‹ስጮህለት የነበረው ለውጥ እውን ሆኗል ›
‹የኢህአዴግ መሪ ህዝብ መሀል ገብቶ አይተን አናውቅ ›
‹ለውጡ በምን አይነት አቅጣጫ እንደሚሄድ ግልጽ ያለ መስመር ስለመኖሩ አላውቅም፤እየጠበቅሁ ነው ›
‹ዛሚ አልተሸጠም፤ ›
‹እኔ እኮ ጥይቱ ፊት ለፊት ቆሜ ነበር ስጮህ የነበረው፤ እነርሱ እንደውም በርቀት ሆነው ነበር የሚጮሁት፤ ቢተኮስም አይነካቸውም ነበር፤ ›
አንጋፋዋ ጋዜጠኛ ሚሚ ስብሃቱ በህዝባዊ ቁጣ ለውጥ ከመጣ ወዲህ ድምጻን አጥፍታ ቆይታለች፤ ከስምንት ወራት የአሜሪካ ቆይታ በኋላ በቅርቡ ወደ ሀገር ቤት የተመለሰችው ሚሚ ጣቢያው ዛሚ በቀድሞ አቅሙና ተነሳሽነቱ ወቅታዊውን ጉዳይ እየዘገበ አይደለም፤ ከለውጡ በፊት አፍቃሪ መንግስት ተደርጋ ትወሰድ የነበረች ሚሚ ጣቢያው በብዙ ተፅእኖ ውስጥ ይሰራ እንደነበርና ያም ሆኖ ግን ያንን ሁሉ መስዋዕትነት አልፎ ‹ላለፉት ሰባት ዓመታት የትኛውም መገናኛ ብዙሃን ባልደፈረበትና ባልተናገረበት ወቅት ይህ ለውጥ እንዲመጣ የሞገትኩ፤ የህብረተሰቡም ድምጽ እንዲሰማ ለህዝቡ ድምጽ የሆንኩ ይካሄዱ የነበሩ ከፍተኛ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን የሙስናውንና የኪራይ ሰብሳቢነቱን በአጠቃላይ በማስረጃ በማስደገፍ ለውጡ ወሳኝና አስፈላጊ እንደሆነ መምጣትም እንዳለበት በሚል ብዙ ሞግተናል፤ ‹ስጮህለት የነበረው ለውጥ እውን ሆኗል › ትላለች፤ በለውጡ ሂደት ፤በአዲሱ አስተዳደርና በቀጣይ የጣቢያው ዕጣ ፈንታ ዙሪያ ሰፋ ያለ ቆይታ አድርገናል፡፡
ቁም ነገር፡- በቅድሚያ አንጋፋዋ ጋዜጠኛ ሚሚ ስብሃቱ ለጊዜሽ አመሰግናለሁ፤
ሚሚ፡- እኔም አመሰግናለሁ ስለተገናኘን፤
ቁም ነገር፡- ለረጅም ጊዜ ከለውጡ ወዲህ ከሀገር ውጭ ሄደሽ ጠፍተሽ መክረምሽ ይነገራል፤ የት ነበርሽ?
ሚሚ፡-እውነት ነው፤አሜሪካ ቆይቼ ነው የመጣሁት፤ በየዓመቱ አሜሪካ ለህክምና እሄዳለሁ፤አሜሪካ ያገለገልኩበት ሀገር አይደል? የጉልበቴን ዋጋ ለመጠቀም የጤና ኢንሹራንስ ስላለኝ በዓመቱ እየሄድኩ የጤና ምርመራ አደርጋለሁ፤ በዚህኛው ጉዞ እንደአጋጣሚ አይኔን ኦፕራሲዮን አድርጌ ስለነበር ከእዛ ጋር የተያያዘ ሌላ ምርመራ ስለነበረ ነው ረዥም ጊዜ የወሰደው እንጂ አለሁ፤
ቁም ነገር፡- ብዙ ቆየሽ?
