ከሆዜ ሞሪንሆ ካቴና የተላቀቀው ፖል ፖግባ

የጎል ድረ ገጹ ጸሃፊ ኒክ ሆውሰን ‹‹አሁን ፖግባ ነጻ ወጥቷል›› ይላል፡፡ የተጫዋቹ የቡድን አጋር ጀሲ ሊንጋርድ ደግሞ ‹እኔ የማውቀው ፖግባ ይህ ነው›› ሲል ተናግሯል፡፡ እውነት ነው፡፡ ፈረንሳያዊው አማካይ ፖል ላቢሌ ፖግባ ተቀይሯል፡፡ አሰልጣኝ ሆዜ ሞሪንሆ ተሰናብተው ኦሌ ጉናር ሶሻየር ማንቼስተር ዩናይትድን ከተረከቡት በኋላ ፖግባ እንደአዲስ ተወልዷል፡፡ አስደናቂ አቋምን እያሳየ ግቦችንም እያስቆጠረ ይገኛል፡፡

ጀሲ ሊንጋርድ ሀሳቡን ይቀጥላል፡- ‹‹የቀድሞውን ፖል ፖግባ በደንብ እያየነው ነው፤ እግር ኳስን እንደሚፈልገው መጫወት ጀምሯል፤ የሚወደው ቦታ ላይ ነው፡፡ ነጻነትን አግኝቷል፤ ወደፊት ተጭኖ መጫወት ተፈቅዶለታል፤ ግቦችንም እያስቆጠረ ነው፤ ኦሌ በብዙ ነገሮች እንዲሻሻል ያግዘዋል ብዬ አምናለሁ››

‹‹በቀድሞው አሰልጣኝ ጊዜም ቢሆን የተለያዩ ጨዋታዎችን እናሸንፍ ነበር፤ አሁን ያለው ልዩነት አጥቅተን የመጫወት እድልን ማግኘታችን ነው፤ ብዙ የግብ እድሎችን መፍጠር ችለናል፤ የበለጠ ተነቃቅተን ለመጫወት ረድቶናል›› በማለት ፖግባም ስለወቅቱ ሁኔታ አስተያየቱን ሰጥቷል፡፡ ተጫዋቾቹ ቃል በቃል ባይናገሩትም የሞሪንሆ ክለቡን መልቀቅ ነጻነትን እንደሰጣቸው በተዘዋዋሪ መንገድም ቢሆን እየገለጹ ነው፡፡ ከሞሪንሆ ካቴና ከተፈቱ ተጫዋቾች መካከል ደግሞ ዋናው ፖል ፖግባ ነው፡፡ የቀድሞው የማንቼስተር ዩናይትድ ተጫዋች ጋሪ ኔቭልም በዚህ ይስማማል፡፡

ደርሶ መልስ

ፈረንሳያዊው አማካይ ፖል ላቢሌ ፖግባ ወደቀድሞ ክለቡ ዳግም የተመለሰው ከሁለት ዓመታት በፊት ነበር፡፡ በነጻ ዝውውር ከስድስት ዓመታት በፊት ማንቼስተር ዩናይትድን ለቆ የጣልያኑን ጁቬንቱስ ተቀላቅሎ የነበረው ፖግባ በጊዜው የዓለማችን ውድ ተጫዋች ባደረገው ዋጋ ነበር ወደኦልድትራፎርድ የተመለሰው፡፡

በጊዜው አንዳንድ የመገናኛ ብዙሃን አባላትና የሌሎች ክለብ አሰልጣኞች ለፖግባ የወጣው 89.3 ሚሊዮን ፓውንድ የዝውውር ዋጋ በጣም ከፍተኛ ነው በሚል ትችት መሰንዘራቸው ይታወሳል፡፡ እግር ኳሱ ወደአስቀያሚ መንገድ እየተጓዘ ነው ብለው ነበር፡፡ የጎል ድረገጽ ዘጋቢ የሆነው ማርክ ዶይል በተለይ ‹‹Poverty, Unemployment, Terror – 105m Euro Pogba Transfer Is An Insult To Humanity›› በሚል ርዕስ በጻፈው ሃተታ ማንቼስተር ዩናይትድ ሰብዓዊነት የጎደለው ተግባር መፈጸሙን ገልጾ ነበር፡፡ ድህነት፣ ስራአጥነትና ሽብርተኝነት ዓለምን እያመሰ ባለበት በዚህ ወቅት ለአንድ ‹‹ቅሪላ አልፊ›› ይሄን ያህል ከፍተኛ ገንዘብ ማውጣት ተገቢ አለመሆኑን በመጥቀስ ድርጊቱን በእጅጉ ኮንኗል፡፡ የሚገርመው ነገር ዶይል ይህንን በጻፈ በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ፓሪስ ሴን ዠርማ ለኔይማር 200 ፓውንድ የዝውውር ዋጋ አውጥቶ አለምን ጉድ አሰኝቷል፡፡

