ያያ ቱሬ ‹‹እግር ኳስን ከመጫወት የሚያግደኝ ኃይል የለም››

 

ያያ ቱሬ ‹‹እግር ኳስን ከመጫወት የሚያግደኝ ኃይል የለም››

አሁን 35 ዓመቱ ላይ የሚገኘው የቀድሞው የማንቼስተር ሲቲና ባርሴሎና ተጫዋች ያያ ቱሬ ከሰሞኑ ከስካይ ስፖርት ጋር ባደረገው አንድ ቃለ ምልልስ ላይ በሰጠው አስተያየት ከ40 ዓመቱ በኋላም በጥሩ ሁኔታ እግር ኳስን መጫወት የሚችልበት አቅም እንዳለው ተናግሯል፡፡ ተጫዋቹ ባለፈው ክረምት ከማንቸስተር ሲቲ ጋር ከተለያየ በኋላ ወደቀድሞ ክለቡ የግሪኩ ኦሎምፒኮስ ተመልሶ ለሶስት ወራት ያህል በዚያ ቆይቷል፡፡ ይሁን እንጅ ከሁለት በላይ ጨዋታዎችን እንኳ ሳያደርግ በታህሳስ ወር በስምምነት ተለያይቷል፡፡ ከዚያ በኋላ ሊያስፈርመው ፍላጎት ያሳየ ክለብ አልነበረም፡፡ እናም ተጫዋቹ አሁን ስራ ፈቷል፡፡ እግር ኳስን እየተጫወተ አይደለም፡፡ ግን ተስፋ አልቆረጠም፡፡ ‹‹እግር ኳስን ከመጫወት የሚያግደኝ ምንም ኃይል የለም›› ይላል፡፡

‹‹ወደ ኦሎምፒያኮስ የሄድኩት በስሜታዊነት ሳይሆን አይቀርም፤ እግር ኳስን በፕሮፌሽናል ደረጃ የጀመርኩበት ክለብ ስለሆነና ለደጋፊዎቹ አንድ ነገር ማበርከት ብችል ብዬ ነበር፤ እኔ አለም ላይ ዝነኛ ተጫዋች ነኝ፤ የምጠቅማቸው መስሎኝ ነበር፤ ግን ሁሉም ነገር እንደጠበኩት አልሆነም›› የሚለው ቱሬ ወደ ግሪክ ዳግም መመለሱ ትክክል እንዳልነበረ ያምናል፡፡

አሁን እረፍት ላይ መሆኑን እና ስለቀጣይ ማረፊያው ለመወሰን የሚረዳውን ዝግጅት በማድረግ ላይ እንደሚገኝ የገለጸው ቱሬ ዳግም በፕሪምየር ሊጉ መጫወት እፈልጋለሁ ብሏል፡፡ ይህ ካልሆነ ግን ወደአረብ ሀገራት፣ ወደ እስያ አልያም ደግሞ ወደ አሜሪካ ሊያመራ እንደሚችል ፍንጭ ሰጥቷል፡፡

ቱሬ ከትንሿ የአይቮሪኮስት ከተማ ቦኪ ተነስቶ እስከ አውሮፓ የዘለቀ ዝና ማግኘት የቻለ፣ በታላላቅ የአለማችን ክለቦች ተዘዋውሮ ስኬትን ያጣጣመ አፍሪካዊ ተጫዋች ነው፡፡ ከቤልጅየም እስከ ግሪክ፣ ከፈረንሳይ እስከ ስፔን፣ ከስፔን እስከ እንግሊዝ ተዘዋውሮ በተጫወተባቸው ሁሉም ክለቦች ጣፋጭና የማይረሱ ድሎችን አጣጥሟል፡፡ የስፔን ላሊጋን፣ የአውሮፓ ቻምፒንስ ሊግ፣ የግሪክ ሊግና የእንግሊዝ ፕሪምየር ሊግ ዋንጫዎችን አንስቷል፡፡ በግሉ ደግሞ የቢቢሲ የአፍሪካ የአመቱ ምርጥ ተጫዋች ክብርን ተጎናፅፏል፡፡ ከታላቅ ወንድሙ ጋር በአንድ ክለብ ውስጥ የመጫወት እድልንም ያገኘ ተጫዋች ነው፡፡ በሙሉ ስሙ ኜኜሪ ያያ ቱሬ የሚባለው አይቮሪኮስታዊ የአማካይ ስፍራ ተጫዋች በእግር ኳስ ሸራ ላይ ስማቸውን በጉልህ ከሳሉ አፍሪካውያን ተጫዋቾች መካከል አንዱ ነው፡፡