ሚሚ፡-ወደ ስምንት ወር ቆይቻለሁ፤
ቁም ነገር፡- ከለውጡ በኋላ ራዲዮንሽ ላይ የለሽም ፤ድምጽሽም አልተሰማም፤
ሚሚ፡-ነበርኩ አንድ ጊዜ በቀጥታ ስልክ ገብቼ ነበር ፤ ቁም ነገር፡- በሀገራችን ለውጥ ከመጣ ወደ 10 ወራት ተቆጥረዋል፤ በመጀመሪያ ደረጃ ለውጥ የሚባለው ነገር መጥቷል ብለሽ ታምኛለሽ?
ሚሚ፡-በትክክል ለውጥማ መጥቷል፤ለዚህ አንድና ሁለት የለውም፤
ቁም ነገር፡- እንግዳው ለውጡን ሚሚ እንዴት ታየዋለች?
ሚሚ፡-ለውጡ መጥቷል፤ ላለፉት ሰባት ዓመታት የትኛውም መገናኛ ብዙሃን ባልደፈረበትና ባልተናገረበት ወቅት ይህ ለውጥ እንዲመጣ የሞገትኩ፤ የህብረተሰቡም ድምጽ እንዲሰማ ለህዝቡ ድምጽ የሆንኩ ይካሄዱ የነበሩ ከፍተኛ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን የሙስናውንና የኪራይ ሰብሳቢነቱን በአጠቃላይ በማስረጃ በማስደገፍ ለውጡ ወሳኝና አስፈላጊ እንደሆነ መምጣትም እንዳለበት በሚል ብዙ ሞግተናል፤ ለውጡ በሚመጣበት ወቅት ብዙም እንደ አድጮቼ አላጣጣምኩትም፤ ግን በርቅት ሆኜ ስከታተለው ነበር፡፡ ስጮህለትበ የነበረው ለውጥ መጥቷል፤ ቀደም ሲል በጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ ይመራ በነበረው የቀድሞው ኢህአዴግ የዲሞክራሲ ምኅዳሩ መጥበቡ ግልፅ ነበር፤ የህዝብን ድምፅ ከማዳመጥና ብሶቱን ከመስማት ይልቅ ወደ አምባገነናዊ አሰራር የተሸጋገረበት ሁኔታ ነበረ የነበረው፤ዛሬ የዲሞክራሲ ምህዳሩ ማንም ሰው ከጠበቀው በላይ መጥቷል፤ በእርግጥም ለውጥ በዚህች ሀገር ላይ መምጣት አለበት ብለን ስንታገል ለነበርነው ሰዎች የምስራች ነው፤ የዲሞክራሲ ምህዳሩ ሰፍቷል፡፡ ይህ ራሱ አንድ ትልቅ ለውጥ ነው፡፡ሌላው ለሁለት አስርት ዓመታት ጦርነትም ሰላምም በሌለበት ሁኔታ ውስጥ የነበረው የኢትዮ ኤርትራ ፍጥጫ ቀርቶ ሰላም መውረዱ ትልቅ ለውጥ ነው፡፡ እንዲህ እንዲህ አይነት የተለያዩ ትላልቅ ለውጦች መጥተዋል፡፡ በካፒታል ሌተር መፃፍ ያለበት ለውጥ ነው የመጣው/ሳቅ/
ቁም ነገር፡- ከለውጡ ጋር ተያይዞ ለውጡን ከሚመሩት ዶ/ር አብይ አህመድ ጋር በተያያዘ አዲስ ‹መደመር› የተሰኘ አዲስ ቃል መጥቷል፤ ሚሚ ተደምራለች?
