ባለ ሁለት መልኩ መሪ

 

ኑርሱልጣን ናዛርባዬቭ – ባለ ሁለት መልኩ መሪ

የካዛኪስታኑ ፕሬዚዳንት ኑርሱልጣን ናዛርባዬቭ ከሃያ ዘጠኝ ዓመት ቆይታ በኋላ ሰሞኑን በድንገት ስልጣን መልቀቃቸው ተሰምቷል፡፡ የ78 ዓመቱ ሰው ከስልጣን ለመነሳት ከወሰኑባቸው ምክንያቶች አንዱ ‹ሀገሬ የሚመራትን አዲስ ትውልድ ትፈልጋለች› የሚል ነው፡፡ የሶቪየት ዘመን የመጨረሻ ዘመን መሪ ተብለው የሚታወቁት ናዛርባዬቭ እ.ኤ.አ እስከ 2020 ሚያዝያ ወር ይቆይ የነበረ የፕሬዚዳንትነት ዘመናቸውን ለታማኝ የፓርቲያቸው አባላት ማስረከባቸውን አስታውቀው በጸጥታ አመራርና በፓርቲ ከፍተኛ ስፍራዎች ቁልፍ መሪነት እንደሚቀጥሉ ተናግረዋል፡፡ ፕሬዚዳንቱ ለሀገራቸው ዜጎች በቴሌቪዥን በተላለፈ መልእክታቸው ‹‹ነፃዋን የካዛክ ግዛት መሥራች እንደመሆኔ ከዚህ በኋላ የኔ ሥራ የሚሆነው ሀገሪቱ የምትመራባቸውን ለውጦች የሚያስቀጥሉ አዳዲስ የመሪ ትውልዶችን ማፍራት ነው›› ብለዋል፡፡

የላዕላዩ ምክር ቤት አፈ ጉባዔ የሆኑት ካሲም ጆማርት ቶካዬቭ ፕሬዚዳንቱን ተክተው እስከ መጪው ምርጫ ድረስ ሀገሪቱን እንደሚያገለግሉ ታውቋል፡፡ የ65 ዓመቱ ቶካዬቭ ከዚህ ቀደም የካዛኪስታን የውጪ ጉዳይ ሚኒስትር እና ጠቅላይ ሚኒስትር የነበሩ ሲሆን የካዛክ፣ ሩሲያን፣ እንግሊዘኛና ቻይንኛ ቋንቋዎችን አቀላጥፈው ይናገራሉ፡፡

በአንድ ወቅት የብረታ ብረት ሠራተኛ የነበሩት ናዛርባዬቭ በፕሬዚዳንትነት ዘመናቸው የውጪ ኩባንያዎችን በመሳብ የሀገሪቱን የነዳጅ ምርት ከሦስት እጥፍ በላይ ማሳደግ የቻሉ ሰው ናቸው፡፡ የቀድሞው የኮሙኒስት ፓርቲ መሪ 18 ሚሊየን ዜጎች ያሏትን ሀገር ከሞስኮው ቅኝ ግዛት እ.ኤ.አ በ1991 ነፃ ያወጡ መሆኑም ይነገርላቸዋል፡፡ የረጅም ጊዜ የሥልጣን ቆይታቸውም ይህ ነው የሚባል ተፎካካሪ የነበረው አይደለም፡፡ እ.ኤ.አ በ2015 በተካሔደው ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ 97.7 በመቶ ድምጽ አግኝተው የሥልጣን ዘመናቸውን ያስረዘሙበት ምክንያትም ይህ ነበር፡፡

የቀድሞዋ ሶቪየት ሕብረት ለአሥራ አምስት ቦታዎች ስትከፋፈል ካዛኪስታንን ይዘው በመጀመርያ ፕሬዚዳንትነት መምራት የጀመሩት ናዛርባዬቭ በሀገራቸው ሰሜናዊ አቅጣጫ ከምትገኘው የሩሲያ ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን ጋር ሲነጻጸሩ በዓለማቀፍ ደረጃ ያላቸው ዕውቅና እጅግ ዝቅተኛ ይሁን እንጂ ለሀገራቸው ባበረከቱት አስተዋጽኦ ግን ከእርሳቸው የሚበልጥ ታሪክ ያላቸው መሆኑን የአልጀዚራ ኢንግሊሹ ናታን ሆጅ ያስረዳል፡፡

የሥልጣን ዓመታት

የቀድሞዋ ሶቪየት ሕብረት ትልቁ የመካከለኛ ኤዥያ ሪፐብሊክ አካል የሆነውን ኮሙኒስት ፓርቲ ተቀላቅለው ተቀዳሚ ጸሐፊ በመሆን ከፖለቲካው ጋር የተዋወቁት ናዛርባዬቭ ከፍተኛ የነዳጅና ማዕድናት ሀብት ያላትን ሀገር በነፃነት መምራት ከጀመሩ በኋላ በዋሽንግተን የሚገኙ የዓለማቀፍ ኃይል አምራች ኩባንያዎችና ፖሊሲ ቀራጮችን ቀልብ መግዛት ያዙ፡፡ ከሶቪየት ሕብረት መውደቅ በኋላ አዲስ የተመሠረተችው ሀገር በድንበሮቿ ስር ከአንድ ሺህ በላይ ስትራቴጂያዊ የኒውክሌር አረሮች ያሏት መሆኑ እንዲሁም ሶቪየቶች የመጀመርያውን አቶሚክ ቦንብ የሞከሩበት ሴሚፓላቲንስክ የተባለ የኒውክሌር መሞከሪያ ስፍራ የሚገኝባት መሆኑ ጂኦግራፊያዊ ዋጋዋ ከፍተኛ መሆኑን ያሳያል፡፡

