አንጋፋዋ ድምፃዊት ራሄል ዮሐንስ ከዚህ ዓለም በሞት ተለየች

በኢትዮጵያ የሙዚቃ ታሪክ ውስጥ ስማቸው በቀዳሚነት ከሚነሱትና በርካታ ተወዳጅ ሥራዎችን ለአድናቂዎቻቸው ካበረከቱት አንጋፋ አርቲስቶች መካከል አንዷ የሆነችው ድምፃዊት ራሄል ዮሐንስ ከዚህ ዓለም በሞት መለየቷ ተሰማ።
አርቲስቷ ከድምፃዊነቷ ባሻገር በሆቴልና መስተንግዶ ዘርፍም ጉልህ አሻራ ያሳረፈች ስኬታማ የሥራ ሰው ነበረች።
ድምፃዊት ራሄል ዮሐንስ መዲናችን አዲስ አበባ ውስጥ በተለይ ካዛንቺስ (ግቢ ገብርኤል) አካባቢ ሚያዚያ 27 ቀን 1939 ዓ.ም ተወለደች። ለቤተሰቦቿ የበኩር ልጅ ስትሆን፣ “ሀና ሀና” በተሰኘው ዝነኛ ዘፈኑ ከሚታወሰው ታናሽ ወንድሟ አንጋፋው ድምፃዊ ሰይፉ ዮሐንስ ጋር የቄስ ትምህርትን እስከ ዳዊት ድረስ ተከታትላለች። የአንደኛ ደረጃ ትምህርቷን ደግሞ በአስፋ ወሰን ትምህርት ቤት አጠናቃለች።
ወደ ሆቴል ሙያ ከፍተኛ ዝንባሌ የነበራት ራሄል፣ በራስ ሆቴል ለ3 ወራት ያህል የአጠቃላይ መስተንግዶ ሥነ-ሥርዓት ሥልጠና ወስዳለች። በመቀጠልም በምርጫዋ በጊዮን ሆቴል የወይን መስተንግዶ ትምህርትን ለሁለት ዓመታት በመከታተል በዲፕሎማ ተመርቃለች።
*በሆቴል ቆይታዋ እንደ ጋማል አብዱል ናስር፣ ሴኩ ቱሬ እና ክዋሚ ንኩርማ ያሉ የአፍሪካና የዓለም መሪዎችን እንዲሁም ከፍተኛ የሀገር ውስጥ ባለሥልጣናትን በከፍተኛ ሙያዊ ብቃት የማስተናገድ ዕድል አግኝታለች።
* ገና በልጅነቷ የበረራ አስተናጋጅ (ሆስተስ) የመሆን ሕልም የነበራት ቢሆንም፣ በየብስ መስተንግዶ (ግራውንድ ሆስተስ) ሥራዋን ጀምራ በሂደት እስከ ጀነራል ማናጀርነት ለመድረስ በቅታለች። በራስ ሆቴል፣ ጊዮን ሆቴል፣ አርጀንቲና፣ ታንዛኒያ እና ፊሊፕስ ኢምባሲ፣ ሸበሌ ሆቴል፣ ሂልተን ሆቴል እንዲሁም በፎርሺፕ ትራቭል የሠራች ሲሆን፣ በግሏም አነስተኛ ሆቴል ከፍታ በስኬት አገልግላለች።
በወቅቱ ከሚያገኟት መደበኛ ደመወዝ ይልቅ በፐርሰንት የሚከፋፈሉት የደንበኞች ስጦታ (ቲፕ) የተሻለ እንደነበር በሕይወት ታሪኳ ታስታውሳለች።
ወደ ሙዚቃው ዓለም መግባትና ስኬታማ አሻራዎች
