ግልጽ የሆነ መመርያ እስኪወጣ ድረስ የክብር ዶክትሬት እንዳይሰጥ መከልከሉን ትምህርት ሚኒስትር አስታወቀ

በኢትዮጵያ እስካሁን 79 ሰዎች የክብር ዶክትሬት ዲግሪ የተሰጣቸው ሲሆን 68 በመቶ የሚሆነው ለክልል ሰዎች ነው ተባለ
ግልጽ የሆነ መመርያ እስኪወጣ ድረስ የክብር ዶክትሬት እንዳይሰጥ መከልከሉን ትምህርት ሚኒስትሩ አስታወቁ
‹‹የተበታተነ አሠራርን ለመቅረፍ ግልጽ የሆነ መመርያ እስኪወጣ ድረስ ዩኒቨርሲቲዎች የክብር ዶክትሬት የሚባል ነገር መስጠት እንዲያቆሙ እንደተነገራቸው›› የትምህርት ሚኒስትሩ ብርሃኑ ነጋ (ፕሮፌሰር) አስታወቁ፡፡
ሚኒስትሩ ይህንን የተናገሩት ‹‹የኢትዮጵያ ሳይንስ አካዴሚ የዶክትሬት ዲግሪና የክብር ዶክትሬት ዲግሪ ሽልማት በኢትዮጵያ›› የሚሉ ጉዳዮችን ምሁራንና ሌሎች ባለድርሻ አካላት በተገኙበት ሐሙስ መጋቢት 26 ቀን 2016 ዓ.ም. ውይይት በተካሄደበት ወቅት ነው፡፡
በኢትዮጵያ የክብር ዶክትሬት ሲሰጥ በተበታተነ ሁኔታ በመሆኑ ዩኒቨርሲቲዎች መስጠት እንዲያቆሙ ውሳኔ መተላለፉን ሚኒስትሩ አስረድተዋል፡፡
ትምህርት ሚኒስቴር የክብር ዶክትሬት ዲግሪ አሰጣጥን በተመለከተ መመርያ እያዘጋጀ መሆኑንና መመርያውንም በዚህ ዓመት አጠናቆ ለመጨረስ ሒደት ላይ እንደሆነ አክለው ገልጸዋል፡፡
ጉዳዩን በተመለከተ ‹‹ዩኒቨርሲቲዎች በሁለት እግራቸው ቆመው ቢሆንና እራሳቸውን መምራት ቢችሉ ኖሮ፣ ጉዳዩ ውስጥ መንግሥት ጣልቃ አይገባም ነበር፤›› ያሉት ሚኒስትሩ በኢትዮጵያም እስካሁን 79 ሰዎች የክብር ዶክትሬት ዲግሪ እንደተሰጣቸው አስረድተዋል፡፡
የክብር ዶክትሬት ዲግሪ ከተሰጣቸው 68 በመቶ የሚሆነው ለክልል ሰዎች እንደሆነ ገልጸው፣ ዩኒቨርሲቲዎች ትክክለኛ ትምህርት የሚቀሰምባቸው ቦታዎች መሆኑ ቀርቶ ለብልሹ አሠራር መከታተያ ቦታ ሆነዋል ብለዋል፡፡
እ.ኤ.አ. በ2000 በዓለም አቀፍ ደረጃ 91 ሚሊዮን የፒኤችዲ ተማሪዎች እንደነበሩና ከዚህ ውስጥ አሜሪካና ቻይና 17 በመቶ ድርሻ እንደያዙ የውይይቱን መነሻ ጽሑፍ ያቀረቡት ማስረሻ ፈጠነ (ፕሮፌሰር) ተናግረዋል፡፡
እ.ኤ.አ. በ2020 ደግሞ 104 ሚሊዮን የፒኤችዲ ተማሪዎች እንደነበሩ ማስረሻ (ፕሮፌሰር)፣ ከዚህ ውስጥ የአሜሪካ ድርሻ ቀንሶ ወደ 11 በመቶ ሲወርድ የቻይና ደግሞ 29 በመቶ ሊያድግ መቻሉን አስረድተዋል፡፡
በዓለም አቀፍ ደረጃ ከእነዚህ አገሮች ውጭ ሌሎች አገሮች እንደየመጠናቸው የፒኤችዲ ትምህርት የሰጡ ሲሆን፣ የዶክትሬት ዲግሪ በኢትዮጵያም ሲታይ በጣም ዝቅተኛ መሆኑን አብራርተዋል፡፡
የዶክትሬት ትምህርት ከአገሮች የሳይንስና ቴክኖሎጂ ዕድገት ጋር በጣም የተቆራኘ መሆኑን ገልጸው፣ የዶክትሬት ዲግሪ ትምህርት በኢትዮጵያ ሲታይ የከፍተኛ ትምህርት መምህርና እጥረት ለማሟላት የታለመ እንደሆነ አክለው ገልጸዋል፡፡
