ስደት በከፍተኛ ሁኔታ መባባሱ በጥናት ተመለከተ

ከኢትዮጵያ ወደ ተለያዩ የውጭ አገሮች፣ ከገጠር ወደ ከተማና ከክልል ወደ ክልል የሚሰደዱ ሰዎች ብዛት ከፍተኛ መሆኑ መረጋገጡን፣ በምሥራቅና በደቡብ አፍሪካ የማኅበራዊ ሳይንስ ምርምር ተቋም (ኦስሪያ) አስታወቀ፡፡

ተቋሙ ላለፉት አምስት ዓመታት፣ ‹‹ማይግሬሽን አውት ኦፍ ፖቨርቲ›› በሚል ርዕሰ ባደረገው ምርምር ያረጋገጠው ነገር ቢኖር ስደትን ሕግ በማውጣትና ድንበር (መተላለፊያን) በመዝጋት ማስቆም እንደማይቻል፣ የምርምሩ ባልደረባና በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ሶሻል አንትሮፖሎጂ መምህር ፈቃዱ አዱኛ (ዶ/ር) ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

ተቋሙ ሐሙስ ግንቦት 8 ቀን 2011 ዓ.ም. በሐያት ሬጀንሲ ሆቴል ለአንድ ቀን ባዘጋጀው ዓውደ ጥናት፣ ‹‹በኢትዮጵያ ስደትን የሚያመቻቹ የተለያዩ አካላት›› በሚል ርዕሰ ጥናታዊ ጽሑፍ ያቀረቡት ተመራማሪው እንዳብራሩት፣ ስደት በሕጋዊና  በሕገወጥ መንገድ ይካሄዳል፡፡ ሕገወጥ የሰዎች ዝውውርን (ስደትን) ለማስቆም ሕግ አውጥቶ፣ ድንበር ዘግቶና ግብረ ኃይል በማቋቋም ለማስቆም ጥረት ቢደረግም፣ ሊያስቀረው እንዳልተቻለ በተደረገው ምርምር መረጋገጡን ተናግረዋል፡፡ ምክንያቱ ደግሞ ሕገወጥ የሰዎች ስደት የሚፈጸመው በብዙ ተዋናዮች መሆኑን የጠቆሙት ፈቃዱ (ዶ/ር)፣ ሕጋዊ መንገድን የሚያስይዝ አካላት በሌላ በኩል ደግሞ ሕገወጡንም የሚያስፈጽሙበት መንገድ መኖሩን መረጋገጡን ጠቁመዋል፡፡

በመተማና በሞያሌ ያሉት መሸጋገሪያ ድንበሮች መዝጋት ቢቻል በሌሎች በማይታወቁ መውጫ አቅጣጫዎች ስደቱ ተባብሶ እንደሚቀጥል፣ በተለይም ባለፈው አንድ ዓመት ውስጥ በተደረገ ጥናት ሊታወቅ መቻሉን አስረድተዋል፡፡

ድንበሮችን ለመዝጋትና ለመቆጣጠር የሚሳተፈው የሰው ብዛት ብዙ መሆኑን የጠቆሙት ተመራማሪው፣ ድንበሮቹ ክፍት ቢሆኑ ግን የሚሳተፉ ተዋናዮች በጣም ትንሽ እንደሚሆኑም ጥናቶች ያሳያሉ ብለዋል፡፡

የመውጫ ድንበሮች ሲዘጉም ሆነ ሲከፈቱ ወጪ እንዳላቸው፣ ነገር ግን ሲዘጋ ከሚመደበው በጀት ይልቅ ሲከፈት የሚመደበው እጅግ ያነሰ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡ ሰው ድንበር ዘሎ ለመሄድ እስከተነሳ ድረስ መሸጋገሪያ ድንበሮችን ዘግቶ ማስቆም እንደማይቻል የገለጹት ተመራማሪው፣ በምርምር የተደረሰበትና ስደትን ለማስቆም የተሻለ ሆኖ የተገኘው መጀመርያ ስደት የሚበዛባቸውን አካባቢዎች መለየት መሆኑን ተናግረዋል፡፡ አካባቢውና ችግሩ ተለይቶ ከታወቀ በኋላ ለድንበር ጥበቃ፣ ለማስተማርና ችግር ሲደርስ ችግሩን ለመከላከል የሚመደበውን በጀት ለሥራ ፈጠራ እንዲውል ማድረግ መሆኑንም አክለዋል፡፡

ይህ ዓይነት ድጎማ በሌሎች አገሮችም ተሞክሮ ውጤት ያመጣ በመሆኑ፣ በኢትዮጵያም ተግባራዊ እንዲሆን የምርምር ውጤቶችን ለፖሊሲ አውጪዎች እንደ ግብዓት እያቀረቡ መሆኑንም አስረድተዋል፡፡

