የአፍሪካ ዋንጫ የበላችበት ሳምንት

/ከእዝራ እጅጉ …/ ተወዳጅ ሚድያና ኮሚኒኬሽን

ውድ አንባቢያን፣ በያዝነው ሳምንት ባለፈው ሰኞ ጥር 13 2011፣ ኢትዮጵያ የአፍሪካ ዋንጫ የበላችበት ቀን ነበር፡፡  ተወዳጅ ሚድያና ኮሚኒኬሽን ይህ የቀድሞ ታሪክ ለአዲሱ ትውልድ ይጠቅማል ብሎ ስላመነበት ከምስል ጋር በማቀነባበር ይህን አጭር መጣጥፍ አቅርቦላችኋል፡፡

የዛሬ 57 አመት ጥር 13 1954 ኢትዮጵያ የ3ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ባለድል ነበረች፡፡ያኔ የግማሽ ፍጻሜ ግጥሚያው ተደርጎ የነበረው ጥር 6 1954 ሲሆን ሀገራችን በዚህ ጨዋታ ቱኒዝያን ድል በመንሳት ለፍጻሜ አልፋለች፡፡ በጊዜው ቱኒዝያ ላይ ግቡን ያስቆጠሩት ሉቺያኖ  ቫሳሎ፣ ግርማ ዘለቀና መንግስቱ ወርቁ ነበሩ፡፡ ጥር 10 ቀን 1954 ኡጋንዳና ግብጽ ተጫውተው  ግብጽ 2ለ1 አሸኝፋ ከሀገራችን ጋር ለፍጻሜ ቀርባለች፡፡ ሀገራችን በአሸናፊነት የተወጣችውን  ይህን ጨዋታ ዶክተር ሰለሞን በርሄ ሲያስታውስ ብዙ ትዝታ ወደ ህሊናው ያመጣል፡፡

3ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ቡድን ያረፈው እቴጌ ጣይቱ ሆቴል ነበር፡፡ ዶክተር ሰለሞን ትዝ እንደሚለው ዋንጫው ተበልቶ ከአዲስ አበባ ስቴዲየም እስከ ጣይቱ ሆቴል በጭፈራ ለመድረስ 2 ሰአት ወስዶ ነበር፡፡ ያኔ ገና የ6 አመት ህጻን  የነበረው ዶክተር ሰለሞን ከወላጅ አባቱ ጋር ኳሱ ለመመልከት ስቴዲየም መግባቱን ያስታውሳል፡፡ አባቱ አቶ በርሄም በወቅቱ  በነበረው ግርግር ተረጋግጠው ቁስሉ ቅርብ ጊዜ ድረስ ነበራቸው፡፡  አቶ በርሄ ይህን እግራቸውን ዛሬ ሲመለከቱ   ‹‹ይህ ለሀገሬ ብሄራዊ ቡድን የተከፈለ መስዋእትነት ነው›› ይላሉ፡፡

አለም አቀፍ ዳኛ ጌታቸው ገብረማሪያም፣ በአለም አቀፍ ዳኝነት ከ35 አመት በላይ ዘልቀዋል፡፡ያኔ 3ኛው የአፍሪካ  ዋንጫ ላይ ተሰልፈው ነበርና እነማን በጨዋታው ላይ እንደነበሩ ለዚህ ጽሁፍ አቅራቢ ነግረውት ነበር፡፡ አንድ ቁጥርን ለብሶ ይጫወት የነበረው  ጊላ ነበር፡፡ 2 አስመላሽ፣ ከኢትዮ ሲሚንቶ ነበር፡፡ 3 ቁጥር ክፍሎም ከኤርትራ ነው፡፡ 4 ደግሞ በርሄ ጎይቶም 5 አዋድ መሀመድ፣ 6 ተስፋዮ ወዲ ቀጭን፣  7 ግርማ ዘለቀ፣ 8 መንግስቱ ወርቁ፣ 9 ሉቺያኖ ቫሳሎ ፣10 ኢታሎ ቫሳሎ 11 ጌታቸው ወልዴ ነበር፡፡

በፍጻሜው እለት ግርማን የቀየረው ተክሌ እንደገባ አንድ አገባ፡፡ ግብጾች እንደምንም ብለው አንድ አገቡ፡፡  አሁን የኢትዮጵያ ደጋፊዎች ተደናገጡ፡፡  ግብጾች አሁንም አንድ ደገሙ፡፡ ከዛም ሉቺያኖ አንድ ግብ ሲያስቆጥር ሁለት እኩል ሆኑ፡፡ ከእረፍት መልስ ኢታሎ 3ኛውን ግብ አገባ፡፡ 4ኛውንም መንግስቱ ወርቁ  ሲያገባ በአዲስ አበባ ስቴድየም ታድሞ የነበረው ተመልካች ተረጋጋ፡፡  በዚህ መልኩ ነበረ ሀገራችን  የ3ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ባለድል ለመሆን የቻለችው፡፡

