ራስን መናቅ – ለምን?

አንዳንድ አስቸጋሪ ሁኔታዎች ሲገጥሟችሁ የራሳችሁን አቅም ትጠራጠሩ ይሆናል፡፡ በዚህም ስጋትና ጫና ውስጥ ትገባላችሁ፡፡ ይህ ደግሞ አዳዲስ ነገሮች ለመሞከር የሚኖራችሁ ተነሳሽነት ላይ የሚያሳድረው ተጽዕኖ ከፍተኛ ነው፡፡ ስለዚህ ከዚህ ችግር ለመላቀቅ ትችሉ ዘንድ በራስ መተማመናችሁን ማዳበርና ጤናማ የሕይወት ምርጫዎችን መከተል ይኖርባችኋል፡፡ ይህን ማድረግ ትችሉ ዘንድ ተከታዮቹን ተግባራት ተለማመዷቸው፡፡

  1. አሉታዊ ንግግር ቀንሱ

ራስን መናቅ ስለራስ አሉታዊ ሃሳቦች ከማሰብና አሉታዊ ንግግሮች ከመናገር ይጀምራል፡፡ እንዲህ ዓይነት ልማድ ካላችሁ መለስ ብላችሁ ራሳችሁን በመጠየቅ አስተሳሰቦቹ ወይም ንግግሮቹ የሚፈጥሯቸውን ጉዳቶች ከመነሻው ለማስቀረት መሞከር ተገቢ ነው፡፡ ከዚህ ጎን ለጎን ፈተና ይሆኑብኛል ብላችሁ የምታስቧቸውን ነገሮች በዝርዝር በማስፈር እያንዳንዱን ፈተናዎች ማለፍ የምትችሉበትን መንገድ ማዘጋጀትም ያስፈልጋል፡፡ አስፈላጊ በሆኑ ሁኔታዎች ውስጥ ራስን መውቀስ ጥሩ ቢሆንም ወደ መማረርና ቅስም ወደ መስበር ከሔደ ግን ራስን ወደመናቅ ይመራል፡፡

  1. በራስ መተማመናችሁን አሳድጉ

ራሳችሁን ከማንም ጋር አታነጻጽሩ፡፡ በሕይወት ውስጥ ሁሉም ሰው የየራሱ ጥንካሬና ደካማነት አለው፡፡ ስለዚህ የራሳችሁን ዓይነት ቀለም ይዛችሁ ኑሩ፡፡ በተለይ ለዚህ የራስ መተማመን እጦት ከሚዳርጓችሁ ነገሮች አንዱ ከመጠን በላይ የሆነ ማኅበራዊ ሚዲያ አጠቃቀም ነው፡፡ ሰዎች ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ጥሩ እና የሚያስቀና ገጽታቸውን ብቻ የመለጠፍ ልማድ አላቸው፡፡ ስለዚህ ማኅበራዊ ሚዲያ አጠቃቀማችሁ ላይ ገደብ አብጁና ራሳችሁን የምታዳምጡበት ሰዓት አመቻቹ፡፡

  1. ስህተት አያስደንግጣችሁ

‹የማይሳሳተው የማይሠራ ብቻ ነው› ይባላል፡፡ ዕውነት ነው፡፡ በተለያዩ የሥራ አጋጣሚዎች መሳሳት ያለና የሚያጋጥም ክስተት ነው፡፡ ስለዚህ በመሳሳታችሁ ሳታዝኑ ከእያንዳንዱ ስህተታችሁ በመማር የተሻለ ስብዕና ለመፍጠር ሞክሩ፡፡

  1. የጤናማነት ተግባራትን አከናውኑ

መደበኛ የስፖርት ሰዓት ቢኖራችሁ ለአካላዊ ቅልጥፍናና ለውስጥ ብሎም ለአእምሮ ጤና የሚኖረው ጠቀሜታ እጅግ ከፍተኛ ነው፡፡ እያንዳንዱን ቀን በአዎንታዊ ስሜት ተቀበሉት፡፡ ከአመጋገባችሁ ጀምሮ ለራሳችሁ ደህንነት ጥንቃቄ ማድረግ አትዘንጉ፡፡

  1. የእንቅልፍ ሰዓታችሁን አክብሩ

የተረጋጋ የእንቅልፍ ሰዓት ለአካላዊም ሆነ ለአእምሯዊ ጤንነት ይረዳል፡፡ በተቃራኒው በቂ እና ሰላማዊ እንቅልፍ አለማግኘት በግላችሁም ሆነ በማኅበራዊ ኑሯችሁ እንዳትረጋጉና ከትርፍ ይልቅ ለኪሳራ እንድትዳረጉ ምክንያት የሚሆን ነው፡፡

በአጠቃላይ ራስን መናቅ የሚመጣው የራስን ዋጋ ጠንቅቆ ለማወቅ ካለመቻል ነው፡፡ ከማንም በላይ በከበረ መንገድ እጅግ የከበረውን የሰው ልጅ ሆናችሁ ተፈጥራችኋል፡፡ ከዚህም በላይ ጤናማና የትኛውንም ነገር የመሥራት አቅም ያለው አእምሮ አላችሁ፡፡ የምትኖሩባት ዓለም ሙሉ ባትሆን እንኳ በተሰጥኦዋችሁና በእያንዳንዱ የሕይወት አጋጣሚዎች ተጠቅማችሁ ‹የተናቃችሁ› መስላችሁ እንድትታዩ የሚያደርጉ አሉታዊ ስሜቶችን ማስወገድ ይገባችኋል፡፡

Kumneger Media
Kumneger Media
Kumneger Media is a News and Entertainment Website & Channel. Kumneger Media in addition to News and Entertainment it is the hub of Politics, Movies, Drama, Music, Comedy, Documentary and More!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትስስር ይፍጠሩ

325,851FansLike
49,039FollowersFollow
13,194SubscribersSubscribe