ሚሚ፡-እኔ እንግዲህ ጋዜጠኛ ነኝ፤ጋዜጠኛ የፖለቲካ ርዕዩተ ዓለምን፤ አመለካከትንና ወቅቱን እየተከተለ አይደለም መሄድ ያለበት ፤ እኔ ሀቅ ወዳለበት ነው የምሄደው፤ መደመር ለኢትዮጵያ ህዝብ ጥቅም ሰላምና ለሀገሪቱ አንድነትና ለህዝቦች አብሮ መኖር በመከባበር ለእድገታችን እስከጠቀመ ድረስ ጋዜጠኛ ጥሬ ሀቆች ላይ ተመስርቶ ነው ስራውን መስራት ያለበት፡፡ ነገሮች የሚተረጎሙበት ነገር ላይ ነው ማተኮር ያለበት፤ከዚህ አንጻር የእኔ ራዲዮ ጣቢያ ራሱ ይህንን ሀሳብ ነው ይዞ ሲሰራ ለዓመታት የኖረው፤ ‹ዛሚ የመጨመር ለውጥ ድምፅ ነው› ብለን ነበር ስንሰራ የኖርነው፤ስለዚህ ለውጥ ምንግዜም ያስፈልጋል ብዬ ነው የማምነው፤ በመደመር ስም ይምጣ፤ በመሻሻል ስም ይምጣ ወደ መጨመር የሚወስድ ለውጥ ለህዝብ የቆመ ሚዲያ ሁሉ የሚደግፈው ነው ብዬ ነው የማምነው፤
ቁም ነገር፡- ለውጡ ግን ባለፉት 7 ዓመታት በታየው ችግር ብቻ ነው የመጣው ማለት ይቻላል ወይ፤ አጠቃላይ የ27 ዓመታት የፖለቲካዊ ቀውስ ውጤት አይደለም ብሎ መውሰድ ይቻላል? እዛ ላይ ብዙም ትችት ስታቀርቢ አትታይም፤
ሚሚ፡-መቼም ታዳጊ ሀገር ላይ ነው ያለነው፤ በሀገር ግንባታ ሂደት ላይ ያለን ህዝቦች ነን፤በእዛ ሂደት ውስጥ መነሳት መውደቅ ያለ ነው፡፡ ግን ትርፍና ኪሳራ የምንለው ነገር ይኖራል በዚህ ሂደት ውስጥ፤እኔ ወደዚህ ሀገር ስመጣ ስርዓት ተመስርቶ ያ ስርዓት ውጤት እያመጣ የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦች በመፈቃቀድ በእኩልነት፤ በሀብታቸው ተጠቃሚ ሆነው አንድ የጋራ የኢኮኖሚና የፖለቲካ ማህበረሰብ የሚመሰርቱበት ስርዓት ተመስርቶ ነው የመጣሁት፡፡ ያ ጥረታቸው ደግሞ ውጤት በእርግጥም አምጥቶ ስሟ ተቀይሮ ገፅታዋ ተቀይሮ በኢኮኖሚቸው ፈጣን እድገት ካስመዘገቡ ሀገራት ተርታ የተሰለፈችበት ሂደት ነው ያየሁት፡፡ ይህንን ሂደት ሲመሩ የነበሩ መሪዎች ለህዝብ ጥቅም ከመሆን ይልቅ ለግል ጥቅማቸው እያመዘኑ ሲሄዱ ነገሮች እየተበላሹ መሄዳቸው ግልጽ ነው፤ ሀሳብ የሚያመጣን የሚቃወማቸውን እያሴሩ ዲሞክራሲያዊ ስርዓቱን የመገንባት ሂደቱን ሙሉ ለሙሉ እርግፍ አድርገው በመተው እንዴት እንጠየቃለን? እንዴት እንተቻለን? ሲሉ የነበረበትን ሂደት ተመልክቻለሁ፡፡ከእዛ በኋላ ብዙ የተሰሩ ነገሮች አይተናል፤ብዙ ተስፋዎችን አይተናል፤ ግን ያንን ሁሉ ተስፋ ያጨለመ ተግባራም ተፈፅመዋል፤ ስለዚህ በጎውን በበጎ ጎኑ እያነሳን መተቸት ያለበትን ደግሞ በአግባቡ እየተቸን እንዲስተካከል እየጠቆምን ነው በእኛ በኩል የመጣነው ፤ ያ ነው የሚዲያ ስራ ብዬ የማስበው፤
ቁም ነገር፡- ለውጥ ባለፉት 27 ዓመታት እንደነበር አይካድም፤ ግን አዲሱ አመራር ወደ ስልጣን ከመጣ በኋላ ደግሞ ባለፉት 27 ዓመታት ስለተፈፀሙ ኢ ሰብኣዊ ድርጊቶች ይፋ ሆነዋል፤ አንዳንዶቹ ሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ከደርግ መንግስት ግፎች ጋር የሚነፃፀሩ አንዳንዴም የማይተናነሱ ናቸው፤ ከዚህ አንፃር ያ የ27 ዓመታት ለውጥ የመጣው የሚባለው በምን አግባብ ነው?