የአርቲስቷ ወደ ሙዚቃው ዓለም የመግባት ጉዞ የተጀመረው በአጋጣሚ ነበር። አንድ ቀን ድምፃዊ ከተማ መኮንን እና ሌሎች አንጋፋ ሰዎች በቤቷ ተገኝተው ምግብ ከተመገቡ በኋላ፣ በጋሽ ከተማ አጋፋሪነት ጨዋታው ይደራል። እሱ ማሲንቆ ሲጫወት እሷም አብራ ማንጎራጎር ጀመረች። በድምጯ የተደነቁት እንግዶች የምግብ ቤቱን ሥራ ትታ ወደ ሙዚቃው እንድትገባና ድምፃዊ እንድትሆን ያበረታቷት ሲሆን፣ ይህም ለኪነጥበብ ሕይወቷ መነሻ ሆነ።
* በ1970ዎቹ መጀመሪያ (1973/74 ዓ.ም) “አንቺ ባለድሪ” የተሰኘውን የመጀመሪያ አልበሟን ከሻምበል በላይነህ ጋር አወጣች። ለዚህ ሥራዋ በአምባሳል ሙዚቃ ቤት 10,000 ብር የተከፈላት ሲሆን፣ በግጥም ይልማ ገብረአብ እንዲሁም በዜማ አበበ መለሰ ተሳትፈውበታል።
* በ1983 ዓ.ም ከታዋቂዎቹ የሀገር ባህል ተጨዋቾች ከባህሩ ቀኜ እና ከይርጋ ዱባለ ጋር የሠራቻቸው ዘፈኖች በሕዝብ ዘንድ ከፍተኛ ተወዳጅነትን አትርፈውላታል። አራዳ፣ ትዝታ፣ ምኒልክ እና ሀገሬ ኢትዮጵያ በግሏ ከሠራቻቸውና እስካሁንም ድረስ ከሚደመጡ ተወዳጅ ሥራዎቿ መካከል ይጠቀሳሉ።
* አርቲስት ራሄል ዮሐንስ ሙዚቃ እስካቆመችበት ጊዜ ድረስ 13 የሚያህሉ አልበሞችን ያሳተመች ሲሆን፣ ከድምፃዊነቷ ባሻገር የዜማ ደራሲም ነበረች። ምኒልክ፣ ጀግናው ሰራዊት እና የአስናቀች ወርቁን ሥራ በራሷ ዜማ ያደሰችበት እንደ እየሩሳሌም ተጠቃሽ የዜማ ድርሰቶቿ ናቸው። የመጨረሻ ሥራዋ በያሬድ ተፈራ የተቀናበረው “ዘናበል” የተሰኘው አልበሟ ነበር።
አርቲስት ራሄል ዮሐንስ የሁለት ወንድና የአራት ሴት ልጆች እናት ስትሆን፣ በርካታ የልጅ ልጆችንም ለማየት በቅታለች። ልጆቿን በሥነ-ምግባር ለማሳደግ ያሳየችው ጥረትና ጥንካሬ በወቅቱ በግጥም ጭምር እንዲህ ተብሎ ተመስክሮላታል፦
” አዝማሪ ይሏታል ራሄል ሆዴን
” አዝማሪ ይሏታል ጭንቄ ራሄልን
” ልጆች ለማሳደግ ያደረገችውን።
የአንጋፋዋ ድምፃዊት ራሄል ዮሐንስ ማረፍ ለሀገራችን የሙዚቃ ኢንዱስትሪ ትልቅ እጣታ ነው። ለቤተሰቦቿ፣ ለወዳጅ ዘመዶቿና ለአድናቂዎቿ በሙሉ መጽናናትን እንመኛለን።
አንጋፋዋ ድምፃዊት ራሄል ዮሐንስ የቀብር ስነ ስርዓት ዛሬ  ሰኔ 29/2018 በ 8፤00 ሰዓት በሰዓሊተ ምህረት ቤተክርስቲያን ይፈጻማል፡፡

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትስስር ይፍጠሩ

325,851FansLike
49,039FollowersFollow
13,194SubscribersSubscribe