ቦሪስ ጆንሰን – ተረኛው የ‹‹ብሬግዚት›› ተፈታኝ

የትውልድ ስማቸው አሌክሳንደር ቦሪስ ዴ ፌፌል ጆንሰን ይባላል፡፡ እ.ኤ.አ ሰኔ 19 ቀን 1964 በዩናይትድ ስቴትሷ የኒውዮርክ ግዛት ውስጥ የምትገኝ ኒው ዮርክ ሲቲ የተባለች ከተማ ውስጥ ተወለዱ፡፡ ትውልደ አሜሪካዊው እንግሊዛዊ በሙያቸው ጋዜጠኛ የነበሩ ሲኾን በአሁኑ ወቅት የወግ አጥባቂ ፓርቲ ፖለቲከኛ ናቸው፡፡ ከጥቂት ወራት በፊት ሥራቸውን በገዛ ፈቃዳቸው የለቀቁትን የቀድሞዋን ጠቅላይ ሚኒስትር ቴሬዛ ሜይ በመተካት የዩናይትድ ኪንግደም ጠቅላይ ሚኒስትር ኾነው ተመርጠዋል፡፡ እ.ኤ.አ ከ2008 እስከ 2016 ድረስ የለንደን ከንቲባ በመኾን ያገለገሉት ቦሪስ ጆንሰን በሀገሪቱ የውጪ ጉዳይ ሚኒስትርነት ከ2016 እስከ 2018 ማገልገላቸው አይዘነጋም፡፡
የኋላ ታሪክ
በልጅነታቸው እንግሊዝ ውስጥ ወደሚገኝ አዳሪ ትምህርት ቤት ከመግባታቸው አስቀድሞ በአሜሪካዋ ኒውዮርክ ሲቲ እና በብራሰልስ ኖረዋል፡፡ በኤተን እና ባሊዮል ኮሌጆች ውስጥ ትምህርታቸውን ከተከታተሉ በኋላም ለጥቂት ጊዜያት የሥራ አመራር አማካሪ በመኾን ካገለገሉ በኋላ ወደ ጋዜጠኝነቱ ዓለም ገብተው የድርሻቸውን ለመወጣት ጥረት ማድረግ ጀመሩ፡፡ እ.ኤ.አ በ1987 ዘ ታይምስ በተባለው መጽሔት ላይ ዘጋቢ ሆነው ሲሰሩ የቆዩ ሲኾነን በሠሩት ሙያዊ ስህተት ከተቋሙ ተባርረዋል፡፡ ከዚያም ወደ ዘ – ዴይሊ ቴሌግራፍ ፊታቸውን መልሰው የአውሮፓ ማኅበረሰብ – ነክ ዜናዎችን እየዘገቡ ቆዩ፡፡ ከ1994 እስከ 1999 በነበሩት ጊዜያት ደግሞ በተባባሪ አርታኢነት ይሠሩ ጀመር፡፡ በ1994 ዘ ስፔክታተር በተባለ መጽሔት ላይ የፖለቲካ ጉዳዮች አምድ አዘጋጅ በመኾን ሲያገለግሉ ቆይተው በ1999 የመጽሔቱ አርታኢ በመኾን እስከ 2005 (እ.ኤ.አ) ድረስ አገልግለዋል፡፡
ጉዞ ወደ ፓርላማ
እ.ኤ.አ በ1997 የወግ አጥባቂው ፓርቲያቸውን በመወከል ለታችኛው ምክር ቤት አባልነት ተወዳዳሪ የነበሩ ቢኾንም በሌበር ፓርቲ ተወካዩ ማርቲን ጆንስ ተሸንፈው ሳይሳካላቸው ቀርቷል፡፡ ከዚያም ትኩረታቸውን ወደ ጋዜጠኝነቱ በማድረግ ‹ሀቭ አይ ጎት ኒውስ ፎር ዩ?› የተሰኘ የቴሌቪዥን ቶክ ሾው በቢቢሲ ቴሌቪዥን ጣቢያ ማቅረብ ጀመሩ፡፡ በድፍረት የተሞላ አዋራጅ አቀራረባቸው፤ ከሚሰጧቸው እዚህ ግቡ የማይባሉ አስተያየቶች ጋር ተደማምረው ሰውየውን በተመልካቾች ዓይን ስር አስገቧቸው፡፡ ከዚህ ዕውቅና በኋላ በድጋሚ በ2001 እ.ኤ.አ ወደ ፓርላማ ለመግባት ያደረጉት ውድድር በስኬት የተቋጨ ነበር፡፡ ሰውየው ለየት ባለ የቴሌቪዥን ሾው አቀራረብ የማረኳቸውን እንግሊዛውያን በፖለቲካ ጉዟቸውም ቀልባቸውን መቆጣጠር ችለዋል፡፡ ይሁን እንጂ ከተለያዩ ቅሌቶች ያመለጡ አልነበሩም፡፡ ከእነኚህ መካከል ስፔክታተር በተሰኘ መጽሔት ላይ ለሠፈረ ስሜታዊ ዘገባ የሊቨርፑል ከተማ ነዋሪዎችን ይቅርታ የጠየቁበት አጋጣሚ ተጠቃሽ ነው፡፡ እ.