ሚሚ፡- እንግዲህ አንተም ጋዜጠኛ ነህ፤ታውቀዋለህ ብዬ ነው የማስበው፤ በእኛ ሀገር የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን፤ የሙስና ጉዳዮችን መንግስት ስልጣኑን አላግባብ ከህግ ውጭ ተጠቅሞ የሚያደርጋቸውን ነገሮች ፈልፍሎ ለማግኘት ለማውጣት ትልቅ ችግር አለ፤ መንግስት ተቆጣጣሪ ያስፈልገዋል የሚባለው ለዚህ ነው፤ ሶስቱ የመንግስት አካላት ማለትም ህግ አውጭው፤ ህግ አስፈፃሚውና ህግ ተርጓሚው ማለት ነው፡፡ ህግ አስፈፃሚው ልጓም ያስፈልገዋል የሚባለው ለዚህ ነው፤አስፈፃሚው ሁሉ ነገር በእጁ እስከሆነ ያንን የፈለገውን ሁሉ እንዳያደርግ ለመቆጣጠር የሚያስችል ሁኔታ ነው ሀገሪቷ ያላት፤ ምክር ቤቱ አለ፤ ከእዛ ደግሞ ሚዲው አለ፤በእኛ ሀገር ያለውን የሚዲያ ተግባርና ሀላፊነት እኔ ላንተ አልነግርህም፤ እኛ ብዙ ጫና እየደረሰብን ነው ስንሰራ የነበርነው፡፡ ከጥቆማ ነበር የምንነሳው፤ ፈልፍለን ለመግባት አንችልልም፤ በሩ እንደሚታወቀው ዝግ ነው፡፡ ግልፅነት የለም፤ ብዙ ያላወቅናቸው ነገሮች ተፈፅመው ሊሆን ይችላል፤ነገር ግን እነዚህ ነገሮችን ግልፅ ሆነው ማስረጃዎች ወጥተው እነኛ ማስረጃዎች መታየታቸው ጥሩ ነው፤ ለሌላ ጊዜ ማስተማሪያ እንዲሆን ማለት ነው፤መንግስት የሚሰራቸው ስራዎች ለሚዲያዎች ግልጽ ስላነበሩ ነው ያ ሁሉ ችግር የተፈጠረው፤ ግልጽነት በሌለበት ሁኔታ መንግስት ከዚህም የከፋ ነገር ሊፈፅም ይችላል፡፡ በየትኛም ዓለም ያለ መንግስት ካልተቆጣጠርነው ስልጣኑን ለማቆየት ብዙ ነገር ያደርጋል፤እኛ ይህንንም ያህል ልንሰራ የቻልነው መስዋዕትነት እየከፈልን ነው፡፡
ቁም ነገር፡- ምነን አይነት መስዋዕትነት?
ሚሚ፡-ለምሳሌ ማስታወቂያ እንዳይሰጠን እየተደረግን ነበር የምንሰራው፤በተለያዩ መንገዶች ጫና ይደረግብናል፤ ጥቆማ የሚሰጡን ሰዎች ራሳቸው ላይ የሚደርስባቸው የተለያዩ ጥቃቶች ነበሩ፤ስለዚህ እንደዚህ አይነት ነገር መውጣቱ አይገርመኝም፤ ትምህርት መውሰድ ካለበት ቀጣዩ መንግስት እንደዚህ አይነት ነገሮች እንዳይከሰቱ ነው፤እርምጃዎች ግልጽነት የተሞላባቸው እንዲሆኑ ስርኣት ማበጀት ያስፈልጋል፡፡
ቁም ነገር፡- ባላፉት 27 ዓመታት ለነበረው ህገ ወጥ ድርጊት ሀላፊነቱን በቀዳሚነት መውሰድ ያለበት ማነው?
