ፍርሐቶቻችን እንደ ጸባዮቻችንና እንደ አኗኗራችን ብሎም እንደሚገጥሙን ወቅታዊ ሁኔታዎች ይለያያሉ፡፡ ከጓደኛ ጸባይ አለመመቸት፣ ከሞት፣ ከሥራ እጦት፣ ከቤተሰብ ሰላም እጦትና ከተለያዩ ነገሮች ጋር ሊያያዝ ይችላል – ፍርሐት፡፡ እነኚህ የተለመዱትና በበርካታ ሰዎች ላይ የሚታዩ የፍርሐት ዓይነቶች ሲኾኑ በዋነኝነት ከሕይወት ስኬት ጎትተው ወደኋላ የሚያስቀሩ ተብለው የተለዩ የፍርሐት ዓይነቶችም አሉ፡፡ psychologytoday.com በተባለው ድረገጽ ላይ አሚ ሞሪን የተባሉት የሥነ ልቦና ባለሙያ 10 የፍርሐት ዓይቶች አስፍረዋል፡፡ ከእነርሱ ውስጥ እኛ ስድስቱን መርጠናል፡፡
1. ለውጥ
በየጊዜው ተለዋዋጭ በኾነች ዓለም ውስጥ ነው የምንኖረው፡፡ ይሁን እንጂ ብዙ ሰዎች ከዓለም ፍጥነት ጋር አብሮ መለወጥን ይፈራሉ፡፡ ሰዎች ለውጥን የሚፈሩት ነገ ምን ይዞ እንደሚመጣ በትክክል ስለማያውቁ ነው፡፡ ለውጥን በድፍረት ያከናወኑ ጥቂቶች ደግሞ ሕይወት ላይ ነግሠው ይታያሉ፡፡ ለውጥን መፍራት በሕይወት ውስጥ ወደኋላ ከሚመልሱን የፍርሐት ዓይነቶች መካከል አንዱ ነው፡፡
2. ብቸኝነት
ብቸኝነት ሲዘወተር ለከባድ የጤና ጉዳት መዳረጉ አይቀርም፡፡ የብቸኝነት ፍርሐት ከልክ ሲያልፍ የጉዳት መጠኑ ከሲጋራ ማጨስ እኩል መኾኑን የሥነ ልቦና ባለሙያዎች ይገልጻሉ፡፡ ስለዚህ ራስን ጤናማ አስተሳሰብ ባላቸው ሰዎች መክበብ አዋጪ ብቻ ሳይኾን ግዴታም ነው፡፡ ይህን ካደረጉ ብቸኝነትን በመፍራት ከስኬት አይጎድሉም፡፡
3. ውድቀት
‹ለውድቀት እዳረግ ይኾን?› ብሎ መጨነቅ የምንሻውን ሥራ በአግባቡና በልበ ሙሉነት እንዳንሠራ ያደርገናል፡፡ ስለዚህ ውድቀትን ፈጽሞ አይፍሩ፡፡ የሚያከናውኗትን እያንዳንዷን ተግባር በማስተዋልና በእርጋታ ያከናውኑ፡፡ ውድቀት ቢገጥምዎ እንኳን መልሶ በማገገም ለስኬት እንደሚበቁ ይመኑና ሥራዎን በአዎንታዊ ስሜት ተሞልተው መሥራትዎን ይቀጥሉ፡፡
4. የተቀባይነት እጦት
ብዙ ሰሰዎች አዳዲስ ሰዎችን ለመተዋወቅ አይደፍሩም፡፡ ምክንያታቸው ደግሞ ‹በሰዎች ዘንድ ተቀባይነት ባላገኝስ?› የሚል ፍርሐት ነው፡፡ ይህን ፍርሐት ይዞ አዳዲስ ሰዎችን አለመተዋወቅ ሊገጥሙዎ ለሚችሉት በጎ ዕድሎችና የሥራ ስኬቶች እንቅፋት መኾኑን ይገንዘቡ፡፡ ስለዚህ ፍርሐትዎን አስወግደው በማንኛውም አጋጣሚ ከአዳዲስ ሰዎች ጋር ይተዋወቁ፡፡
5. እርግጠኛ አለመኾን
ምንም ዓይነት አዲስ ነገር ለመሞከር ካሰቡ የግድ ሙሉ በሙሉ እርግጠኛ እስኪኾኑ አይጠብቁ፡፡ አዳዲስ ነገሮች ሁሌም አጠራጣሪና አስፈሪ መኾናቸው አይቀርም፡፡ ስለዚህ በጥርጣሬ ከሙከራዎ አይሽሹ፡፡ ሕይወት ተመሳሳይ መንገድ ሲኖሯት አሰልቺ መኾኗ ግልጽ ነው፡፡ ስለዚህ እርግጠኛ ያለመኾን ፍርሐትዎ ከስኬት እንዳያርቅዎ ጠንካራ ውሳኔ ይወስኑ፡፡
6. የ‹ክፉ ነገር› ፍራቻ
አዲስ ነገር ስንሞክር ሁሌም ያልጠበቅነው ነገር ይገጥመናል፡፡ ያ ነገር ከአቅማችን በላይ ይኾናል ወይም አሉታዊ ተጽዕኖ ይኖረዋል ብለንም እንፈራለን፡፡ ይህ ፍርሐት ግን ሙሉ በሙሉ ትክክል ላይኾን ይችላል፡፡ ስለዚህ በፍርሐቱ ተገድበን ከስኬት ጉዟችን ፈጽሞ ወደኋላ ማፈግፈግ አይገባም፡፡
6ቱ ጎታች ፍርሐቶች