ከልጅነት እስከ እውቀት

የተወለደው እ.ኤ.አ መጋቢት 15 ቀን 1993 በፈረንሳይዋ ሴንት ኢተ ማርኔ ነው፡፡ ከጊኒያዊያን ቤተሰቦች የተወለደው ፖል ፖግባ ታላላቅ ወንድሞቹም ልክ እንደሱ እግር ኳስ ተጫዋቾች ናቸው፡፡ በእርግጥ ሁለቱ የፖል ፖግባ ታላቅ ወንድሞች በደቂቃ ልዩነት በተፈጠረ እድሜ ታላቅና ታናሽ ተባሉ እንጅ መንትዮቹ ናቸው፡፡ ሁለቱም በብሔራዊ ቡድን ደረጃ ለተወለዱባትና ለቤተሰቦቻቸው ሃገር አፍሪካዊቷ ጊኒ ይጫወታሉ፡፡ የ3 ዓመት ታናሻቸው ፖል ፓግባ ግን የፈረንሳይ ብሔራዊ ቡድን ተጫዋች ነው፡፡ በ2014 በተደረገው የብራዚሉ ዓለም ዋንጫ ፈረንሳይን በመወከል ተጫውቶ አስገራሚ እንቅስቃሴ ማድረጉ ይታወሳል፡፡ በ2018 ደግሞ ሩሲያ አለም ዋንጫ ላይ ሀገሩን ሻምፒዮን አድርጓል፡፡

የ25 ዓመቱ አማካይ ፖል ፖግባ በስፖርት ተንታኞች ዘንድ ከሁለት የቀድሞ የሀገሩ ተጫዋቾች ጋር ይነጻጸራል፡፡ ረዥም ቁመቱና በመሃል ሜዳ የሚያሳየውን የኳስ ቁጥጥር ተመልክተው ‹‹አዲሱ ፓትሪክ ቬራ›› እያሉ የሚጠሩት ሲኖሩ በሚፈጥራቸው የግብ እድሎችና ከመሃል ተነስቶ ወደፊት በመግፋት በተቃራኒ ተከላካዮች ላይ በሚፈጥረው ተጽዕኖ እንዲሁም በሚያስቆጥራቸው ግቦች መነሻነት ‹‹ጥቁሩ ዚዳን›› የሚሉትም አሉ፡፡

የፈርጉሠን ስህተት?

ሰር አሌክስ ፈርጉሠን በማንቼስተር ዩናይትድ ክለብ በቆዩባቸው ከሁለት አስርት ዓመታት በላይ ጊዜ ውስጥ የማይደፈሩ ታላላቅ ስኬቶችን አስመዝግበዋል፡፡ ክርስቲያኖ ሮናልዶን ጨምሮ ምርጥ ምርጥ የእግር ኳስ ኮከቦችን የቀያይ ሰይጣኖቹን ማልያ ለብሰው እንዲጫወቱ አድርገዋል፡፡ ይሁን እንጅ ፖል ፖግባን በተመለከተ ስህተት ሰርተዋል ብለው የሚኮንኗቸው አሉ፡፡ ፖግባ ያደገበትን የፈረንሳዩን ሊ ሃቭሬ የተባለ ክለብ ለቆ ማንቼስተርን ሲቀላቀል ገና የ15 ዓመት ልጅ ነበር፡፡ በጊዜው የፈረንሳዩ ክለብ ለፊፋ ክስ አቅርቦ ነበር፡፡ ‹‹ማንቼስተር ዩናይትድና የተጫዋቹ ቤተሰቦች በመመሳጠር የኔን ጥቅም አሳጥተው የኔ ንብረት የሆነውን ተጫዋች አሳጥተውኛል›› ብሎ ተከራክሮ ነበር፡፡ ፊፋ ጉዳዩን ተመልክቶ ውድቅ ያደረገው ግን ወዲያው ነው፡፡ ተጫዋቹ ከቀድሞ ክለቡ ጋር የተዋዋለው ምንም አይነት ስምምነት አልነበረም፡፡ ከፖግባ ወደማንቼስተር ዩናይትድ መግባት ጋር ተያይዞ የሊ ሃቭሬ ክለብ ፕሬዚዳንት ከማንቼስተር ዩናይትድ በኩል የመኖርያ ቤትና የ87 ሺህ ዶላር ስጦታ በድብቅ አግኝተዋል በሚልም ይታማሉ፡፡

