ቀራፂ በቀለ መኮንን ስለ አፄ ኃይለ ሥላሴ ሐውልት ይናገራል

ለአፍሪካ አንድነት ድርጅት መመስረት ጉልህ ሚና ከነበራቸው መሪዎች መካከል በቀዳሚነት የሚጠቀሱት የግርማዊ ቀዳማዊ አፄ ኃይለ ሥላሴ የመታስቢያ ሐውልት በአፍሪካ ሕብረት ቅጥር ጊቢ ውስጥ የካቲት 03/2011 ዓ.ም ተመርቋል።

በሥነ ሥርዓቱ ላይ የአፍሪካ ሕብረት አዲስ አበባ ውስጥ በሚያካሂደው 32ኛ የመሪዎች ጉባኤ ላይ ለመሳተፍ የመጡ የሃገራት መሪዎች እና የተጋበዙ እንግዶች ተገኝተዋል። የእርሳቸው ሐውልት መቆሙንም ተከትሎ በርካቶች ሲነጋገሩበት ነበር።

ሐውልቱን ከቀረፁት ቀራፂያን መካከል በግምባር ቀደምትነት የሚጠቀሱትን ሰዓሊና ቀራፂ እንዲሁም በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ሥነ ጥበብና ዲዛይን ትምህርት ቤት መምህር የሆነውን ተባባሪ ፕሮፌሰር በቀለ መኮንንን አነጋግረናል።

ቢቢሲ፡ የቆመው ሐውልት ጃንሆይን አይመስልም የሚሉ አስተያየቶች ሲሰሙ ነበር። ለዚህ ያለህ ምላሽ ምንድን ነው?

በቀለ፡ አንድ ሥራ ተሰርቶ ሲጠናቀቅ ብዙ ዓይነት ሃሳብ እንደሚመጣ ይጠበቃል። ሃሳቦቹ ትክክል ናቸው ማለት ግን አይቻልም፤ እኔም ሰምቻቸዋለሁ። ስለዚህ ይህንን አስተያየት የሰጡት በሙሉ ንጉሡንም ሐውልቱንም አይተዋቸው አያውቁም።

ይህንን ሃሳብ ይዘው ሲጨቃጨቁ የነበሩት አንድ ተማሪ በስርቆሽ ያነሳውን የሐውልቱን ፎቶ ይዘው ነው፤ ዛሬ ላይ ሳይ ቀረብ ብለው ሐውልቱን የጎበኙ ሰዎች ‘አፉ በሉን! ‘እያሉ ሲለጥፉ አይቻለሁ። (ሳቅ) ፎቶ ሲነሳ ጥንቃቄና ሙያ ይጠይቃል እንግዲህ ንጉሡ አልፈዋል (ሳቅ) የቢቢሲው ጋዜጠኛ ያነሳውን ፎቶግራፍ ገፃችሁ ላይ አይተው በእርሱ መዳኘት ይችላሉ። የንጉሡ ቤተሰቦችም በእያንዳንዱ ሒደት ይጎበኙት ነበር፤ አሁን ባለውም ደስተኞች ናቸው።

ቢቢሲ፡ ሐውልቱን ለመስራት እንደ ሞዴል የተጠቀማችሁት ፎቶ ግን የትኛውን ነው?

በቀለ ከ300 ፎቶግራፎች በላይ ከተለያዩ ቦታዎች ተሰብስበው ስናጠና ነው ቆየነው፤ ቅርፅ ለመስራት አንድ ፎቶ ብቻ መጠቀም አይቻልም፤ በእርግጥ እርሳቸውን መግለፅ ይኖርበታል። አንድ እንግሊዛዊ ቀራፂ ንጉሡ በሕይወት እያሉ እንግሊዝ በቆዩበት ጊዜ አጠገባቸው ሆኖ እያየ ሁለት ሦስት መልክ ያለው ሐውልት ሰርቷል። የጥበብ ሥራ በመሆኑ ቅርፁን ስታይው ጃንሆይን አይመስሉም።

በመሆኑም በአፍሪካ ኅብረት ምስረታ ጊዜ የነበሩ ፎቶግራፎች ብዙ ናቸው። ወደ 100 የሚሆኑ በአፍሪካ ህብረት ምስረታ ወቅት የነበሩ ፎቶዎችን ሰብስበናል። እንግዳ ሲቀበሉና ስብሰባ ሲያደርጉ የሚለብሷቸው ልብሶችና የሚገልጿቸው አካላዊ ገለፃዎች ላይ ተመስርቶ ተሰራ እንጂ የአንድ ፎቶግራፍ ውጤት ብቻ አይደለም።

ቢቢሲ የተጠቀምከው ጥበባዊ ግነት አለ?

