ሲኒማ ኢትዮጵያ ሊዘጋ ነው ተባለ

መቼም ሲኒማ ኢትዮጵያ ገብቶ ፊልም ያላየ ሰው ይኖር ይሆን? ይኖራል፤ ግን የከተማ ልጅ ሆኖ ፊልም ለማየት የመጀመሪያ ሲኒማ ቤቱ ሲኒማ ኢትዮጵያ ስለመሆኑ አያጠራጥርም፤ እናስ? እናማ ከአሜሪካ ፊልሞች ጀምሮ እስከ ህንድ ፊልም ድረስ እየተጋፋን የተመለከትንበት ሲኒማ ኢትዮጵያ በቅርቡ ሊዘጋ ስለመሆኑ  እየተነገረ ነው፤ ለምን አልክ?

ነገሩ እንዲህ ነው፤ ሰሞኑን መቼም ራሱን ኪቤአድ በማለት ይጠራ የነበረው የአሁኑ የፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን እስከ ዛሬ ድረስ ቤት የማከራይበት  ዋጋ ላይ ጭማሪ ሳላደርግ ነው የኖርኩት በማለት በንግድ ቤቶች ላይ የዋጋ ጭማሪ ማድረጉን መቼም ሰምተሃል አይደል? ጭማሪው አንዳንዶችን ከገበያ ውጭ የሚያደርጋቸው ስለመሆኑ የመጣባቸው የዋጋ ጭማሪ ያሳያል ፡፡ ለምሳሌ አልክ? ለምሳሌ ከገበያ ውጭ የመሆን ዕጣ ፈንታ ከሚገጥማቸው የንግድ ድርጅቶች መሀከል አንዱ የሆነው ሲኒማ ኢትዮጵያ  ነው ተብሏል፤

ከኪቤአድ ተከራይቶ እነዛን ሁሉ ፊልሞች ሲያስኮመኩመን የኖረው ሲኒማ ኢትዮጵያ በወር ይከፍል የነበረው ኪራይ ብር 7800 የነበረ ሲሆን አሁን ኪቤአድ አጠናሁት ብሎ የጨመረበት የወርሃዊ ኪራይ 193 ሺ ብር ስለመሆኑ ሰራተኞቹ ለቁም ነገር መፅሔት ሹክ ብለዋል፡፡እናስ? እናማ ሲኒማ ኢትዮጵያ የመንግስት ተቋም በመሆኑ አቤቱታውን ለሚመለከተው መ/ቤት ቢያስገባም እስከ ዛሬ ድረስ ምላሹ ዝምታ ብቻ ሆኗል ተብሏል፡፡

የውጭ ሀገር ፊልሞችን እየገዛ ለተመልካች ሲያሳይ የኖረው ሲኒማ ኢትዮጵያ የውጭ ምንዛሬ ከጠፋበት ጊዜ ጀምሮ ፊቱን ወደ ሀገር ቤት ፊልሞች አዙሮ የአማርኛ ፊልሞች በ30 ብር እያሳየ ነው የነረው፡፡ ሲኒማ ቤቱ በዚህ ዋጋ የሚቀጥል ከሆነ የመግቢያ ዋጋው ላይ ቢያንስ ከ150 ብር በላይ ይሆናል ተብሏል፡፡ በፒያሳ ምድር በ30 ብር ፊልም ሲያይ የኖረ ተመልካች በ150 ብር ፊልም ሊያይ ይችላል ወይ የሚለው አነጋጋሪ ሆኗል፡፡

የኪቤአድ ብትር ያረፈው በሲኒማ ኢትዮጵያ ላይ ብቻ መሰለህ እንዴ? እናስ? የኪነጥበባት ማህበራትም ተመሳሳይ የመጥፋት አዝማሚያ እያሳዩ ስለመሆኑ ሰሞኑን ይፋ ሆኗል፡፡ ከሙያ ማህበራት መሀከል ስታዲየም አካባቢ በሚገኘው የኪቤድአድ ህንፃ ላይ ቢሮ የተከራዩት የኢትዮጵያ ሙዚቀኞች ማህበር፤ የኢትዮጵያ ደራሲያን ማህበር፤ የኢትዮጵያ የቴአትር ሙያተኞች ማህበር፤ የኢትዮጵያ የስዕልና ቅርፃ ቅርፅ ሙያተኞች ማህበርና የኢትዮጵያ የጤና ሙያተኞች ማህበር ከፍተኛ የተባለ የኪራይ ጭማሪ ተደርጎባቸዋል፡፡

አምስቱ ማህበራት  በወር 1200 ብር ይከፍሉ የነበረ ሲሆን አሁን በተደረገው የዋጋ ጭማሪ  እያንዳንዳቸው 12 ሺ 600 ብር በድምሩ 63 ሺ ብር እንዲከፍሉ ተወስኖባቸዋል፡፡ ማህበራቱም አገልግሎት ሰጪ መሆናቸውን በመጥቀስ አቤቱታቸውን ለኪቤአድ ያስገቡ ሲሆን ለእነርሱም የተሰጠው ምላሽ ዝምታ ብቻ ሆኗል፡፡

ለመሆኑ የኪነ ጥበባት ማህበራቱ በወር ይከፍሉ የነበረው ምን ያህል እንደነበር አውቀሃል? አላወቅሁም? በወር ብር 240 ብር፤ ከ240 ብር 12 ሺ 600 ብር፤ በል ቻዎ…

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትስስር ይፍጠሩ

325,851FansLike
49,039FollowersFollow
13,194SubscribersSubscribe