ሃካን ሱኩር ከእግር ኳስ ተጫዋችነት እስከ ታክሲ ሹፌርነት

ሃካን ሱኩር በቱርክ እግር ኳስ ታሪክ በርካታ ጎሎችን ያስቆጠረ ተጫዋች ነው። እስካሁንም የሚድርስበት አልተገኘም። በአንድ ወቅት በአውሮጳ እግር ኳስ አሉ ከሚባሉ ተጫዋቾችም አንዱ ነበር።
አሁን ግን አሜሪካ ውስጥ የታክሲ ሹፌር ሆኗል፤ መፃሕፍትም ይሸጣል። እንዴት?
ከአንድ የጀርመን ጋዜጣ ጋር ቆይታ ያደረገው የ48 ዓመቱ ሳኩር ሕይወቱ ባልተጠቀ መንገድ እንዴት እንዲህ ሊሆን እንደቻለ ያስረዳል።
ሱኩር፤ ከቱርክ ፕሬዝደንት ረጂፕ ጣይብ ኤርዶዋን ጋር ያለኝ ቅራኔ ነው ለዚህ ያበቃኝ ይላል። ከእንገድልሃለን ማስፈራሪያ ጀምሮ እስከ ገንዘብ ክልከላ ድረስ የዘለቀ እርምጃ እንደተወሰደበት ይዘክራል።
«ምንም ነገር የለኝም። ኤርዶዋን ሁሉን ነገር ወስዶብኛል። ነፃነቴን ገፎኛል። ሃሳቤን ነፃ ሆኜ መግለፅ ተሳነኝ፤ ሠርቼ መብላት አልቻልኩም።»
በፈረንጆቹ ከ92-2007 ባለው ጊዜ ሳኩር ለቱርክ 112 ጊዜ ተሰልፎ የተጫወተ ሲሆን 51 ጎሎችን አስቆጥሯል። ቱርክ በ2002 የዓለም ዋንጫ ሶስተኛ ስትወጣ የቡድኑ አባል ነበር። የብሔራዊ ቡድኑ የምንጊዜም ኮከብ ግብ አስቆጣሪ ነው፡፡
በዓለም ዋንጫ ታሪክ ደግሞ ፈጣኗን ግብ በማስቆጠር ቀዳሚው ሰው እሱ ነው፡፡ ደቡብ ኮሪያ ላይ በ2002 ግብ ያስቆጠረው ጨዋታው በተጀመረ ገና በ10ኛው ሰከንድ ነበር፡፡
ለእንግሊዙ የእግር ኳስ ክለብ ብላክበርንና ለጣሊያኑ ኢንተርሚላን ይጫወት የነበረው ሱኩር፤ የእግር ኳስ ሕይወቱን አብዛኛውን ጊዜ ያሳለፈው ጋላታሳራይ ለተሰኘው የቱርክ ክለብ በመጫወት ነበር።
ሱፐር ሊግ በመባል በሚታወቀው የቱርክ እግር ኳስ ሊግ እንደ ሱኩር ብዙ ጎል ያገባ እስካሁን አልተገኘም።
ሱኩር ጫማ ሲሰቅል ወደ ፖለቲካ ገባ። በግሪጎሪያን አቆጣጠር 2011 ላይ ምርጫ የኤርዶዋንን ፓርቲ ወክሎ ተዋዳድሮ በማሸነፉ በላይኛው ምክር ቤት የሕዝብ እንደራሴ ለመሆን በቃ።
ነገር ግን ፌቱላህ ጉሌን ከተሰኘው የኤርዶዋን ዋነኛ ተቀናቃኝ ድርጅት ጋር ተያይዞ ስሙ ይነሳ ነበር። የቱርክ መንግሥት ደግሞ 2016 ላይ ለተከሰተውና በርካታ ሰዎችን ለቀጠፈው የቱርክ የመፈንቅለ-መንግሥት ሙከራ ድርጅቱን ተጠያቂ ያደርጋል።
ሱኩር በወቅቱ አሜሪካ ነበር። የመፈንቅለ-መንግሥት ሙከራውንም አጣጥሏል። ነገር ግን የቱርክ መንግሥት ቴሌቪዥን ጣቢያ ተጨዋቹ የፌቱላህ አባል ነው፤ አሁን በጥገኝነት አሜሪካ ይገኛል ሲል ዘገበ።
ዘገባው ሱኩር፤ ሳን ፍራንሲስኮ በተሰኘችው የአሜሪካ የሃብታሞች ከተማ 3 ሚሊዮን ዶላር በሚያወጣ ቤት ውስጥ ይኖራል፤ የራሱ ካፌም አለው ሲል አተተ።