በቀለ፡ በትክክል! እጃቸውና ደረታቸው ላይ፤ ደረታቸው አካባቢ ገነን ለማድረግ ሞክረናል። የጠቢቡ ነፃነት የሚባል ነገር አለ አይደል? በማይበላሽና ከስርዓት በማይወጣ መንገድ ገነን ለማድረግ ሞክረናል፤ ሌላው ሰውነታቸው መለስ ይላል። በእርግጥ በአካልም እንደዚህ ነበሩ። እጃቸውንም ሲፅፉ እንደሚታየው፤ እኛም ዳቦ ስንቀበል እንዳየነው ሎጋ፣ ቀጠን ቀጠን ያሉ ጣቶችን በማድረግ የምንችለውን ሁሉ አድርገናል።

ቢቢሲ፡ ሐውልቱ ከምንድን ነው የተሰራው?

በቀለ፡ የተሰራው ከነሃስ ነው።

ቢቢሲ፡ በቀላሉ በዝናብና በፀሀይ እንዳይበላሽ የተለየ ጥበብ ተጠቅማችኋል?

በቀለ፡ ነሃስ የሚመረጠው ለዚህ ነው፤ ዓለም ላይ ለልዩ ጉዳዮች ካልሆነ በስተቀር የህዝብ ሐውልቶች ብዙ ጊዜ የሚሰሩት በነሃስ ነው። በነሐስ እንዲሰሩ የሚፈለገው በውስጣቸው ያለው አብዛኛውን የሚይዘው መዳብ ነው፤ መዳብ ደግሞ ኦክስጅን ስለሚይዝ አሮጌ ሲሆኑ የሻገተ አረንጓዴ ይሆናሉ።ልክ መዳብ ያላቸው ሳንቲሞች ሲቆዩ እንደሚፈጥሩት ቀለም ዓይነት።

እናም ኦክስጅን እንዲስብ አድርገን ነው የሰራነው ይህም አካበባቢውን እንዲመስልና በጊዜ ሂደት መልኩ እንዲለወጥ ይፈለጋል…ያ እንዲሆን አድርገን ነው የሰራነው። ጠንካራ ብረትም ስለሆነ አይሰበርም፤ አይሸማቀቅም።

ቢቢሲ፡ ቀመቱና ክብደቱ ምን ያህል ነው?

በቀለ ከነመቆሚያው ወደ ሦስት ሜትር ነው። ይህም የእርሳቸውን ቁመት ሁለት እጥፍ ይሆናል ማለት ነው። ክብደቱ ደግሞ ከ650 እስከ 680 ኪሎግራም ይመዝናል። በትክክል ይታወቃል፤ ነገር ግን ሲበየድ የተጨመሩ የብየዳ ብረቶች ኪሎ ስለሚጨምር ነው 30 ኪሎ ግራም እንደ ገግምት የተቀመጠው።

ቢቢሲ፡ የት ነው የተሰራው?

በቀለ፡ የሸክላ ሞዴሉ አዲስ አበባ የኒቨርሲቲ ሲሆን ቀሪው ሥራ የተከናወነው እንግሊዝ ኤምባሲ አካባቢ በተከራየነው ቤት ነው። ቁርጥራጮቹን ይዘን የመጨረሻውን ሞዴል የሰራነው ግን በእኔ ስቱዲዮ ውስጥ ነው።

ቢቢሲ፡ ሐውልቱ ተቀርፆ ለመጠናቀቅ ምን ያህል ጊዜ ፈጀ?

በቀለ፡ እንደሌሎች አገራት ለጥበብ ሥራዎች የሚሆኑ ግብዓቶች የማግኘት እድሉ ባለመኖሩ ረዘም ያለ ጊዜ ፈጅቶብናል … ስድስት ወር አካባቢ ነው የፈጀው።

ቢቢሲራው ወደ እናንተ የመጣው እንዴት ነበር ?