ፖል ፖግባ በዚህ ሁሉ ውዝግብ ውስጥ ቀያይ ሰይጣኖቹን ቢቀላቀልም እድሜው አድጎ ክለቡን ማገልገል በሚችልበት ወቅት አሰልጣኝ ሰር አሌክስ ፈርጉሠን ከእሳቸው የማይጠበቅ ስህተት ሰሩ፡፡ ፖል ፖግባ በነጻ ዝውውር የጣልያኑን ጁቬንቱስ ሲቀላቀል ሀጢያቱን ለተጫዋቹ አሽከመው ዘወር አሉ፡፡ ‹‹ክለቡን መልቀቅ እንደሚፈልግ ቀድመን አውቀናል፡፡ የሚያበሳጭ ነገር ነው፡፡ እውነት ለመናገር ምንም አይነት ክብር አላሳየንም፡፡ ለማንኛውም እንኳን ተገላገልን›› በማለት ተናገሩ፡፡ ሌላ ጊዜ ደግሞ የፖል ፖግባን ወኪል ሚኖ ራዮላን ተጠያቂ አደረጉ፡፡ ‹‹በዓለም ላይ ከሁለት ሰዎች ጋር ፈጽሞ መግባባት አልችልም፤ አንዱ ሚኖ ራዮላ ነው፤ ፖል ፖግባን ያስኮበለለው እሱ ነው›› ብለው ነበር፡፡

የስፖርት ተንታኞች ግን ሀጢያቱን ወደ አሰልጣኙ ይገፉታል፡፡ ያንን ድንቅ ወጣት ተጫዋች ከፈረንሳይ ካመጡት በኋላ ረስተውት ነበር ብለው ይተቿቸዋል፡፡ ያ ባይሆን ኖሮ ልጁን ከአንድ አመት በፊት ቀደም ብሎ የረዥም ዓመታት ኮንትራት በማስፈረም ዋስትና ሊሰጡት ይገባ ነበር ይላሉ፡፡ አሰልጣኙን በጥርጣሬ ሲመለከት የነበረው ፖል ፖግባ ሳይጠበቅ በ2012 ክረምት ላይ የጁቬንቱስ ተጫዋች ሆኖ የ4 ዓመታት ኮንትራት ሊፈራረም ችሏል፡፡ ወጣቱ አማካይ በማንቼስተር ዩናይትድ ማልያ ለዋናው ቡድን ተሰልፎ የተጫወተው 3 ጨዋታዎች ላይ ብቻ ነበር፡፡ በነዚህ ጨዋታዎች የተሰለፈውም ቢሆን ተቀይሮ እየገባ ነው፡፡

ስኬታማ አመታት

ፖል ፖግባ በጣልያን የእግር ኳስ ዘመኑን የጀመረው በተሳካ ሁኔታ ነው፡፡ የተመልካቾችን ትኩረት ለማግኘት ጊዜ አልወሰደበትም፡፡ ጣልያናውያን በቅጽል ስም ነው የተቀበሉት፡፡ ‹‹Polpo paul›› ይሉታል፡፡ ፖል ኦክቶፐስ ለማለት ነው፡፡ ለዚህ ስያሜ ያበቁት ደግሞ ረዣዥም እግሮቹ ናቸው፡፡