ፕሬዚዳንቱ በሀገራቸው የሚገኙትን የኒውክሌር አረሮች ለሩሲያ አሳልፈው ከሰጡ በኋላ ‹የሠላም ማዕከል› በተሠኘ መጽሐፋቸው ላይ ሀገራቸውን ከኒውክሌር መሳርያ የጸዳች ሲሉ ሰይመዋታል፡፡ ከጎረቤት ሀገራት መሪዎች ጋር እራሳቸውን በማነጻጸርም ብሩህ አስተሳሰብ ያላቸው የቀድሞዋ ሶቪየት ዘመን መሪ አድርገው ይቆጥራሉ፡፡ ሳፓርሙራት ኒያዙቭ የተባሉት የቱርክሜንስታን መሪ ተሽከርካሪ የወርቅ ምስላቸውን ማሠራትና የሳምንቱን ቀናት ስያሜ መቀየርን ጨምሮ የተለያዩ አስገራሚ ነገሮች አድርጓል፡፡ ኢስላም ካሪሞቭ የተባሉት የኡዝቤኪስታኑ መሪም የፖለቲካ ተቀናቃኞቹን በማሠርና በጭካኔ በማስገረፍ ይታወቃል፡፡ ከእነኚህ መሪዎች ጋር ራሳቸውን በማነፃፀር ዘመናዊ ነኝ ይበሉ እንጂ ፈላጭ ቆራጭነታቸው በሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች ዘንድ ከፍተኛ ትችት ይደርስባቸዋል፡፡ የአሜሪካ የውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር እ.ኤ.አ በ2015 በካዛኪስታን የተካሔደውን ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ናዛርባዬቭ በ98 በመቶ ድምጽ ማሸነፋቸውን ተከትሎ ምርጫው ‹ተገቢ አካሔድ ያልነበረውና ትክክለኛ ፖለቲካዊ ፉክክር ያልነበረበት ነው› ሲል አጣጥሎታል፡፡

የሕዝቡ መሪ

ናዛርባዬቭ ከፕሬዚዳንትነት በፈቃዳቸው ይነሱ እንጂ ከሀገሪቱ ፖለቲካ ፈፅሞ የሚርቁ አይመስሉም፡፡ እንዲያውም ‹ኤልባሲ› ወይም የሕዝቡ መሪ የሚል ስም ተሰጥቷቸው የሀገሪቱ የደህንነት ምክር ቤት ሰብሳቢ ሆነው ቀሪ ዕድሜያቸውን የሚገፉ ይሆናል፡፡ በእርግጥ ሀገሪቱም በከፍተኛ የዕድገት ለውጥ ውስጥ እያለፈች ነው፡፡ ወደፊት በቻይናና በአውሮፓውያን መካከል ለሚካሔድ ንግድ መተላለፊያ የምትሆን ስትራቴጂካዊ ሀገር መሆኗም ነው የሚነገረው፡፡ እርሳቸውም ከአደባባዩ ገለል አሉ እንጂ የሀገሪቱን የደህንነት ምክር ቤት በኃላፊነት መያዛቸው ሀገሪቱ የምታደርጋቸውን የውጪ ግንኙነቶችና የደህንነት ፖሊሲዎች ላይ ከፍተኛ ሚና በመጫወት ከኋላ ሆነው ለመተወን መዘጋጀታቸውን ነው የፖለቲካ ተንታኞች የሚያስረዱት፡፡ ‹‹ከእናንተ ጋር እቆያለሁ፤ ሀገሪቱንና ሕዝቦቿን መንከባከብ ሥራዬ ይሆናል›› ሲሉ መናገራቸውም ይህንኑ የሚያመለክት ነው፡፡

በሀገሪቱ ሰላምና መረጋጋትን በማስፈን በኩል ጥሩ ስም ማትረፍ ቢችሉም ተቃዋሚዎቻቸውን በመጨቆን በኩልም ስማቸው ይነሳል፡፡

ካዛኪስታን ማን ናት?

አሥራ ስምንት ሚሊየን ሕዝብ ብቻ የሚኖርባት ካዛኪስታን በቆዳ ስፋቷ ከዓለም ዘጠነኛ ደረጃን መያዟ አስገራሚ ነው፡፡ አንድ ሚሊየን ስኩዌር ማይል የሚሸፍነው መሬቷ በሰሜን ከሩሲያና በምሥራቅ ከቻይና ጋር ሲያዋስናት በስትራቴጂና በኢኮኖሚ ረገድ ትልቅ ጥቅም እንዲኖራት ያደረገው ደግሞ የነዳጅ ሀብት ያላት መሆኑ ነው፡፡ በዓለም ላይ ስሟ ብዙም የማይነሳው ሀገር ‹አሸናፊዎች ሁሉንም ይወስዳሉ› በሚለው ሕግ በሚያምኑ መሪዎች መተዳደሯ ፖለቲካዋ ተዳፍኖ በኢኮኖሚዋ ብቻ ስሟ እንዲጠራ ግድ የሚያስብል ነው፡፡

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትስስር ይፍጠሩ

325,851FansLike
49,039FollowersFollow
13,194SubscribersSubscribe