በቀለ፡ እኔ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ነው የማስተምረው፤ እኔን ቢያነጋግሩኝም በዩኒቨርሲቲው ያሉ ባለሙያዎች በቡድን ነው ስንሰራ ቆየነው። ረዳቶች ነበሩኝ። እንደ ፕሮፌሰር ዘይኑ፣ ተመራቂ ተማሪ የሆነው አቶ ሔኖክ አዘነና ሌሎች በነሃስ ጥበብ ላይ ሙያ ያላቸው ባለሙያዎች ተሳትፈውበታል።

ቢቢሲ፡ ምን ያህል ገንዘብ ወጣበት?

በቀለ፡ ብዙ ነው የፈጀው… እ… እስካሁን አልደመርኩትም ግን ብዙ ገንዘብ ነው የወጣበት። ገንዘብ ብቻ ሳይሆን ተፈላጊውን ውጤት ለማምጣት የሰው ጉልበትም በጣም የበላ ነው።

ቢቢሲ፡ እንደው ገንዘቡን ከእዚህ እስከዚህ ብሎ ማስቀመጥ ይቻላል?

በቀለ፡ ከአንድ ሚሊየን ብር በላይ ነው፤ ለሂደቱ የሚያስፈልጉ ኬሚካሎች አሉ አገር ውስጥ የሌሉ… ቁሳቁሶች አሉ .. በጣም ብዙ ነገሮች አሉ …

ቢቢሲ፡ እንደው በትክክል ባይሆንም ስንት አወጣ ማለት እንችላለን?

በቀለ፡ ከ1.5 ሚሊየን ብር በላይ ነው ለማቴሪያል ብቻ የወጣው።

ቢቢሲ፡ ምን ያህል ነው የተከፈላችሁ?

በቀለ ታክስ ይኖራል… ገና ነው …ሰርተን ያስረከብነውም ሰሞኑን ስለሆነ ቀስ ብለን የምናየው ነው የሚሆነው …ብዙ ገንዘብ አይኖረውም ትንሽ ስለሆነ፤ የሥራውን ጥበባዊም ሆነ የሰው ኃይል ዋጋውን እንደማይመልስ ግን አረጋግጣለሁ።

ቢቢሲ፡ የገጠማችሁ ተግዳሮት ምንድን ነው?

በቀለ፡ ብዙ ነገር የተሳካ ነበር ማለት ይቻላል፤ የግብዓት ጉዳይ ግን እጥረት ሳይሆን ሙሉ በሙሉ ጠፋ ማለት ይቀላል። ከእርሳስ አቅም እራሱ አላሰራ እስኪል ድረስ … ልክ የጋፋት የቴዎድሮስ ሰዎች አፈር አቅልጠው ብረት ሥሩ እንደተባሉት ዓይነት ነገር ነው። ብቻ በጥንታዊው መንገድም ቢሆን ብዙ የሰው ኃይል በመጠቀም ወደሚፈለገው ነገር መጥተናል።

ቢቢሲ የሐውልቱን ወ የሸፈነው ማነው?

በቀለ ኢትዮጵያን ወክሎ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ነው።

ቢቢሲ፡ ሌላ ተባባሪ አካል የለም?

በቀለ፡ እኛ ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ጋር ነው የምንገናኘው

ቢቢሲ፡ ከዚህ በፊት በሌሎች አገራት ከተሰሩት የቀዳማዊ ኃይለ ላሴ ሐውልቶች ይህን ለየት የሚያደርገው ምንድን ነው?

በቀለ፡ በዚህ መጠን ሙሉ ነሃስ ተሰርቶ አያውቅም። የትም አገር፤ የትም ቦታ! የእርሳቸውን መጠን ሁለት እጥፍ ተሰርቶ አያውቅም እሱ ነው ለየት የሚለው።

ቢቢሲ፡ ሐውልቱ መቆሙን ተከትሎ የተቃውሞና የድጋፍ ሀሳቦች እየተንሸራሸሩ ነው፤ ይህንን እንዴት ትመለከተዋለህ?