ስደት የሚጀመረው ከቤተሰብ በሚደረግ ግፊት፣ በደላሎች፣ በኤጀንሲዎችና መንግሥታዊ ባልሆኑ ድርጅቶች ጭምርና እስከ ውጭ አገር ድረስ ባሉ የተለያዩ አካላት በመሆኑ መከላከል አስቸጋሪ መሆኑን አስረድተዋል፡፡ መንግሥት ሕገወጥ የሰዎች ዝውውር ላይ ዘመቻ ከፍቶ ለማስቆም እየሞከረ መሆኑን ጠቁመው፣ ሕገወጡና ሕጋዊው የሰዎች ዝውውር ብዙም ስለማይለያይና ሕገወጡን የሚያቀናጀው ሕጋዊው በመሆኑ ማስቆም አደገኛ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ሕገወጥ ዝውውሩን ለማስቆም ከአፍሪካ ኅብረት፣ ከእንግሊዝ መንግሥት፣ ከጀርመን ተራድኦና ከሌሎችም ለጋሽ አገሮች በርከት ያለ ገንዘብ ቢመደብም፣ የመንግሥት ሰዎችም በሁለት መንገድ መንቀሳቀስ ስለሚችሉ ማስቆም ከባድ መሆኑን አክለዋል፡፡ ነጋዴ፣ ቤተሰብና ዘመድ አዝማድ በገንዘብ፣ ቤተ ክርስቲያንና መስጊድ ደግሞ በፀሎት እየረዱ እንዲባባስ የሚያደርጉትን ስደት ማስቆም የሚቻለው፣ የመሰደድ ምክንያትን በማጥናትና ለመከላከል የሚደረገውን ወጪ ለስደተኞቹ ማቋቋሚያ ፕሮጀክት ነድፎ ሥራ በመፍጠርና እንደ ችሎታቸው በማሰማራት ብቻ መሆኑን በምርምሩ እንደ ተደረሰበት አስረድተዋል፡፡

ስለስደት ሲወራ ብዙ ጊዜ ትኩረት የሚደረገው ስደተኛ ላይ መሆኑን የጠቆሙት ደግሞ፣ የኦስሪያ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ትሩፌና ሙኩና (ዶ/ር) ናቸው፡፡ ስደት እንደ መጥፎ ነገር ተደርጎ ቢወሰድም፣ በሌላ በኩል ግን አገርንም ሆነ ቤተሰብን የሚጠቅም እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡

ለሥራ የሚሰደድ አንድ ዜጋ ከሄደበት አገር ሲመለስ የዕውቀት ሽግግር አድርጎ ስለሚመለስ፣ በአገሩና በሕዝቡ ላይ ውጤት በማምጣት ሊጠቅም እንደሚችል አስረድተዋል፡፡ ለተቋማትም የአቅም ግንባታ የሚሆን ዕውቀት ይዘው እንደሚመለሱ፣ በክፍያ ከውጭ አገሮች የሚመጡ መምህራንንም መተካት እንደሚችሉም ገልጸዋል፡፡

በምርምር የተገኘው ውጤት በአገር ውስጥ የተለያዩ ፕሮጀክቶችን በማቋቋምና በመደገፍ፣ ወደ ውጭ አገሮች የሚደረግን ስደት ማስቆም የሚቻል መሆኑንም አክለዋል፡፡

ጥናታቸውን ለፖሊሲ አውጪዎች በግብዓትነት መልክ በማቅረብ መንግሥት ትኩረት እንዲያደርግበት እንደሚያደርጉም ትሩፌና (ዶ/ር) ገልጸዋል፡፡ ዜጎች የሚሰደዱት ራስንና ቤተሰብን ለመርዳት በመሆኑ፣ መንግሥት በእርሻ ላይ ፕሮግራም አድርጎ ቢሠራ ሊቆም የሚችል መሆኑንም አክለዋል፡፡ በተለይ ተቋሙ ከገጠር ወደ ከተማና ከትንሽ ከተማ ወደ ትልቅ ከተማ፣ እንዲሁም ከክልል ወደ ክልል በሚደረገው ስደት ላይ ትኩረት አድርጎ እየሠራ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

የሰዎች ዝውውር በዓለም ላይ ያለና የሚኖር ተፈጥሯዊ ሒደት መሆኑን የገለጹት የሠራተኛ ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ተወካይ ወ/ሮ መሰለች አሰፋ፣ በሕገወጥ የሚደረግ የሰዎች ዝውውር ዓለም አቀፋዊ፣ አኅጉራዊ፣ ቀጣናዊና ብሔራዊ ችግር እየሆነ መምጣቱን ተናግረዋል፡፡ በተለይ በሴቶች፣ በሕፃናትና ወጣቶች ላይ የሚደርሰው ችግር ከፍተኛ በመሆኑ፣ ዓለም አቀፍ የመቆጣጠሪያና የመከላከያ ኮንቬንሽኖችና ዲክላሬሽኖች ተቀርፀው አገሮች የሕጋቸው አካል ለማድረግ እየሠሩ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ ኢትዮጵያም እንደ መነሻ፣ መሸጋገሪያና መዳረሻ ስለምትቆጠር የተለያዩ የመከላከያ ሕጎችን፣ ሥልቶችንና አደረጃጀቶችን በመፍጠር እየሠራች መሆኗን አስታውቀዋል::

ምንጭ፡ ሪፖርተር

Kumneger Media
Kumneger Media
Kumneger Media is a News and Entertainment Website & Channel. Kumneger Media in addition to News and Entertainment it is the hub of Politics, Movies, Drama, Music, Comedy, Documentary and More!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትስስር ይፍጠሩ

325,851FansLike
49,039FollowersFollow
13,194SubscribersSubscribe