ሚሚ፡-ኢህአዴግ ነዋ! እርግጥ አሁን ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ የሚመሩት ኢህአዴግና ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ የሚመሰሩት ኢህአዴግ አንድ አይደለም፡፡ይሄኛው ራሱን በትክክል አድሶ የመጣ ነው፡፡በእዛ ወቅት ለተፈጸሙ ድርጊቶችም ሀላፊነት ያለበት ይሄኛው ኢህአዴግ ነው፡፡አሁንም ያለውን ችግርም ማስተካከል ያለበት ይሄኛው ኢህአዴግ ነው ስልጣን በእጁ ስላለ ማለት ነው፡፡ስለዚህ እኔ ስራዬን በምሰራበት ወቅት የነበረው ኢህአዴግ ነው፡፡ አላሰራ ሲል የነበረውም ኢህአዴግ ነው፡፡ግን ከውስጥ ነው ለውጡ የመጣው፤ በአንድ ንግግራቸው ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ እንዳሉት ለውጡ ከእንቁላል ውስጥ ተበርቅሶ እንደሚወጣ ነው የወጣው ብለዋል፤ይህንን ጀግንነትና ድፍረት የተሞላበት ለውጥ እርምጃ መውሰድ የቻለ ኢህአዴግም በዶ/ር አብይ ስር ተፈጥሯል፤ዶ/ር አብይ አንድ ጊዜ ብቻ አይደለም ኢህዴግን እንዲመሩ የተመረጡት፤ ሁለት ጊዜ ነው በጉባኤም ጭምር የተመረጡት፤ኢህአዴግ እንደዚህ አይነት መሪ ኖሮት አያውቅም፤አዲስ መሪና አዲስ አተያይ ይዞ ነው የመጣው፤ ያም ሆኖ ግን አሁንም ያለው ኢህአዴግ ነው፤ ላለፈውም ችግር ተጠያቂ መሆን ያለበት ኢህአዴግ ነው፤
ቁም ነገር፡- የቀድሞው ኢህአዴግና የአሁኑ ኢህአዴግ የተለያዩ ናቸው ካልሽ ምን አይነት ለውጥ ነው እያሽ ያለሽው?
ሚሚ፡- እንግዲህ ለውጡ ገና ጅማሬ ላይ ነው ያለው፡፡ ለውጡ በምን አይነት አቅጣጫ እንደሚሄድ ግልጽ ያለ መስመር ስለመኖሩ አላውቅም፤እየጠበቅሁ ነው አዲሱ ኢህአዴግ በምን አቅጣጫ እንደሚሄድ፤ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ስራ ላይ ናቸው ብዬ ነው የማስበው፡፡ ምን አይነት ነገሮችን ነው ይዞ የሚመጣው? በአጀማመሩ አይተነዋል፤ ትላልቅ ነገሮችን ነው ይዞ የመጣው፤ዲሞክራሲያዊ ምህዳሩን ሙሉ ለሙሉ ነው የከፈተው፤ ነፃነት እንዲኖር ነው በሩን የከፈተው፤ትላንትና ሊመጡ ይችላሉ ልናያቸው እንችላለን ያላልናቸው አካላት በሙሉ ነው የመጡት፤የኢትዮጵያ ህዝቦች ሰፊ ምርጫ እንዲኖራቸው ያስቻለ ምህዳር ነው ያለው ፤የሴቶችንን ተሳትፎ በምንመለከትበት ጊዜ ከፍተኛ ለውጥ ነው ያለው፡፡ አስታውሳለሁ የቀድሞው ኢህአዴግ የሴቶችን ተሳትፎ ባጣጣለበት ወቅት ለምንድነው እንደዚህ የሚደረገው ብዬ እንደውም የሁለቱ ምክር ቤቶች የጋራ ስብሰባ መክፈቻ ላይ አለመነሳቱን ጠቅሼ መተቸቴን አስታውሳለሁ፤ አሁን ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ሲመጡ 50 ከመቶ ካቢኒያቸውን ሴቶች ነው ያደረጉት፤ይሄ ትልቅ ተስፋ ነው ለማለት እችላለሁ፡፡ ከዚህ አንጻር መጪው ጊዜ ተስፋ ሰጪ ነው ብዬ የማስበው፤የኢህአዴግ መሪ እኮ ህዝብ መሀል ገብቶ አይተን አናውቅ፤ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ግን ህዝብ መሀል እያየናቸው ነው፤
ቁም ነገር፡- ግን እኮ ይህ ለውጥ እንዲመጣ አስቀድመን ስንናገር ነበር፤ የሚሉ ግለሰቦችም የፖለቲካ ፖርቲዎችም እዚህም እዚያም እየተደመጡ ነው?ለውጡ የመጣው በማን ነው?