ፖግባ ለጁቬንቱስ የመጀመሪያ ጨዋታውን ያደረገው ክለቡ በቅድመ ዝግጅት ጨዋታ የፖርቹሉን ቤኔፊካ በገጠመበት ወቅት ነው፡፡ 78ኛው ደቂቃ ላይ የአሮጊቷን አንጋፋ ተጫዋች አንድሪያ ፒርሎን በመቀየር ለመጀመሪያ ጊዜ ነጭና ጥቁሩን ማልያ ለብሶ ተጫወተ፡፡ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ የዓለም እግር ኳስ አፍቃሪያን አይን እንዳረፈበት ይገኛል፡፡

ጁቬንቱስ ናፖሊን 2ለ0 ባሸነፈበት ጨዋታ የመጀመሪያ ጎሉን ጥቅምት 20 ቀን 2012 እ.ኤ.አ ያስቆጠረው ፖግባ ከ10 ቀናት በኋላ አሮጊቷ ከቦሎኛ ጋር ባደረገችው ጨዋታ ድንቅ ብቃቱን አሳየ፡፡ በወቅቱ ጨዋታውን 2ለ1 ሲያሸንፉ የመጀመሪያዋን ጎል ከማስቆጠሩ በተጨማሪ ፋብዮ ኳግሊያሬላ ላስቆጠራት ወሳኝ ጎልም ምክንያት ሆነ፡፡ የጣልያን ጋዜጦች በቀጣዩ ቀን ማለዳ በፖል ፖግባ ምስል ደምቀው የአድናቆት ቃላትን ሞልተው ታዩ፡፡

ላ ሪፐብሊካ፣ ኤል ሚሴገሮ እና ጋዜጣ ዴሉ ስፖርት የተባሉት የሃገሪቱ ተነባቢ ጋዜጦች ‹‹የወደፊቱ የሴሪአው ኮከብ መጣ›› ብለው ዘገቡ፡፡ ፖግባ ከጁቬንቱስ ጋር ስኬታማ ጊዜን አሳልፏል፡፡ በተደጋጋሚ ክለቡን ከሽንፈት ከመታደጉም ባለፈ ሙሉ ሶስት ነጥብ ይዞ እንዲወጣ አስችሏል፡፡ በየጨዋታው ኮከብ /Man Of The Match/ ተብሎ ይወጣል፡፡ በ2013 የአውሮፓ ምርጥ ወጣት ተጫዋቾች ክብርን ያገኘ ሲሆን በ2014 ደግሞ ለባሎንዶር ከታጩት 23 ተጫዋቾች መካከል አንዱ መሆን ችሏል፡፡ ከእጩዎቹ ውስጥ በእድሜ ትንሹ እሱ ነበር፡፡

ፖግባ ምርጥ ተጫዋች ነው፡፡ በአንድ ወቅት የቀድሞው የጁቬንቱስ ተጫዋች አንድሪያ ፒርሎ ለዴይሊ ቴሌግራፍ በሰጠው ቃለምልልስ ስለተጫዋቹ የሰጠው አስተያየት ለዚህ ማሳያ ይሆናል፡፡ ‹‹ፖግባ ወደእኛ መጥቶ የመጀመሪያ ልምምዱን በሰራበት ወቅት ሁላችንም በማንቼስተር ላይ ስንስቅ ነበር፤ የሳቅነው ይሄንን የመሰለ ድንቅ ልጅ በነጻ በመልቀቃቸው ነው፤ ዛሬም ድረስ እንስቃለን፤ ለማመን ይከብዳል፤ አስታውሳለሁ የመጀመሪያ ልምምድ ሰርቶ ወደመልበሻ ክፍል ስንሄድ ጅያንሉጅ ቡፎን እየሳቀ ወደእኔ መጥቶ ‹የእውነት ግን በነጻ ነው የለቀቁት?› አለኝ›› ይላል ፒርሎ፡፡ ፖግባ በጁቬንቱስ ቆይታው አራት ጊዜ የሴሪኤውን ዋንጫ አንስቷል፡፡ በማንቼስተር ዩናይትድ ቤትም ብዙ ስኬቶችን ለማጣጣም ይመኛል፡፡

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትስስር ይፍጠሩ

325,851FansLike
49,039FollowersFollow
13,194SubscribersSubscribe