ኤ.አ በ2004 እንዲሁ ከአንድ ጋዜጠኛ ጋር ጀምረውታል በተባለ ያልተገባ የፍቅር ግንኙነት ምክንያት ከሚኒስትርነት ማዕረጋቸው እንዲነሱ ተደርጓል፡፡ ይሁን እንጂ በዚህ ቅሬታ ውስጥም ቢኾን እ.ኤ.አ በ2005 ለፓርላማ አባልነት በድጋሚ መመረጣቸው አልቀረም፡፡
የለንደን ከንቲባ
እ.ኤ.አ ሐምሌ 2007 ኬን ሊቪንግስተን ከተባሉት የሌበር ፓርቲ ተፎካካሪያቸው ጋር በቀረቡበት የለንደን ከተማ ከንቲባነት ውድድር ሳይሳካላቸው ቢቀርም በወቅቱ በጠቅላይ ሚኒስትር ጎርደን ብራውን ይመራ የነበረውን የሌበር ፓርቲ መንግሥት እንደማይቀበሉ የሚነገርላቸው ቦሪስ ጆንሰን በ2008 አሸንፈው የልባቸውን ምኞት ማሳካት ችለዋል፡፡ እ.ኤ.አ በ2012 በለንደን ከንቲባነት በድጋሚ መመረጣቸው በብዙዎች ዘንድ እጅግ አስገራሚ ነበር፡፡ ምክንያቱም ፓርቲያቸው ‹ኮንሰርቫቲቭ› ፓርቲ በእንግሊዝ፣ በስኮትላንድ እና በዌልስ ከ800 በላይ መቀመጫዎቹን ያጣበት ወቅት ነበር፡፡
ከፖለቲካ እንቅስቃሴዎቻቸው ጎን ለጎን በድርሰቱም ጠንካራ የኾኑት ቦሪስ ጆንሰን ‹ሌንድ ሚ ዩር ኢርስ› የሚል የወጎች ስብስብ መጽሐፍ በ2003፣ ‹ሰቨንቲ ቱ ቨርጅንስ› የተሰኘ ልብወለድ በ2004 እንዲሁም ‹የሮም ሕልም› የተሰኘ በሮማን ኢምፓየር ላይ በተደረገ ጥናት የተዘጋጀ መጽሐፍ በ2006 ለንባብ አብቅተዋል፡፡ እ.ኤ.አ በ2014 ያወጡት ‹ዘ ቸርችል ፋክተር፤ ሀው ዋን ማን ሜድ ሒስትሪ› የተሰኘው በቀድሞው የሀገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ዊንስተን ቸርችል ላይ ትኩረት ያደረገ መጽሐፍም የሰውየውን የደራሲነት ገጽታ በጉልህ ማሳየት የሚያስችል ነው፡፡
ብሬግዚት
እ.ኤ.አ በ2015 ወደ ፓርላማ አባልነት ሲመለሱ የሰውየው ቀጣይ ትኩረት የወቅቱን ጠቅላይ ሚኒስትር ዴቪድ ካሜሮን በማሸነፍ ጠቅላይ ሚኒስትር የመኾን ሐሳብ እንዳላቸው መወራት ጀምሮ ነበር፡፡ እርሳቸው ግን እ.ኤ.አ ሰኔ 23 ቀን 2016 ለተካሔደው ሕዝበ – ውሳኔ ‹‹ብሪታኒያ ከአውሮፓ ሕብረት መውጣት አለባት›› የሚለውን ሐሳብ በመምራት ብሪታንያ በአውሮፓ ሕረት አባልነቷ መቀጠል አለባት የሚለውን ሐሳብ ከሚያራምዱት ጠቅላይ ሚኒስትር ዴቪድ ካሜሮን ጋር መገዳደር ያዙ፡፡ የሕዝበ ውሳኔው ቁርጥ ሲታወቅና ከሃምሳ ሁለት በመቶ በላይ ብሪታንያውያን ሀገራቸው ከአውሮፓ ሕብረት አባልነት መውጣቷን መምረጣቸው ሲረጋገጥ ጠቅላይ ሚኒስትር ዴቪድ ካሜሩን በፈቃደኝነት ስልጣን እንደሚለቁ አስታወቁ፡፡ በዚህ ወቅት የብዙዎች የቀደመ ግምት የአደባባይ ምሥጢር ኾኖ የሀገሪቱ ቀጣይ ጠቅላይ ሚኒስትር ቦሪስ ጆንሰን እንደሚኾኑ በሰፊው መነገር ጀመረ፡፡