የልጅነት ህይወት

‹‹የልጅነት ህይወቴ የሚረሳ አይደለም፤ እንደሁሉም አፍሪካዊ ህፃን ነው ያደኩት፡፡ እግር ኳስን ከጧት እስከ ማታ እጫወት ነበር፡፡ ግን በባዶ እግሬ ነበር የምጫወተው፤ በተጨማሪም ጎዳና ላይ ስለምንጫወት ብዙም ምቾት አይሰጠንም፤ ጫማ ለመግዛት ቤተሰቦቻችን ይቸገራሉ፤ በጣም ውድ ነበር፤ በዚያ ጊዜ ጫማ እንዲገዛለት ቤተሰቡን የሚጠይቅ ልጅ የፈረደበት ነው፤ ምክንያቱም አባቱ በንዴት ሊገድለው ይችላል›› በማለት ያያ ቱሬ የልጅነት ህይወቱን በአጭሩ ይገልጸዋል፡፡ ያያ ቱሬ እስከ 10 ዓመቱ ድረስ እግሩ ላይ ጫማ አላደረገም ነበር፡፡ በድህነት ውስጥ ይኖሩ የነበሩት ቤተሰቦቹም ለሱም ሆነ ለሌሎች ልጆቻቸው ጫማ ለመግዛት የሚያስችል በቂ ገንዘብ አልነበራቸውም፡፡

ለእግር ኳስ የሚመች ተክለ ቁመና ያለው ያያ ቱሬ ታላቅ ወንድሙ ኮሎ ቱሬን አርአያ አድርጎ እሱን እየተከተለ ነው ያደገው፡፡ የታላቅ ወንድሙ ስኬታማ የእግር ኳስ ጉዞ በልቡ ውስጥ ትልቅ መነሳሳትን ይፈጥርለት እንደነበር ያያ ቱሬ ተናግሯል፡፡ አስቸጋሪውን የልጅነት ህይወቱን የሚያጣፍጠው በእግር ኳስ ነበር፡፡ ከፊቱ የሚመጣውን ታላቅ ዝናና ውጤት እያሰበ በአቧራማው የሠፈራቸው መንገድ በባዶ እግሩ ኳስ ያንከባልል ነበር፡፡ ህይወት ለሱ አልጋ ባልጋ አልነበረችም፡፡ ከትንሿ ቦኪ ከተማ ተነስቶ ወደ አይቮሪኮስት ዋና ከተማ አቢጃን አስከተጓዘበት ጊዜ ድረስ እግር ኳስን የሚጫወተው በክለቦች ወይም በአካዳሚ ታቅፎ አልነበረም፡፡

እ.ኤ.አ ግንቦት 13 ቀን 1983 የተወለደው ያያ ቱሬ ታላቅ ወንድሙ ወደሚጫወትበት የአቢጃኑ ሚሞሳስ ወጣት ቡድን አባል ከሆነ በኋላ ግን በፍጥነት ወደ ላይ መውጣት ጀመረ፡፡

በሚሞሳስ ወጣት ቡድን ውስጥ ድንቅ ችሎታ እንዳለው ያሳየው ያያ ቱሬ በሃገሩና በአውሮፖ በሚገኙ ታላላቅ ክለቦች እይታ ውስጥ የገባው ወዲያው ነበር፡፡ በጊዜው የአጥቂ መስመር ተሰላፊ ሆኖ ይጫወት የነበረው ቱሬ ተመልካቾችንና የክለብ አሰልጣኞችን ቀልብ ለመግዛት ጊዜ አልወሰደበትም፡፡ በ18 አመቱ የቋሚ ተሳላፊነት አድልን ማግኘት የቻለው ያያ ቱሬ እ.ኤ.አ በ2001 ለቤልጅየሙ ክለብ ቤቨርን ፊርማውን አኖረ፡፡ ክለቡ የአፍሪካ ተጫዋቾችን እያደነ በማስፈረም ይታወቃል፡፡

ቱሬ ከቤልጅየሙ ክለብ በኋላ ለዩክሬኑ ሜታሉ ዶኒስክ ለግሪኩ አሎምፒያኮስና ለፈረንሳዩ ሞናኮ እየተዘዋወረ ተጫውቷል፡፡ በነዚህ ክለቦች ያሳየው ድንቅ አቋም ደግሞ በአውሮፓ ሃያሉ ክለብ ባርሴሎና እንዲፈለግ አድርጎታል፡፡

እ.ኤ.አ በ2007 የፈረንሳዩን ክለብ ምናኮን ለቆ በርካታ ውጤቶችን ያጣጣመበትን ባርሴሎናን ተቀላቀለ፡፡ ባርሴሎናዎች ያያ ቱሬን ያስፈረሙት የተከላካይ አማካይ ስፍራ ላይ እንዲጫወትላቸው ነበር፡፡ ቱሬ የመሃል ተጫዋች ቢሆንም አስፈላጊ ከሆነ ግን በየትኛውም ቦታ የመጫወት ክህሎት አለው፡፡ የሜዳውን ሁሉንም ከፍሎች እያካለለ የሚጫወተው የአፍሪካው ኮከብ በባርሴሎና ለመንገስ የወሰደበት ጊዜ አጭር ነው፡፡ እንደ ሳሙኤል ኢቶ ሁሉ እሱም በክለቡ ውስጥ ታሪክ ከሠሩ አፍሪካውያን ተጫዋቾች አንዱ ለመሆን ችሏል፡፡ በስፔናዊ ተጫዋቾች በተሞላው ክለብ ውስጥ እንደ አልማዝ ያበሩ አፍሪካዊያን ያያ ቱሬና ሳሙኤል ኢቶ ናቸው፡፡