ዶክተር ሰለሞን ስለዛ ዘመን ጨዋታ ሲያስታውስ የመንግስቱን ክህሎት አይዘነጋውም፡፡ በዶክተር ሰለሞን አተያይ መንግስቱ ወርቁ የኳስ አርበኛ ነው፡፡ በነገራችሁ ላይ የአፍሪካ ፉትቦል ፌዴሬሽን የተመሰረተው በ1949 የካቲት ወር ላይ ነበር፡፡ መስራቾቹም ግብጽ ሱዳንና ኢትዮጵያ ነበሩ፡፡ በጊዜው ሀገራችንን በመወከል በስብሰባው ላይ ታድመው የነበሩት አቶ ይድነቃቸው ተሰማ እና ሌተናል ኮሎኔል ገበየው ዱቤ ነበሩ፡፡ በዛው አመት በሱዳን በተካሄደው የመጀመሪያው  የአፍሪካ ዋንጫ  ግብጽ ሱዳንና አትዮጵያ የውድድሩ ተካፋዬች ነበሩ፡፡ አቶ አበበ ገላጋይ  ስለአፍሪካ ዋንጫዎች የዛን ጊዜዎቹ ግጥሚያዎች አሰብ ሲያደርጉ አቅም ኖሯቸው ነገር ግን ለመሰለፍ እድል ያላገኙ ተጫዋቾች  እንደነበሩ ያነሳሉ፡፡ ለዚህም እንደምሳሌ የኮተን ተጫዋች የሆነውን ሙቅቢል አህመድን ይጠቅሳሉ፡፡

ኢትዮጵያ የአፍሪካ ዋንጫ የበላችበት ያ ዘመን ሲነሳ ውድድሩ  የተካሄደበት ስቴድየም አብሮ ይነሳል፡፡ በዛ ስቴድየም ውስጥ የሚገኙ ቆሎ ነጋዴዎች፣  ኮካ ኮላ የሚሸጡ ልጆች የሚዘነጉ አይደሉም፡፡ ከእነዚህ ቆሎ ነጋዴዎች አንዱ ፣አስፈው ሽንብር ይነሳል፡፡ አስፋው ሽንብር የስቴድየሙ ማድመቂያ ነበር፡፡

የፎቶግራፍ ባለሙያው በዛብህ አብተው ደግሞ በ3ኛው የአፍሪካ ዋንጫ  ላይ ሜዳ ላይ የሚጫወቱትን  እነ መንግስቱ ወርቁን  እነ ሉቺያኖ ቫሳሎን ለማንሳት ይሯሯጡ ነበር፡፡ ያኔ ጎልማሳ የነበሩት አቶ በዛብህ አብተው  በአሁኑ ሰአት የ88 አመት ሰው ናቸው፡፡  ያኔ ስመ- ጥሩ የነበረው ጋዜጠኛ  ሰለሞን ተሰማ  ፎቶ ፍለጋ አቶ አብተው ጋር ያቀና ነበር፡፡  አቶ በዛብህም ያነሱትን ምስል ቶሎ  ብለው ሰለሞን መጽሄት ላይ እንዲያወጣው ይሰጡት ነበር፡፡

አቶ በዛብህ አብተው ከ5 አመት በፊት ለዚህ ጽሁፍ አቅራቢ  እንደነገሩት የአፍሪካ ዋንጫ እለት ብዙ  ያነሱት ምስል የመንግስቱ ወርቁን ነበር፡፡  አቶ በዛብህ እንደነገሩኝ ትኩረት ሰጥተው የሚያነሱት ለሚያጠቃው ቡድን ነበር፡፡  በነገራችን ላይ ኢትዮጵያ የአፍሪካ ዋንጫን ከበላች   ከ1 አመት ከ4ወር በኋላ የአፍሪካ አንድነት ድርጅት በግንቦት 1955 ተመሰረተ፡፡

ማስታወሻ : የዚህ ጽሁፍ አቅራቢ እዝራ እጅጉ ሙላት  ለ19 አመት በጋዜጠኝነት ያገለገለ ሲሆን የ 13 ሰዎችን ግለ- ታሪክ በዲቪዲና በኦድዮ ሲቲ ያሳተመ ነው፡፡ በዚህ 3 ወር ውስጥ ተጨማሪ 5 ታሪኮችን በዲቪዲና በኦድዮ ሲዲ እንደሚያሳትም ይጠበቃል፡፡ እዝራ ተወዳጅ ሚድያና ኮሚኒኬሽን የተሰኘ የራሱን ድርጅት የመሰረተ ነው፡፡

Gmail .tewedajemedia@gmail.com

 

 

 

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትስስር ይፍጠሩ

325,851FansLike
49,039FollowersFollow
13,194SubscribersSubscribe