ይሁን እንጂ ጆንሰን ማይክል ጎቭ በተባሉ የ‹‹ብሪታንያ ከአውሮፓ ሕብረት ትውጣ›› አቀንቃኝ ወዳጃቸው ክህደት ተፈጸመባቸው፡፡ ማይክል ጎቭ የብሪታንያን ከአውሮፓ ሕብረት መውጣት ዘመቻ ለመምራት ጆንሰን ብቁ ባለመኾናቸው አልመርጣቸውም፤ ከዚያ ይልቅ ራሴን ለውድድሩ ዝግጁ አደርጋለሁ አሉ፡፡ በዚህ ምክንያት የጆንሰን ደጋፊዎች ድጋፋቸውን ወደ ማይክል ጎቭ ስላዞሩ ጆንሰን ራሳቸውን ከጠቅላይ ሚኒስትርነት ውድድር ውጪ አደረጉ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ቦሪስ ጆንሰን
የኮንሰርቫቲቭ ፓርቲዋ ቴሬዛ ሜይ የብሪታንያ ጠቅላይ ሚኒስትር መኾናቸው ሲረጋገጥ ቦሪስ ጆንሰንን የውጪ ጉዳይ ሚኒስትር አድርገው መረጧቸው፡፡ ይሁን እንጂ ‹‹ብሬግዚት›› የሚባለውንና ብሪታንያ ከአውሮፓ ሕብረት አባልነት የምትወጣበት ዘመቻ ጽኑ ደጋፊ የኾኑት ቦሪስ ጆንሰን ዘመቻውን በበላይነት ሲመሩ የነበሩት ዴቪድ ዴቪስ በፈቃዳቸውን ስልጣን መልቀቃቸውን ተከትሎ ኃላፊነቱን ለመያዝ የ‹‹ብሬግዚት›› ጉዳይ አያያዙ ካላማራቸው የቴሬዛ ሜይ መንግሥት የውጪ ጉዳይ ሚኒስትርነት በፈቃዳቸው ለቀቁ፡፡
ብሪታኒያን ከአውሮፓ ሕብረት አባልነት ለማስወጣት ለሁለት ያዘጋጇቸው ዕቅዶች ለሁለት ያህል ጊዜያት የከሸፉባቸው ጠቅላይ ሚኒስትር ቴሬዛ ሜይ ስልጣናቸውን በገዛ ፈቃቸው መልቀቃቸውን ተከትሎ እርሳቸውን ለመተካት ከተወዳደሩት አሥር እጩዎች መካከል አንዱ ነበሩ ቦሪስ ጆንሰን፡፡ ከወሳኝ ትግል በኋላም ሐምሌ 24 ቀን 2019 ላይ የዩናይትድ ኪንግደም ጠቅላይ ሚኒስትር በመኾን ተመርጠው ሀገሪቱን ማስተዳደር ከጀመሩ ወራት ተቆጥረዋል፡፡ ጋዜጠኛውና የተለየ ስብዕና ባለቤቱ ቦሪስ ጆንሰን ከዚህ ቀደም የሀገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትሮች ያላሳኳቸውን ከአውሮፓ ሕብረት አባልነት ነፃ የኾነች፣ የኢኮኖሚ አቅሟ የዳበረና የዓለም ፖለቲካ ውስጥ ከዚህ በላይ ፈርጣማ የኾነ ክንድ ያላት ብሪታንያን መፍጠር ይጠበቅባቸዋል፡፡ ይሳካላቸው ይኾን? ወደፊት የምናየው ይኾናል፡፡

Kumneger Media
Kumneger Media
Kumneger Media is a News and Entertainment Website & Channel. Kumneger Media in addition to News and Entertainment it is the hub of Politics, Movies, Drama, Music, Comedy, Documentary and More!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትስስር ይፍጠሩ

325,851FansLike
49,039FollowersFollow
13,194SubscribersSubscribe