በቀለ ኖርማል ነው… ጤና ነው ብዬ ነው የማስበው። ሰው አንድ ዓይነት አይደለም። አንድ ዓይነት አለመሆኑም ጥሩ ነው፤ አንዳንዴ የኛ የሚከፋው እ… ነገራችንን ሁሉ የክፋት የክፋት መንገዱን ሁሉ እየነቀስን እየነቀስን.. እዚች አገር አንድም ጥሩ፣ አንድም ደግ፣ አንድም አዋቂ፣ አንድም ፃድቅ እንዳይኖር እስከማድረስ ድረስ እንሄድና ፅንፋዊ ሆነን ራሳችን ማጥፋታችን ነው እንጂ የሚከፋው… እየሱስም ተቃዋሚ ነበረው አይደል ? ተቃዋሚ መኖሩ አይደለም ክፋቱ እኔ ከሌለሁበት ሁሉንም ነገር ይጥፋ የሚል ነገር አለብን፤ እሱ ነው ክፉ ነገር እንጂ የተወሰኑ ሰዎች ቢቃወሙ ጤነኛ ነገር ነው ብዬ አስባለሁ።

በተለይም እርሳቸው ከሄዱ በኋላም ብዙ የሰራናቸው ያጠፋናቸው ነገሮች አሉ። እነርሱን የምንቆጥር ከሆነ እንዳልኖርን ነው የሚቆጠረው፤ ቢያንስም ቢበዛ ደግ ደጉን ስናነሳ ነው እንደ እድሜ የምንቆጥረው ጊዜውን…

ቢቢሲ፡ ሐውልቱ በመቀረፁ እንደ ግለሰብ ምን ተሰማህ?

በቀለ፡ ልጅም ሆኜ ቢሆን አስታውሳቸዋለሁ ከእጃቸው ዳቦና ብር ተቀብያለሁ፤ ብዙ ጊዜ አይቻቸዋለሁ። ታሪካቸውንም እንደማንኛውም ኢትዮጵያዊ አውቃለሁ፤ ትልቅና ኢትዮጵያን ያኮሩ ሰው እንደሆኑ፣ በተለይ ከእርሳቸው በኋላ ኢትዮጵያ ምን እንደሆነች እንደኛ ኖሮ ለሚያውቅ ሰው ቢመለከት ከእርሳቸው ምን እንደታጣ ማመዛዘን ስለሚችል ይህን ሁሉ ስታስቢ እንዴት ደስ ላይል ይችላል?

ቢቢሲ፡ ስለ እርሳቸው ምን ትውስታ አለህ?

በቀለ፡ እንግዲህ ተወልጄ ያደኩት ደብረዘይት ነው፤ አሁንም ከደብረዘይት አልተነጠልኩም፤ ጃንሆይ ደብረ ዘይት በየሳምንቱ ይመጡ ነበር። ለመዝናኛ ይመርጧታል።

ያኔ ከዘጠኝ ዓመት አንበልጥም ያን ጊዜ ሕፃናት ተሰልፈን ስንጠብቃቸው እንግዳ ያዙም አልያዙም ይቆማሉ፤ ቆመው ብርና ዳቦ ይሰጡናል። አርብ አርብ ደብረዘይት ቅዳሜና እሁድን ለማሳለፍ እንዲሁም ለማስቀደስ ይመጣሉ፤ እንጠብቃቸዋለን።

የእጃቸው ስስነት ያ የሚነገርላቸው ግርማ ሞገስ በተለየ ዓይን ነበር የምንመለከታቸው። እቤት ደግሞ ገንዘቡን ስንሰጥ የብዙ ልጆች እናት ገንዘቡ በረከት እንዲኖረው ተብሎ ከእንጀራ ስር ይቀመጣል።

ይህ ሕብረተሰቡ ምን ያህል ለንጉሡ ታማኝ እንደነበረ የሚያሳይ ነው። ዓለምም እንደዚህ ነው የሚያያቸው፤ ምንም ይሁን ምን ብዙ ታሪክ ያላቸው ሰው ናቸው።

Sourceቢቢሲ
Kumneger Media
Kumneger Media
Kumneger Media is a News and Entertainment Website & Channel. Kumneger Media in addition to News and Entertainment it is the hub of Politics, Movies, Drama, Music, Comedy, Documentary and More!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትስስር ይፍጠሩ

325,851FansLike
49,039FollowersFollow
13,194SubscribersSubscribe