«እርግጥ ነው ካሊፎርኒያ ውስጥ ካፌ ነበረኝ። ነገር ግን የማላውቃቸው ሰዎች ካፌዬን መጎብኘት ጀመሩ። አሁን የኡበር ሹፌር ነኝ።»
ቱርክ ውስጥ ያሉ ቤቶቹ፣ ቢዝነሶቹም ሆኑ የባንክ አካውንቶቹ በኤርዶዋን መንግሥት እግድ እንደተጣለባቸው ይናገራል። የመንግሥትን ወቀሳም ያጣጥላል።
ከዛሬ ሁለት ዓመት በፊት ኒው ዮርክ ታይምስ ከተሰኘው ጋዜጣ ጋር ቆይታ ያደረገው ሱኩር «ሃገሬን እወዳለሁ፣ ሕዝቡን እንዲሁ። ምንም እንኳ ስለኔ ያላቸው አተያይ የተጣመመ ቢሆንም» ብሏል።
በወቅቱ ዘገባው የኤርዶዋን መንግሥትን ጨቋኝነት ያሳያል በሚሉ ሰዎች ዘንድ ትኩረት አግኝቷል።
2018 ላይ የአርሴናሉ አማካይ ሜሱት ኦዚል ከፕሬዝደንት ኤርዶዋን ጋር ፎቶ በመነሳቱ ነቀፌታ አስተናግዶ ነበር። ጀርመናዊው የአርሴናል እግር ኳስ ተጫዋች ሜሱት ኦዚል በዚህ ምክንያት ራሱን ከበሔራዊ ቡድን ማግለሉን አስታውቋል።
ውሳኔውን አስመልክቶ በሰጠው ረዘም ባለ መግለጫ ላይም የ29 ዓመቱ ኦዚል «ከጀርመን እግር ኳስ ማሕበር የደረሰኝ ምላሽ የብሔራዊ ቡድኑን ማልያ ድጋሚ መልበስ እንዳልሻ አድርጎኛል» ሲል አስታውቆ ነበር።
በሩሲያው የዓለም ዋንጫ ደካማ አቋም አሳይቷል ተብሎ የተወቀሰው ኦዚል «ጀርመን በሩስያው የዓለም ዋንጫ ላይ ላሳየችው የወረደ አቋም ሁሉ እኔ ተጠያቂ እየሆንኩ ነው» በማለት ምሬቱን አሰምቷል።
«ሳሸንፍ ጀርመናዊ ስሸነፍ ስደተኛ» ሲልም የተሰማውን ስሜት በፅሑፍ ገልጿል።
ከቱርኩ ፕሬዝደንት ሬሴብ ጣይብ ኤርዶዋን ጋር ፎቶ ተነስተዋል በሚል ኦዚል እና የማንቼስተር ሲቲው አማካይ ኢልካይ ጉንዶሃን ወቀሳ ሲዘንብባቸው እንደነበረ አይዘነጋም።
«እኔና ጉንዶጋን ከፕሬዚዳንቱ ጋር የመከርነው ስለ እግር ኳስ እንጂ ስለፖለቲካ አይደለም» ይላል ኦዚል።
ኋላ ላይ የቱርክ ገዥው ፓርቲ ሁለቱ እግር ኳስ ተጫዋቾች ከፕሬዚዳንቱ ጋር የተነሱትን ፎቶ ለምርጫ ቅስቀሳ ተጠቅሞበታል።
ከክስተቱ በኋላ በርካታ የጀርመን ፖለቲከኞች «ተጫዋቾቹ ለጀርመን ያላቸው አተያይ ጥያቄ የሚያጭር ነው» ሲሉ ተደምጠዋል።
የጀርመን መንግሥት የጣይብ ኤርዶዋን አገዛዝ ላይ የተፈፀመውን መፈንቅለ መንግሥት ተከትሎ ቱርክ የወሰደችውን እርምጃ በፅኑ እንደሚቃወም አሳውቆ ነበር።
ከቱርካዊያን ቤተሰቦች የተወለደው ሜሱት ኦዚል ግን «ከቱርክ ፕሬዝደንት ጋር ፎቶ አልነሳም ብል የአያቶቼን አምላክ እንደናቅኩ ነበር የምቆጥረው ሲል» አቋሙን ግልፅ አድርጓል።
ሃካን ሱኩር በአንጻሩ እንደ ኤርዶሃን የሚጠላው ሰው ያለ አይመስልም፡፡

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትስስር ይፍጠሩ

325,851FansLike
49,039FollowersFollow
13,194SubscribersSubscribe