር የሚኖርዎ ግንኙነት እኩል ለሸክም በተዘጋጁ ትከሻዎች ላይ የሚያርፍ ነው፡፡ እርስዎም ባለቤትዎም ‹አንድ› ተብሎ ለሚጠራው ማንነታችሁ ግማሽ አካሎች ናችሁና ሁለታችሁም እኩል የሆነ ዋጋ አላችሁ፡፡

 

ምንጭ፡- ከwikihow ድረገጽ በከፊል የተወሰደ፡፡

 

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትስስር ይፍጠሩ

325,851FansLike
49,039FollowersFollow
13,194SubscribersSubscribe