ሚሚ፡-ብዬ ነበር የሚል የፖለቲካ ጨዋታ የትም አያስኬድም፤ሀቅን ተጨባጭ ሰዶችን ማየት ነው እኔ የምፈልገው፤ ተብሎ ከነበር ዋጋ የለውም፡፡ ካለበለዚያ ቀለበት መንገድን እኮ ደርግ አስቦት ነበር እንደሚባለው ነው፤ ማነው የሰራው ነው ጥያቄው? በተግባር ያሳዩን ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ናቸው፤ ይህ ነገር እንዳይመጣ ነበር ሚዲያውን በእጅ አዙር ሲያሽመደምዱት የነበረው፤ በተለይ እንደ ዛሚ አይነት የሚያጋልጣቸውን ሚዲያ በቀጥታ አልነበረም ለማሽመድመድ የሚሞክሩት፤ በቀጥታ ቢመጡ ለህዘብ እንደምናጋልጣቸው ስለሚያውቁ በተዘዋዋሪ ነበር ተጽዕኖ ለመፍጠር የሚሞክሩት፤
ቁም ነገር፡- ምን አይነት ተፅእኖ?
ሚሚ፡-ለምሳሌ ብሮድ ካስት ባለስልጣን ዛሚን ለማዘጋት ለማስፈራራት ሞክሮ ነበር፤ህዝብ ፊት ነበር የታገልነው፤ህገ ወጥ ደብዳቤ ተፅፎልን አንበረከክም ብለን ምላሽ የሰጠነው በግልጽ ነው፡፡
ቁም ነገር፡- በመንግስት ተፅእኖ ይደረግብን ነበር ብትይም ለመንግስት ቅርበት ካላቸው ሚዲያዎች መሀከል አንዱ ዛሚ እንደሆነ ነው የሚታወቀው፤ለምሳሌ የኢህአዴግ ኢንዶውመንት ድርጅቶች ናቸው ያንቺ ጣቢያ ስፖንሰሮች?
ሚሚ፡-ድርጅቶቹ ስፖንሰር የሚደርጉት ለራሳቸው ጥቅም አኳያ ነው፤ ዛሚ የሚደመጥ ሬዲዮ ጣቢያ ስለሆነ ማስታወቂያቸውን በዚህ ጣቢያ ላይ ማስነገራቸው እንደውም የድርጅቶቹን ብልጠት ነው የሚያሳየው፤በእኛ በኩል ስፖንሰር ከየትኛውም አካል ይምጣ እንቀበላለን፤ በድብቅ ያደረግነው ነገር የለም፤ ምስጢር የለም ፤በግልፅ ህዝብ እያየ እየሰማ ነው ማስታወቂያው የሚተላለፈው፤ በአንድ ወቅት እንደውም ወ/ሮ አዜብን ቃለ መጠይቅ ባደረኩበት ወቅት በግልጽ ላደረጉልን ድጋፍ አመስግኛለሁ፤ማስታወቂያ አጥተን ወደ መዘጋት በደረስንበት ወቅት ይህንን ሁሉ ድርጅት ይዛችሁ ለምንድነው ማስታወቂያ የማትሰጡን እናስተዋውቅላችሁ ብለን ጠይቀን ነው ከኢፈርት የተሰጠን፤ እንደማንኛውም ድርጅት ነው ግንኙነታችን፤
ቁም ነገር፡- ሜቴክስ?
