በኢትዮጵያ በየሰዓቱ 57፣ በየቀኑ ደግሞ 3 ሺህ 368 ጨቅላ ሕፃናት ሕይወታቸውን እንደሚያጡ ተገለጸ

በኢትዮጵያ በየሰዓቱ 57፣ በየቀኑ ደግሞ 3 ሺህ 368 ጨቅላ ሕፃናት ለሞት እንደሚዳረጉ የጤና ሚኒስቴር ይፋ አደረገ።

ሚኒስቴሩ ይህንን አሳሳቢ መረጃ ያወጣው «ለጨቅላ ሕፃናት ክትትልና እንክብካቤ የወደፊት ሕይወት እና አቅም በመሆኑ መዋዕለ ነዋይ ይመድቡ» በሚል መሪ ሃሳብ፣ ዓለም አቀፍ ቀናቸው ሳይደርስ የተወለዱ ጨቅላ ሕፃናት ቀንን ከአጋር አካላት ጋር በመሆን በአዲስ አበባ ባከበረበት ወቅት ነው።

ለዚህ ከፍተኛ የሕፃናት ሞት ዋነኛ ምክንያቱ ሕፃናቱ ከ37 ሳምንታት የእርግዝና ጊዜ በፊት ያለ ጊዜያቸው በመወለዳቸው እና ለቅዝቃዜና ለተለያዩ በሽታዎች በቀላሉ በመጋለጣቸው መሆኑ ተገልጿል።

ከወሊድ በፊት ለእናቶች የሚደረግ የሕክምና ክትትልና እንክብካቤ ማነስም ለችግሩ መባባስ አንዱ መነሻ መሆኑ ተመላክቷል።

በዓለም አቀፍ ደረጃ በየዓመቱ 13 ሚሊዮን ሕፃናት ቀናቸው ከመድረሱ በፊት በመወለዳቸው ምክንያት ሕይወታቸውን የሚያጡ ሲሆን፣ አብዛኛው ሞት የሚከሰተው በአፍሪካ እና በደቡባዊ እስያ ሀገራት መሆኑን የሚኒስቴሩ መረጃ ያሳያል።

ኢትዮጵያም ያለ ጊዜያቸው የሚወለዱ ሕፃናት ችግር በስፋት ከሚታይባቸው ግንባር ቀደም አምስት የዓለም ሀገራት ተርታ ተመድባለች።

ይህንን አሳሳቢ ሁኔታ ለመቅረፍ በዘላቂ የልማት ግብ እቅድ መሠረት እስከ 2030 ድረስ በትኩረትና በቅንጅት በመሥራት የጨቅላ ሕፃናትን ሞት ለመቀነስ ጥረት እየተደረገ መሆኑን የጤና ሚኒስቴር አስታውቋል።

ሕፃናቱን ከሞት አደጋ በመታደግ ነገ ሀገር ተረካቢ አምራች ኃይል እንዲሆኑ ለማስቻል ወላጆች፣ ማህበረሰቡና የጤና ተቋማት የበኩላቸውን ከፍተኛ ድርሻ እንዲወጡም ጥሪ ቀርቧል።

 እንደ ዩኒሴፍ (UNICEF) መረጃ ግን፣ በኢትዮጵያ በየዓመቱ ወደ 87,000 እስከ 90,000 የሚጠጉ ጨቅላ ሕፃናት (ዕድሜያቸው ከ28 ቀን በታች የሆኑ) ሕይወታቸውን ያጣሉ። ይህም በአማካይ፦

  • በቀን ወደ 240 እስከ 250 ጨቅላ ሕፃናት
  • በሰዓት ወደ 10 ጨቅላ ሕፃናት አካባቢ መሆኑን ያሳያል።
Sourcelomi news

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትስስር ይፍጠሩ

325,851FansLike
49,039FollowersFollow
13,194SubscribersSubscribe