ማንቸስተር ሲቲ የእንግሊዝ እግር ኳስን ይቆጣጠር ይሆን?

በጣልያን ዩቬንቱስ፣ በጀርመን ባየርሙኒክ፣ በፈረንሳይ ፓሪስ ሴንት ዠርማ እንዲሁም በስፔን ደግሞ ባርሴሎና የበላይነቱን ለአመታት ተቆጣጠረውታል፡፡ በእንግሊዝ ግን የተለየ ነው፡፡ ለረጅም ዓመታት ሳይቋረጥ የሚዘልቅ የአንድ ወይም ሁለት ክለብ የበላይነት የለም፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ማንቼስተር ሲቲ የጀመረው አካሄድ ግን ያስፈራል፡፡ በለሎች ሊጎች የምናየው ነገር በተወዳጁ እንግሊዝ ፕሪምየር ሊግ ላይም እንዳናየው ያሰጋል፡፡
እጅግ ድንቅ ፉክክር የታየበት የእንግሊዝ ፕሪሚዬር ሊግ ያለፈው ወድድር ዘመን እነሆ በአዲሱ ተተክቷል።
‹‹አውሮፓ ውስጥ ተፅዕኖ ፈጣሪ የሆነው የእንግሊዝ ፕሪሚዬር ሊግ የዓለማችን ሀብታም ክለቦች የሚገኙበት ቢሆንም አደጋ የተጋረጠበት ይመስላል። አደጋው ደግሞ የባለፈው ውድድር ዘመን ሻምፒዮን ማንቸስተር ሲቲ ነው›› ይላል የቢቢሲ ስፖርት ተንታኙ ቤን ሱዘርላንድ።
የእንግሊዝ ፕሪሚዬር ሊግ ተወዳጅ እንዲሆን ካደረጉት ጉዳዮች መካከል ዋነኛው ልብ-አንጠልጣይ ፉክክር የሚታይበት መሆኑ ነው። ፈጣን፣ ፈታኝ እና የማይጠበቁ ውጤቶች የሚመዘገቡበት ሊግ ነው። ቢሆንም ይህ ምስል አደጋ ላይ ይመስላል።
በዓመታት ሂደት ሊጉ ስድስት ኃያላን ክለቦች ተብለው የሚታወቁትን አምርቷል። ማንቼስተር ዩናይትድና ማንቼስተር ሲቲ፣ ሊቨርፑል፣ አርሴናል እና የከተማ ተቀናቃኙ ቶተንሃም እንዲሁም የምዕራብ ለንደኖቹ ቼልሲ።
አደጋው እዚህ ጋ ነው። በሂደት ስድስቱ ኃያላን ቀርቶ አንድ ኃያል እንዳይሆን የሚል ስጋት።
የስጋቱ ምንጭ
ያለፈው ውድድር ዘመን እጅግ ተወዳጅ ያደረገው ሊቨርፑል የሲቲን እግር እየተከተለ ዋንጫ ለማግኘት ያደረገው ጥረት ነበር።
ነገር ግን ሁለቱም ክለቦች የቋመጡለትን ዋንጫ ተቀያይረው አግኝተዋል። ፕሪሚዬር ሊግን የቋመጠው ሊቨርፑል ቻምፒዮንስ ሊግ ሲያነሳ፤ ቻምፒዮንስ ሊግን ለማንሳት የሻተው ሲቲ የሊጉን ዋንጫ ወስዷል።
ሊቨርፑል የሊጉን ዋንጫ ካነሳ ሶስት አስርት ዓመታት ተቆጥረዋል፤ በአቡ ዳቢ ቱጃሮች የተያዘው ሲቲ ደግሞ ቻምፒዮንስ ሊግ አንስቶ አያውቅም።
ሲቲ ዘንድሮ የሊጉን ዋንጫ ማንሳት ከቻለ ሌላ ታሪክ ይፅፋል። በአንድ ውድድር ዘመን በርካታ ጎሎች በማስቆጠር እና በርካታ ነጥቦች በማምጣት ሲቲ ሪከርዱን ይዟል።
በኤፍ ኤ ዋንጫ ዋትፈርድን 6-0 በመርታት ተመልካችን አጀብ አሰኝተዋል። ይህን ያዩ የኳስ ተንታኞች ‘እግር ኳስ ከስማለች’ እስከማለት ደርሰዋል።
የፈርናንዲሆ ምትክ ያስፈልጋቸዋል እየተባሉ ሲታሙ የነበሩት ሲቲዎች ባለተሰጥዖው ሮድሪን አስፈርመዋል። በዘመናዊ እግር ኳስ ምርጡ አሰልጣኝ የሚል ስያሜ የተሰጠው ፔፕ ጉዋርዲዮላን የያዙት ሲቲዎች ወደፊትም ተፅዕኖዋቸው እንደሚቀጥል ይገመታል።
የተሻለ የእረፍት ጊዜ ያሳለፉት ሲቲዎች በኮሚኒቲ ሺልድ ጨዋታ ሊቨርፑልን መርታት ችለዋል። በአቋምም ሆነ በስነልቡና ጥንካሬ ከሊቨርፑል የተሻሉ ሆነው ነበር የታዩት።
በሌላ በኩል ሌሎች ኃያላን ሲቲን ተቋቁመው የሊጉን ዋንጫ ያነሳሉ ማለት ከባድ ነው።
አርሴናሎች ፔፔን ቢያስፈርሙም፤ ተከላካይ መስመሩ አሁንም ጥገና የሚያሻው ይመስላል። ኪዬራን ቲየርኒን ከሴልቲክ፣ ዴቪድ ልዊዝን ደግሞ ከቼልሲ ማስፈረማቸው ሳይዘነጋ።