ሚሚ፡-ከሜቴክ ያገኘነው ገንዘብ የለም፤ የወሰድነው ጀነሬተር ነው፤ጀነሬተር አጥተን ጣቢያችን ሊቆም ነበር፤ በሀገር ውስጥ ራሱ የሰራውን ጀኔሬተር ነው የሰጠን ፤የጀኔሬተሩን ዋጋ ወደ ማስታወቂያ ቀይረን ነበር ማስታወቂያ ስናስኬድላቸው የነበረው እንጂ አምስት ሳንቲም ከሜቴክ አልወሰድንም፤ምናልባት ካለማወቅ ወይም ለማወቅ ካለመፈለግ ካልመነጨ በቀር ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጀምሮ ቴሌ ብትል 80 ከመቶ ማስታወቂያ አስነጋሪ መንግስት በሆነበት ሀገር ዛሚ የሚሰጠው ማስታወቂያ አልነበረም፤ ቢሰጠን ኖሮ ደግሞ እዚህ ደረጃ ላይ አንገኝም ነበር አሁን፤
ቁም ነገር፡- ግን ቅድም እንዳልሽው ዛሚ ተደማጭ ራዲዮ ጣቢያ ከሆነ ማስታወቂያ በራሱ እንዴት ሳይመጣ ቀረ፤ አይጋጭም?
ሚሚ፡-ፍርሃት ነዋ! ፍርህት አለ፤ ይነግሩናል እኮ የግል ድርጅቶቹ ፍርሃት እንዳለባቸው፤ እንደውም አንዳንዶቹ ስማችን ሳይነገር በጀርባ በኩል ገንዘብ እንስጣችሁ የሚሉ ነበሩ፤ እኛ ይህንን ልናደርግ አንችልም፤ ከተሰጠን በግልጽ በአደባባይ መናገር አለብን ብለን የመለስናቸው ብዙ ኢንቨስተሮች ነበሩ፤ስለሚያስፈራሯቸው ግን ማስታወቂያ አይሰጡንም፤
ቁም ነገር፡- ዛሚ አሁን በምን ደረጃ ላይ ነው ያለው፤ ቅርብ ጊዜ የወጡ ያልተረጋገጡ መረጃዎች ስለመሸጡ ይገልፃሉ፤ ዛሚ ተሸጠ ወይስ ተከራየ?
ሚሚ፡-እንግዲህ ባለፈው ጊዜ ያሳለፍነው ችግር ብዙ ደቁሶናል፤አድማጮቻችንም በሚገባ የሚያውቁት ነው በምን አይነት አስቸጋሪ ሁኔታዎች ውስጥ እንደምንሰራ፤ከዚህ በኋላ ለሚዲያ ስራ በጣም የተሻለ ጊዜ ይሆናል የሚል እምነት ነው ያለኝ፡፡ ዛሚ አልተሸጠም፤ እንደዛ የሚባል ነገር የለም፤ አቅም እያሰባሰብን ነው፤እስከ ዛሬ ድረስ ብቻችንን ስንውተረተር ቆይተናል፤አገልግሎታችንን በተሻለ ሁኔታ መቀጠል እንፈልጋለን፤ ስለዚህ አሁን በአዲስ መልክ የመጣው ለውጥ ህጋዊና መዋቅራዊ ለውጦችን ይዞ እስከ ሚመጣ ድረስ ጊዜ ይወስዳል፤እስከ እዛ ድረስ ይህንን ጊዜ እንዴት ነው መወጣት ያለብን በሚል የተለያዩ አማራጮችን እያየን ነው፡፡ ከተለያዩ የመገናኛ ብዙሃን ጋር በመቀናጀት አቀራረባችንንና አድማሳችንን የማስፋት እቅዶችን እየፈተሽን ነው፡፡ እኛ ያለን አቅም አለ፤ሌላው ደግሞ የፋይናንስ አቅም አለው፤ ያንን አንድ ላይ አድርገን ለመጓዝ እየሞከርን ነው፤
ቁም ነገር፡- የሰራተኞቹ ወቅታዊ ሁኔታስ በምን ደረጃ ላይ ነው፤ ማለት ደሞዝ እየተከፈላቸው አይደለም ይባላል፤
ሚሚ፡-ውሸት ነው፤ደሞዝ ቀርቶ አያውቅም፤ እኔ ጦሜን እውላለሁ እንጂ የሰራተኞቼ ደሞዝ አይቀርም፤ዛሚን ወርቄን እየሸጥኩ ነው እዚህ ደረጃ ያደረስኩት፤
ቁም ነገር፡- ከናሁ ቴሌቪዥን ጋር ተያያይዞ የተሰማው ዜና ምን ያህል እውነት ነው?