ባርሴሎና በ2009 እ.ኤ.አ የ6 ዋንጫዎች ባለቤት ሲሆን የያያ ቱሬ አስተዋጽኦ ከፍተኛ ነበር፡፡ ክለቡን እስከለቀቀበት ጊዜ ድረስ ቱሬ ለባርሴሎና 100 ጨዋታዎች ላይ ተሰልፎ ተጫውቷል፡፡

ማንቼስተር ሲቲ

አይቮሪኮስታዊው ተጫዋች ያያ ቱሬ የግሉን ብቻ ሳይሆን የክለቦችንም ታሪክ ቀይሯል፡፡ ከባርሴሎና ስኬት በኋላ ወደ እንግሊዙ ማንቼስተር ሲቲ በ2010 የተቀላቀለው ቱሬ ክለቡ ከረዥም አመታት በኋላ የፕሪምየር ሊግ ዋንጫ እንዲያነሳ አስችሏል፡፡

ማንችስተር ሲቲዎች በከተማ ተቀናቃኛቸው ማንቼስተር ዩናይትድ ለአመታት የተወሰደባቸውን ብልጫ ማስመለስ የጀመሩት ቱሬ ክለቡን ከተቀላቀለ በኋላ ነው፡፡ ከ44 አመታት ስኬት አልባ ጉዞ በኋላ ሲቲ የፕሪምየርሊግ ዋንጫን እንዲያነሳ ከማስቻሉም በተጨማሪ የኤፍ ኤ ካፕ ዋንጫን ከ35 አመታት በኋላ ክለቡ እንዲያነሳ የእሱ መኖር አስፈላጊ ነበር፡፡ ምክንያቱም የማሽነፊያዋን ብቸኛ ግብ ያስቆጠረው እሱ ነውና፡፡

በማንቼስተር ሲቲ ያሳየው ድንቅ አቋም በግሉ የተለያዩ ሽልማቶችን እና ክብሮችን እንዲያገኝ አስችሎታል፡፡ የቢቢሲ የአፍሪካ የዓመቱ ምርጥ ተጫዋች ክብርን ከማግኘቱ በተጨማሪ በ2011 እና በ2012 የካፍ የአመቱ ምርጥ ተጫዋች ተብሎም ተመርጧል፡፡

ቱሬ ሜዳ ውስጥ በሁሉም ቦታ ላይ ይጫወታል፡፡ ኳስ ለቡድን አጋሮቹ አስተካክሎ የማቀበል ችሎታው፣ ጉልበቱና ቴክኒኩ እንዲሁም የቅጣት ምት ስፔሻሊስት መሆኑ በስፖርት ባለሙያዎች ዘንድ አድናቆትን አትርፈውለታል፡፡ በወሳኝ ሰዓት የሚያስቆጥራቸው ግቦች ደግሞ የተጫዋቹን ደረጃ በእጅጉ ከፍ አድርገውለታል፡፡ ደጋፊዎችን አስፈንጥዟል፡፡

በአይቮሪኮስት ብሄራዊ ቡድን ውስጥ ብዙ ስኬታማ ተጫዋቾች አሉ፡፡ በአውሮፓ ክለቦች ውስጥ የነገሱና ክለቦቻቸውን ለተለያዩ ክብሮች ያበቁ ተጫዋቾችን በዛ አድርገን መዘርዘር እንችላለን፡፡ ይሁንና እነዚህ ውጤታማ ተጫዋቾች ሃገራቸውን ውጤታማ ማድረግ ተቸግረው ነበር፡፡

በአፍሪካ ዋንጫና በአለም ዋንጫ ከመሳተፍ የዘለለ በዋንጫ የታጀበ ታሪክ አላስመዘገቡም፡፡ ያያ ቱሬ ግን ከዚህ እድለ ቢስ ትውልድ ዝርዝር መውጣት ችሏል፡፡ በ2015 አፍሪካ ዋንጫ ሃገሩን ሻምፒዮን አድርጓል፡፡

ያያ ቱሬ ዝምተኛ ነው፡፡ ከልክ ያለፈ መዝናናት አይመቸውም፡፡ አብዛኛውን ጊዜ የሚያሳልፈው እግር ኳስ በመጫወትና በመመልከት ነው፡፡ ከዚያ የተረፈውን ደግሞ የቪዲዮ ጌሞችን በመጫወት ያሳልፈዋል፡፡ መጠጥ አይወድም፡ ፡ የእስልምና እምነት ተከታይ የሆነው ያያ ቱሬ ወደ ጨዋታ ከመግባቱ በፊት ፀሎት ያደርጋል፡፡ መኪናው ውስጥ ሁሌም የዊትኒ ሆስተንን ሙዚቃ ያዳምጣል፡፡ ለስለስ ያሉ ሙዚቃዎችን መስማት እንደሚወድ ይናገራል፡፡

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትስስር ይፍጠሩ

325,851FansLike
49,039FollowersFollow
13,194SubscribersSubscribe