ሀገርን መውደድ – እንዴት?

ሀገርን መውደድ የሚኖሩባትን መሬት መውደድ ነው፡፡ ሰው የሚኖርባትን መሬት ለመውደድ አስታዋሽ እንደማይሻ ሁሉ ሀገሩንም ለመውደድ አስታዋሽ አያስፈልገውም፡፡ ነገር ግን በተለይ አሁን ባለችው ኢትዮጵያ ለምንኖር ዜጎች እጅግ ፈታኙ ነገር ይህ ይመስላል፡፡ ብዙ ሰዎች በቋንቋና በብሔሮቻቸው ተሸሽገው ሀገራቸው ላይ የጥላቻ ንግግር ሲናገሩ፤ ብሔራዊ ስሜት የሚሰማቸው ዜጎችንም ከማንጓጠጥና ከማሳደድ ጀምሮ ሕይወት እስከማሳጣት ሲደርሱ ይስተዋላል፡፡ ይህ አካሔድ ከወዲሁ ካልተቀጨ መጨረሻው አያምርምና ሀገርን መውደድን ማስታወስ ተገቢ ሳይኾን አልቀረም፡፡
ለመሆኑ ሀገርን መውደድ ከምን ሊመነጭ ይችላል? መገለጫዎቹስ ምንድን ናቸው?
1. የቁሳቁስ መገለጫዎች
አንዳንድ ሰዎች በዚህ ነገር ስኬታማ ናቸው፡፡ አንገታቸው ላይ የሀገራቸውን ባንዲራ ቀለም የያዙ አልባሳት ጣል ያደርጋሉ፡፡ ከእነኚህ ከፍ ያሉት ደግሞ በሸሚዞቻቸው፣ በኮፍያቸውና በተለያዩ ጌጣጌጦቻቸው ሁሉ የሀገራቸውን መለያ መጠቀም የዘወትር ልምዳቸው ነው፡፡ ቤታቸው ውስጥ ባንዲራ መለጠፍ፣ የንጉሦቻቸውንና ሀገራዊ እሴትን የሚያንፀባርቁ ምስሎች መጠቀም፣ የቤታቸው አሠራርና የውስጥ ቁሳቁሶች ሀገራዊ መልክ እንዲኖረው በማድረግ ሌሎችን ያስደምማሉ፡፡ ይህ በየዕለቱ ሀገራቸውን እንዲያስታውሱ፣ ከመጣው ሁሉ መሪ በላይ አስተምራ ያሳደገች ሀገራቸውን ከልባቸው እንዲወዱ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያበረክታል፡፡
2. ታሪክን ማወቅና ማንፀባረቅ
ታሪክን ማወቅ ሀገርን ለመውደድ እጅግ ጠቃሚ ነው፡፡ ሀገራችንን የምንወዳት ስናውቃት ነው፡፡ መጻሕፍትን ማንበብ፣ ታሪካዊ ቦታዎችን መጎብኘት፣ የታላላቅ ሰዎችን ንግግሮች ማድመጥ እንዲሁም በስነ ጽሑፍ፣ በኪነ ጥበብና በሌሎች መስኮች የሚገለጡ የታሪክ አሻራዎችን ተከታትሎ ዕውቀት መቅሰም ተገቢ ነው፡፡ ከዚህ ባሻገር ሃይማኖታዊ የአደባባይ በዓላትና የብሔራዊ በዓላት አከባበር ላይ መገኘት ሌላው አስተማሪ አካሔድ ነው፡፡ በእንዲህ ባሉ አጋጣሚዎች የታሪክ ሰዎችንና ተመሳሳይ ፍላጎት ያላቸውን ሀገር – ወዳድ ዜጎች ማግኘት ስለሚቻል በሀገር አቀፍ ርዕሰ ጉዳዮች በመወያየት ለሀገራችን ያለንን ፍቅር ይበልጥ ማጉላት የምንችልበት አጋጣሚ ይፈጠራል፡፡
3. ንቁ ዜጋ መኾን
ለሀገራችን ያለንን ፍቅር መግለጽ የምንችልባቸውን አጋጣሚዎች ሁሉ እንጠቀምባቸው፡፡ የሀገራችንን የፖለቲካ ሥርዓት ባንወድ እንኳን ሌሎችን የምንወድና ለማኅበረሰባችን ችግር ቀድመን የምንደርስ መኾናችንን ለማሳየት እንሞክር፡፡ ለምሳሌ በበጎ ፈቃደኝነት አገልግሎት ላይ መሳተፍ፣ የገቢ ማሰባሰቢያ ዘመቻዎችን መደገፍ፣ የሀገርን ስም የሚያጎድፉ ተግባራት ሲፈጸሙ በንቃት ከዜጎች ጎን በመቆም የሀገርን ገጽታ የሚገነቡ ቀስቃሽና አስታዋሽ ጽሑፎች መጻፍ፣ ንግግሮች ማድረግ፣ በፖለቲካና ኢኮኖሚ ውድቀት ውስጣቸው የተጎዳ ዜጎችን ማጽናናት እጅግ አስፈላጊ ነው፡፡
ከዚህ ጎን ለጎን ከቀድሞው ሥርዓትና ባህል ያፈነገጡ የአነጋገር፣ የአለባበስ፣ የአኗኗር ዘይቤዎች ሲፈጠሩ ከስር ከስር በመከታተል ማጋለጥና ጥቅም የሌላቸው መኾኑን በማስረዳት የተጣመመውን ማቅናት፣ የተበላሸውን ማስተካከል ያስፈልጋል፡፡
4. ለህፃናት አርአያ መኾን
ለህፃናት የምንነግራቸው ተረቶች፣ ምሳሌያዊ አነጋገሮችና የምናስጠናቸው መዝሙሮች ሀገራቸውን እንዲወዱና ‹ያገባኛል› የሚል ቁጭት የሚያንገበግባቸው ዜጎች ሆነው እንዲቀረጹ የማድረግ ኃይላቸው እጅግ ከፍተኛ ነው፡፡ ከምንም በላይ ደግሞ በተግባር ሀገራችንን የምንወድ ኾነን ስንታይ የእግራችንን ፈለግ የሚከተሉ ህፃናት ይፈጠራሉ፡፡ አዎንታዊ ስሜት የሚፈጥሩና በጎ የኾኑ ጀግኖችን ታሪክ በየአጋጣሚው መተረክ ፈለጋቸውን ከወዲሁ መከተል እንዲጀምሩ ያነሳሳል፡፡ ብሔራዊ መዝሙርን ማለማመድ፣ ሀገር – በቀል ታሪኮችን ማስጠናት፣ የቀድሞ ዘመን ባህል፣ ወግ፣ በጎ ልማዶችና እሴቶችን በዝርዝር ማስጠናት እነርሱ ነገ ለሚረከቧት ሀገር ራሳቸውን ከወዲሁ ማዘጋጀት እንዲችሉ ትልቅ መነቃቃት ይፈጥራል፡፡

መነሻ ምንጭ፡- wikihow.com

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትስስር ይፍጠሩ

325,851FansLike
49,039FollowersFollow
13,194SubscribersSubscribe