ሱዳን የግድቡን ሙሌት በተመለከተ ከኢትዮጵያ ያገኘቸውን መረጃ “ብዙም ዋጋ የለውም” አለች

ሙሌቱን በማስመልከት የመስኖ ሚኒስትሯ ለኢትዮጵያ አቻቸው ለኢ/ር ስለሺ በቀለ (ዶ/ር) ደብዳቤ ጽፈዋል፡፡

ካርቱም ግድቡን የተመለከቱት የመረጃ ልውውጦች በአስገዳጅ የህግ ማዕቀፎች ስር መፈጸማቸውን እንደምትሻ አስታውቃለች፡፡

የግድቡን ሁለተኛ ዙር ሙሌት በተመለከተ “ብዙም ዋጋ የለውም” ያለችውን መረጃ ከኢትዮጵያ ማግኘቷን ሱዳን አስታወቀች፡፡

የ2ኛ ዙር ሙሌቱን በማስመልከት የሃገሪቱ የመስኖ እና ውሃ ሃብት ሚኒስትር ያሲር አባስ (ፕ/ር) ለኢትዮጵያ አቻቸው ለኢ/ር ስለሺ በቀለ (ዶ/ር) ደብዳቤ ጽፈዋል፡፡

በደብዳቤያቸው “ኢትዮጵያ ለተከታታይ 2ኛ ዓመት ግድቡን ለመሙላት መወሰኗ በሱዳን ላይ አደጋን ደቅኗል” ብለዋል፡፡

ኢትዮጵያ ግድቡን ለ2ኛ ዙር ለመሙላት የወሰነችው የግድቡን መካከለኛ የውሃ መተላለፊያ መንገድ ለመገንባት በወሰነችበት እንደ ጎርጎሮሳውያኑ አቆጣጠር በወርሃ ግንቦት የመጀመሪያ ሳምንት ነው የሚለው ደብዳቤው የውሃ ፍሰቱ ከታችኞቹ የግድቡ የውሃ መተላለፊያ በሮች አቅም በላይ ሲሆን ውሃው መከማቸቱና በግድቡ አናት ላይ መፍሰሱ ግልጽ ነው ሲል ያትታል፡፡

“ሙሌቱን በተመለከተ የሰጣችሁን መረጃ ለሱዳን እምብዛም ዋጋ ያለው አይደለም” ሲል የሚያብራራም ሲሆን በሮዛሪዬስ ግድብ ላይ ሊመለስ የማይችል ነገር መሰራቱን ይጠቁማል፡፡

ሱዳን ሙሌቱ ሊያስከትል ይችላል ያለችውን ምጣኔ ሃብታዊና ማህበራዊ ተጽዕኖ ለመቀነስ በርከት ያሉ እርምጃዎች ወስዳለችም ይላል ደብዳቤው፡፡

ሆኖም እርምጃዎቹ በግድቦቿ ላይ ሊደርስ ከሚችለው ተጽዕኖ ጥቂቱን ብቻ ሊያስቀሩ የሚችሉ እንደሆኑ ይጠቅሳል፡፡

“ይህ ኢትዮጵያ በወጉ ካለመተባበሯ የመጣ ነው” የሚሉት ያሲር አባስ ሁኔታው “የትብብር እና ጉልህ ጉዳትን ያለማስከተል ዓለም አቀፍ የውሃ መርሆዎች የሚቃረን ነው” ሲሉ ያሳስባሉ፡፡

ህዳሴ ግድብን መሰል ግዙፍ ግድቦችን መሰረታዊ እና እጅግ አስፈላጊ ጥናቶችን ሳያደርጉ መሙላት እና ማስተዳደር በእንዲህ ዓይነት ጉዳዮች ላይ የተለመዱ ዓለም አቀፍ አካሄዶችን መጣስ እንደሆነም ነው አባስ በደብዳቤያቸው የገለጹት፡፡

ሃገራቸው ሙሌቱን የተመለከተው የመረጃ ልውውጥ ከግድቡ ደህንነት እና ሌሎችም ተጽዕኖዎች ጋር ለተያያዙት ስጋቶቿ ምላሽ በሚሰጥ መልኩ በአስገዳጅ የህግ ማዕቀፎች ስር እንዲፈጸም እንደምትሻም ገልጸዋል፡፡

ይህን በተመለከተ ኢትዮጵያ በባለፈው ታህሳስ መባቻ ላይ ለሱዳን በጻፈችው ደብዳቤ ይህንኑ አቋም ማንጸባረቋንም ነው ሚኒስትሩ ያስታወሱት፡፡

የተቋረጠው የሶስትዮሽ ድርድር በቶሎ እንዲጀመር ሃገራቸው ያቀረበችውን ጥያቄ ኢትዮጵያ ትቀበለዋለች የሚል ተስፋ እንዳላቸውም አባስ በደብዳቤው ገልጸዋል፡፡

ሱዳን ድርድሩ በአፍሪካ ህብረት፣ በዓለም አቀፋዊ እና ቀጣናዊ ተቋማት ቡድን እንዲመራ ሃሳብ ስለማቅረቧም በደብዳቤው ተጠቅሷል፡፡

ግድቡ በፍትሀዊነት እና በምክንያታዊነት የሚጠቅም የጋራ ፕሮጀክት መሆኑን ደጋግማ የገለጸችው ኢትዮጵያ የታችኞቹን የተፋሰሱን ሀገራት በማይጎዳ መልኩ እንደሚገነባ ማስታወቋም የሚታወስ ነው፡፡

Kumneger Media
Kumneger Media
Kumneger Media is a News and Entertainment Website & Channel. Kumneger Media in addition to News and Entertainment it is the hub of Politics, Movies, Drama, Music, Comedy, Documentary and More!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትስስር ይፍጠሩ

325,851FansLike
49,039FollowersFollow
13,194SubscribersSubscribe