ሰራዊቱ እስካሁን በተናጠል የተኩስ አቁም ላይ እንደነበር ይታወሳል!
መንግስት በአሸባሪው የሕወሐት ኃይል ላይ “ብርቱና የማያዳግም” እርምጃ እንዲወሰድ አቅጣጫ መቀመጡን የሚያስታውቅ መግለጫ አውጥቷል
መንግስት “ኢትዮጵያን ለማፈራረስ የተነሣ የክህደት ኃይል” ያለውን አሸባሪ የሕወሐት ኃይል እና የውጭ እጆች ስውር ደባ ለመደምሰስ “ብርቱና የማያዳግም” እርምጃ እንዲወሰድ አቅጣጫ ሰጠ፡፡
የሀገር መከላከያ ሠራዊት፣ የክልል ልዩ ኃይሎች እና ሚሊሻዎች የማያዳግም ክንዳቸውን እንዲያሳርፉ አቅጣጫ ማስቀመጡንም ወቅታዊ ጉዳዮችን በተመለከተ ባስተላለፈው መልዕክትና ሀገራዊ ጥሪ አስታውቋል።
“አሸባሪው የወያኔ ቡድን” የተሰጠውን ተደጋጋሚ የመታረም ዕድል ለመጠቀም አለመፈለጉን ያስታወቀው መንግስት ለትግራይ ህዝብ ሲባል ገበሬው ተረጋግቶ እንዲያርስም በማሰብ የተናጠል የተኩስ አቁም ቢደረግም ቡድኑ ከድርጊቱ ከመታቀብ ይልቅ በአጎራባች የአማራ እና የአፋር ክልሎች መግደል፣ መዝረፍ እና ገበሬዎች እንዳያርሱ ማስተጓጎል መቀጠሉን ነው ያስታወቀው፡፡
ሕጻናትን ለጦርነት ማሰለፉን፣ ርዳታ የጦርነት መሣሪያ መሆኑን፣ እናቶችና ወጣት ሴቶች መደፈራቸውን፣ የእምነት ተቋማት የጦር መለማመጃዎች እና የጦር መሣሪያ መጋዘን መደረጋቸውን፣ የርዳታ እህል የጫኑ መኪናዎች ወደ ትግራይ ክልል እንዳይገቡ መስተጓጎላቸውንም በመግለጫው አስቀምጧል፡፡
በመግለጫው በአፋር ክልል በአንድ የሕክምና ተቋም የተጠለሉ ከ200 የሚበልጡ ሰዎች መታረዳቸውንና ከ300,000 በላይ ዜጎች መፈናቀላቸውንም ነው ያስቀምጠው፡፡
ሆኖም ‘ሰራዊቱ አስፈላጊው ርዳታ እንዳይደርስና ሰብአዊ መብቶች እንዳይከበሩ ዕንቅፋት ሆኗል’ እያለ ሲከስ የነበረው ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ይህ ሁሉ ሲሆን በዝምታ ማለፉንም ጠቁሟል፡፡
“ኢትዮጵያን ለመበተን ከተነሳበት የአሸባሪነት ባህሪው ሊላቀቅ ያልቻለው አሸባሪው ቡድን፤ ወጣቶችን በእኩይ ፕሮፓጋንዳ በመደለልና ሕጻናትን በሐሽሽ እንዲናውዙ በማድረግ ለጦርነት እየመለመለ፣ በአፈሙዝ የሚነዱ አዛውንቶችን ጭምር እያሰለፈ ነው” ሲል በመግለጫው ያተተው መንግስት ይህን “ሕዝብ አስጨራሽ የሆነ የሽፍትነት አካሄድ” ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብም ሆነ ለትግራይ ሕዝብ በተደጋጋሚ በመናገር ማስጠንቀቁን አስታውቋል።
ሕዝባዊ መልክ ያለውን ይህን ጥቃት መመከት የሚገባው በዚያው አግባብ ነው ያለም ሲሆን፤ መላው ሕዝብ፣ የሀገር መከላከያ ሠራዊት እንዲሁም የክልል ልዩ ኃይሎችና ሚሊሻዎች “ይህን ኢትዮጵያን ለማፈራረስ የተነሣ የክህደት ኃይልና የውጭ እጆች ስውር ደባ ለመደምሰስ ብርቱና የማያዳግም ክንዳቸውን” እንዲያሳርፉ አቅጣጫ መቀመጡንም ነው ያስታወቀው፡፡
እድሜያቸውና ዐቅማቸው የሚፈቅድላቸው ኢትዮጵያውያን ሁሉ በሀገር መከላከል ዘመቻው እንዲሳተፉ፣ ይህን ማድረግ ያልቻለው የልማት ሥራዎች ተሳትፎውን እንዲያጠናክር እና የመንግሥት ሠራተኛው በሙሉ ዐቅሙ ያለ ቢሮክራሲ ሥራውን እንዲያከናውንም ጠይቋል። ሁሉም ዜጋ ነቅቶ አካባቢውን እንዲጠብቅም ነው ያሳሰበው።
ሚዲያዎች፣ የኪነ ጥበብ ባለሞያዎችና ማኅበራዊ አንቂዎች ሕዝቡ ከሀገሩ ጎን እንዲቆም የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱም ጠይቋል። በውጭ ለሚኖሩ ኢትዮጵያውያንም ጥሪ አቅርቧል።
መንግስት እስካሁን በተናጠል የተኩስ አቁም ላይ እንደነበር ይታወሳል፡፡