በተለይ ከአብዮቱ በኋላ በርካታ የውጭ አገር መምህራን ኢትዮጵያን ለቀው መውጣታቸውን ያስታወሱት ማስረሻ (ፕሮፌሰር) የዶክትሬት ትምህርት አሰጣጥ ፅንሱ የተጀመረው የከፍተኛ ትምህርት መምህራን እጥረት ለማሟላት እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡
በወቅቱ ኢትዮጵያ የውጭ አገር መምህርን ለመቅጠር አቅም እንደሌላት በሌላ በኩል ደግሞ በበቂ ሁኔታ መምህራኖችን ውጭ የማስማር አቅም አለመኖሩ ችግሩ ሊፈጠር ችሏል ብለዋል፡፡
በተለያየ ምክንያትም ውጭ ለመማር የሄዱ ምሁራኖች ለመማር የሄዱበት አገር እንደሚቀሩ ጠቅሰው፣ እ.ኤ.አ. በ2010 የተደረገ ጥናት እንደሚያሳየው ኢትዮጵያ በወቅቱ ከሦስት ሺሕ በላይ የፒኤችዲ ምሩቃን እንደሚያስፈልጋት እንደነበር ተናግረዋል፡፡
የፒኤችዲ ፕሮግራም በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ሲጀመር ሦስት ደረጃዎች እንደነበሩት አስታውሰው በወቅቱም የተማሪውን ውጭ መቅረት ዕድልና የመምህራን እጥረት እንዲቀንስ ለማድረግ ታስቦ እንደነበር ገልጸዋል፡፡
በሌላ በኩል የክብር ዶክትሬት ዲግሪ በዓለም አቀፍ ደረጃ ዩኒቨርሲቲዎች ሲሰጥ አካዴሚያዊ ያልሆነ ዕውቅናን በመንተራስ እንደሆነና ተሸላሚዎችም ካላቸው ክህሎት፣ ስብዕና እንዲሁም ያበረከቱት አስተዋጽኦ ጋር በተያያዘ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
የክብር ዶክትሬት ዲግሪ መስጠት የተጀመረው በ1478 በኦክስፎርድ ዩኒቨርሲቲ መሆኑን የገለጹት አቅራቢው፣ ዩኒቨርሲቲውም በወቅቱ ሊዮኔል ውድልቢል ለሚባል ሰው መስጠቱን አስረድተዋል፡፡
እ.ኤ.አ. ከ1478 በኋላ በዓለም አቀፍ ደረጃ በርካታ የክብር ዶክትሬት ዲግሪ መሰጠቱን ጠቅሰው፣ በኢትዮጵያ የክብር ዶክትሬት ዲግሪ ሲሰጥ በዘፈቀደና መሥፈርትን ባላሟላ መልኩ እንደሆነ አስታውሰዋል፡፡
በዓለም አቀፍ ደረጃ ዩኒቨርሲቲዎች የክብር ዶክትሬት ዲግሪ አሰጣጥን የተመለከተ መመርያ እንዳላቸውና መመርያውንም ላላሟሉ ሰዎች የክብር ዶክትሬት ዲግሪ የሚሰጡ ዩኒቨርሲቲዎች እንዳሉ አብራርተዋል፡፡
በኢትዮጵያ በአሁኑ ጊዜ በርካታ ሰዎችን እያሳሰበ የመጣው ጉዳይ ዩኒቨርሲቲዎች የራሳቸው ሰው የሚሉትን ብቻ በመምረጥ የክብር ዶክትሬት እየሰጡ መሆኑ ነው ብለዋል፡፡
የክብር ዶክትሬት ዲግሪን ከዩኒቨርሲቲዎች የሚያገኙ ሰዎች ጭምር እንደመጠሪያ እንደሚጠቀሙበትና ይኼም በጣም የተሳሳተ ነገር እንደሆነ ገልጸው፣ በርካታ የመገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎችም ይኼንን ድርጊት እንደሚፈጽሙ አስታውሰዋል፡፡
ዩኒቨርሲቲዎች የክብር ዶክትሬት ዲግሪ የሰጧቸውን ሰዎች ያልተገባ ድርጊት ከፈጸሙ፣ የክብር ዶክትሬት ዲግሪውን መንጠቅ እንደሚችሉ ጠቁመዋል፡፡
ሪፖርተር

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትስስር ይፍጠሩ

325,851FansLike
49,039FollowersFollow
13,194SubscribersSubscribe