አዲስ አሰልጣኝ የቀጠሩት ቼልሲዎች ኤደን ሃዛርድን ለቼልሲ ቢሸጡም በተጣለባቸው ቅጣት ምክንያት ተጫዋች መግዛት አልቻሉም። ይህ ደግሞ ለአዲሱ አሰልጣኝ ፍራንክ ላምፓርድ ሁኔታዎችን የሚያከብድበት ይመስላል።
የዩናይትዱ ኦሌ ጉናር ሶልሻዬር ቡድኑን የተቀበለ ሰሞን ድንቅ አቋም ቢያሳይም ወደ መጨረሻ ከበድ ያለ ጊዜ አይቷል። ዩናይትዶች ሊጉን ያሸንፋሉ ተብሎ የተሰጣቸው ግምት ከእስከዛሬው እጅግ ዝቅ ያለ ነው።
ታድያ የእነዚህ ኃያላን ቡድኖች እንደ ሲቲ ዝግጁ አለመሆን ለሊጉ አደጋ መሆኑ አይቀርም። እንደ ጣልያን [ጁቬንቱስ ለ8 ተከታታይ ዓመታት ዋንጫ ያነሳበት]፤ እንዲሁም ጀርመን [ባየርንሚዩኒክ ለሰባት ተከታታይ ዓመታት] ሊጎች አጓጊነቱ የወረደ እንዳይሆን ነው ዋነኛው ስጋት።
በየወሩ ክፍያ እየከፈሉ የሚመለከቱ ተመልካቾች ክፍያቸውን ሊያቋርጡ ይችላሉ፤ በተለይ ደግሞ እንግሊዝ የሚገኙቱ የሃገሪቱ ምጣኔ ሃብት ማሽቆልቆል ከማሳየቱ ጋር በተያያዘ።
በዓለም አቀፍ ደረጃም ቢሆን ፉክክር የማይታይበት ሊግን ለማዬት ተመልካቾች ብዙም ጉጉት ላያሳዩ ይችላሉ የሚል ስጋት አለ። ጣልያን እና ጀርመን የአፍሪቃ እና እስያ ተመልካቾችን ለመመለስ ብዙ ትግል እያደረጉ እንዳለ ልብ ይሏል።
አውሮፓ ሱፐር ሊግ እውን ከሆነ አደጋው ለፕሪሚዬር ሊግም ጭምር ነው።
ሲቲ በገንዘቡ ነው ዋንጫ እየገዛ ያለው የሚለው ትላልቅ የሊጉ ክለቦች ጭምር ሊቀላቀሉ ይችላሉ። 500 ሚሊዮን ዩሮ ደግሞ የሱፐር ሊግ ዓመታዊ ገቢ ሊሆን እንደሚችል እየተነገረ ነው። ምንም እንኳ የሱፐር ሊግ ሃሳብ ከ98 የአውሮፓ ክለቦች በ94ቱ ተቃውሞ ገጥመውም።
ግን ዕቅዱ እንዳለ ነው። ማን ያውቃል ከጊዜ ወደ ጊዜ የደጋፊዎች ቁጥር እየጨመረ ሊመጣ ይችል ይሆናል።
ቶተንሃም፣ ቼልሲ እና አርሴናል ባለፈው ዓመት አንድ ወቅት ላይ ለሊጉ ለዋንጫ ያሰፈሰፉ ቡድኖች ነበሩ። ቢሆንም ከተስፋ ውጭ ምንም የተጨበጠ አልነበረም። ይህ ደግሞ ደጋፊዎቻቸው በጊዜ ሂደት እየሸሹ እንዲመጡ ምክንያት ሊሆን እንደሚችል ሳይታለም የተፈታ ነው።
ደጋፊዎች ሁሉንም የቀጥታ ሥርጭት ጨዋታዎች ከፍለው መመልከት አይችሉም። አውሮፕ ሊግ ጨዋታዎች ግን ክፍያቸው እንግሊዝ ፕሪሚዬር ሊግ ያነሰ ነው። ይህ ደግሞ ትልቅ አደጋ ነው።
ማንቸስተር ሲቲ መቆም ካልቻለ የእንግሊዝ ፕሪሚዬር ሊግ ዕጣ ፈንታ ከሴሪ ኤ፣ ቡንደስሊጋ እና የስኮቲሽ ፕሪሚዬርሺፕ የተለየ የሚሆን አይመስልም፤ የአንድ ቡድን ፍፁም ተፅዕኖ የሚታይበት ሊግ።
የእንግሊዝ ፕሪሚዬር ሊግ አሁን ላይ አጓጊና እና ኃያል ይመስላል፤ በዚህ ከቀጠለ ግን አወዳደቁ የሚያምር አይሆንም።

Kumneger Media
Kumneger Media
Kumneger Media is a News and Entertainment Website & Channel. Kumneger Media in addition to News and Entertainment it is the hub of Politics, Movies, Drama, Music, Comedy, Documentary and More!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትስስር ይፍጠሩ

325,851FansLike
49,039FollowersFollow
13,194SubscribersSubscribe