ሚሚ፡-የተወሰነ እውነት አለው ውሸትም አለው፤እንዳልኩት ጣቢያውን ለማስቀጠል ከተለያዩ ተቋማት ጋር ንግግር ጀምረናል፤ አንዱ ናሁ ቴሌቪዥን ነው፤እነሱ የሚፈልጉት ነገር አለ፤ እኛም እንደዚሁ፤ስለዚህ ገና እየተነጋገርን ነው፤ገና አላለቀም፤
ቁም ነገር፡- ብዙ ጊዜ ስትናገሪ ኢህአዴግ የአፈፃጸም እንጂ የርዮተ ዓለም ችግር የለበትም ትያለሽ፤ አሁን የመጣው ለውጥ ግን በመሠረቱ ርዮተ ዓለማዊ መሆኑን የሚያመለክቱ ስር ነቀል ናቸው፤ ከቀድሞው ኢህአዴግ ባህሪ ጋር የማይሄዱ ብዙ ለውጦች እየተደረጉ ነው፤ ይሄ የርዕዮተ ዓለሙን ችግር አያሳይም?
ሚሚ፡- እንግዲህ ቀደም ሲል የነበረው ኢህአዴግ ይከተለው የነበረው መመሪያው ልማታዊ መንግስት ነኝ የሚል ነው፤ ይሄ ደግሞ በዓለም የኢኮኖሚ ርዕዮት ውስጥ ያለ መስመር ነው፤ በብዙ ሀገሮችም ውስጥ ተሞክሮ የተሳካ መሆኑ የተፈተሸ ነው፡፡ እኛም ሀገር ለውጥ አላመጣም ለማለት አይቻልም፤ እኔ እንደጋዜጠኛ ኢህአዴግን ልሞግት የምችልው ይዞ በመጣውና መመሪያዬ ነው በሚለው ርዕዮተ ዓለም መሠረት ነው፡፡ስለዚህ ባለው መሠረት ነው መፈተሸ ያለበት፡፡ ለምሳሌ የኢኮኖሚ ፖሊሲው ለሀገር ውስጥ ባለሀብትን አቅም ፈጥሬ ነው ግዙፍ የሚባሉ ተቋሞችን ለውጭ ባለሀብቶች ክፍት የማደርገው የሚል መመሪያ ነበር ሲከተል የነበረው፤አሁን ደግሞ ይሄን ስለመቀየሩና ብዙዎቹ ሀገራዊ ግዙፍ ተቋሞች ለውጭ ሽያጭ ስለመከፈታቸው ተነግሯል፤ ግን ግልፅ ያለ የፖሊሲ ለውጥ ስለመኖሩ የቀረበ ነገር የለም፤ እንዳኩት አሁንም ያለው ሀገር እየመራ ያለው ኢህአዴግ የሚባል ፖርቲ ነው፤ግን የእነዚህ ነገሮችን ተግባራዊ ሲያደርግ የወጡ የህግ ማእቀፎች ምንድናቸው? ብዙ ህግጋት መቀየተር እንዳለባቸው ይሰማኛል፤ ከልማታዊ መንግስትነት ወደ ሊብራል መንግስትነት ወይም ወደ ካፒታሊዝም ለመቀየር ብዙ ማሻሻያዎች መደረግ አለባቸው፡፡ ይህንን ለውጥ በአጭር ጊዜ እያየን አይደለም፡፡ግልፅ የፖሊሲና የርዕዮተ ዓለም ለውጥ አደርጋለው ብሎ መግለጫ ከሰጠ በኋላ ነው የአሁኑንም መንግስት ባልከው መሠረት ሰርተሃል ወይ? ብለን መጠየቅ ያለብን እንደጋዜጠኛ፡፡
ሚሚ ያደረገችው ቃለ መጠይቅ በቪዲዮ ከታች የምታዩት ነው!
(ክፍል ሁለት ይቀጥላል!!)