ወንዶች በተለያዩ ስፍራዎች ደምቀው ከሚታዩበት እንዲሁም በቀላሉ ትኩረት እንዲስቡ ከሚያደርጋቸው አንዱ ሙሉ ልብስ (በተለምዶ ሱፍ የምንለው) መልበሳቸው ነው።
አንዳንድ ወንዶችም ቄንጠኛ በሆኑና በሚማርኩ ሙሉ ልብሶች ሽክ ብለው መታየት ያዘወትራሉ። ታዲያ ይህን የድምቀትና የኩራት መገለጫ የሆኑ አልባሳት በተለያዩ የግብዣ ቦታዎች ለብሰው ማግኘት የዝግጅቱ አድማቂ የመሆን እድልን ይፈጥርላቸዋል።
እስከዛሬ ሙሉ ልብስን የምናውቀው ሰዎችን ውብ አድርጎ በማሳየት ተግባሩ ብቻ እንደነበር የአደባባይ ምስጢር ነው። ከሰሞኑ ግን ሙሉ ልብስ መልበስ ከማስዋብ የዘለለ ጥቅም እንዳለው እየተነገረ ነው። ፈጣን የማስታወስ ችሎታን ለማዳበርና የተነቃቃ ስነ ልቦና ባለቤት ለመሆን ሙሉ ልብስ መልበስ የተሻለ እንደሆነም በጉዳዩ ዙሪያ የተደረገ አንድ ጥናት አረጋግጧል።
ኦዜድ የተባለ ድረ ገፅ አስገራሚ ዜናዎችን በሚዘግብበት ገጹ ላይ በጉዳዩ ዙሪያ የተደረገን አንድ ጥናት በመጥቀስ እንዳስነበበው፤ ከተለመደው ወጣ ባለ መንገድ አዘውትረው ሙሉ ልብስ የሚለብሱ ሰዎችን አስተሳሰብ እንደሚቀይር፣ የአእምሯቸው የመስራት መጠን እንዲያድግ እንደሚያደርግና የነገሮችን አተያይ እንደሚያሰፋ ጥናቱ ማረጋገጡን ነው የዘገበው።
ዘገባው ተመራማሪዎቹን ጠቅሶ እንዳስነበበው፤ ጥናቱ በሚደረግበት ወቅት በመጀመሪያው ዙር ጥናቱን ለማካሄድ የተወሰዱት ተማሪዎች በመደበኛ የሆነ አለባበስ ለብሰው እንዲመጡ ከተደረገ በኋላ ግራ የሚያጋቡ ጥያቄዎች ቀረቡላቸው፣ በቀጣይ ጊዜ ደግሞ ተማሪዎቹ ሙሉ ልብስ ለብሰው እንዲመጡና ተመሳሳይ ጥያቄዎች እንዲቀርብላቸው ተደረገ፤ ተማሪዎቹ ለጥያቄው የሰጡት መልስ በፊት ከመለሱት ጋር ሲነፃፀር እጅግ አስገራሚና በራስ መተማመንን የሚያሳይ እንደነበር መረጃው ያሳያል። አያይዞም ሙሉ ልብስ በሚለበስበት ወቅት ከማህበረሰቡ የመለየት ስሜት ስለሚያሳድር ከተለመደው አመለካከት አሻግሮ የማየት ዕድል እንደሚፈጥር ተገልጿል።
ሁል ጊዜ በሥራ ቦታም ሆነ በመዝናኛ ስፍራዎች ላይ መደበኛ የሆነ አለባበስ መልበስ የሰዎች አስተሳሰብ ተመሳሳይ እንዲሆን ያደርጋል። ድንገት የሆነ ወቅት ላይ ለየት ያለ ልብስ በተለይ ሙሉ ልብስ ሲለበስ ደግሞ የሰዎች አስተሳሰብ እንደልብሳቸው ሊቀየር እንደሚችል ነው ጥናቱ ማረጋገጡን ዘገባው ያመለከተው።
እውን የሰዎች አለባበስ አስተሳሰባቸ ውን ይወስናል? ሁኔታውን በማስተዋል መልሳችንን ለራሳችን መያዝ እንችላለን።
ሙሉ ልብስና አስተሳሰብ
