ተከራዩ (አጭር ልቦለድ) 

/በትንሳኤ ካሳሁን/

ብዙ ተከራዮች አሉ። ብዙዎቹ ወንዶች ትንሽነቴን የሚዘነጉ ወይም ሆን ብለው የረሱ የሚመስሉ ናቸው።ሴቶቹም ቢሆኑ መፈለጌን እንደ ትልቅ ነገር እያደናነቁ የሚያሽካኩ … አስቀያሚ ገጣጣነታቸውን እና ያለመፈለግ ንዴታቸውን የሚሸሽጉበት መንገዳቸው ይመስለኛል። ልጅነቴን ትተው…… ቢችሉ አሳምነው…… ካልቻሉ ደሞ አስገድደው ቢያስደፍሩኝ ግድ የላቸውም። ሁሉም ተከራይ ቤተሰብ ሆኖ እንዲኖር ይፈቀድለታል።ሚስጥር መደበቅ አይታሰብም።(ይህ ታዲያ እኛ ቤት ነው።)

እና የሱን ነገር ከሌላው ተከራይ ምን ይለየዋል? በራችን ቅርብ ስለሆነ? መስኮት ስር ቁጭ ብሎ የሚደረገውን ሁሉ ማየት እና ደካማ አይናፋርነቴ ውስጥ ገብቶ ሊያጠቃኝ መሞከሩ ነው?

የሚመጡልኝ ደብዳቤዎች ብዛትና ከእናቴ መሸሸግ አለመቻሌ ያበሳጨኛል።የሁሉንም ነገር መነሻ እንዴት አነፍንፋ እንደምትደርስበት አላውቅም። መዋሸት አልችልም።” የሴት መላ” ይባላል ቆይ እኔ ሴት አይደለሁም። ካደኩ በኋላ ነው እንደሴት ሊሰማኝ የሚገባው?

ካደኩ በኋላ መተኛቴን እያሰብኩ እንዳልከፋ…. መተኛቴን እንደ ተሸናፊነት በመቁጠር…. (አንዴ የተኛኝ ወንድ ድጋሚ ዞር ብሎ ባያየኝስ ሀፍረቱን እሸከመዋለሁ ወይ?) የፈለኩትን ወንድ መልሶ ለማግኘት ስለማፍር እየፈለኩ እያማረኝ….. ትኩስ እሳት የወጣትነት ፍላጎቴ ገንፍሎ ቢወጣም ምንም የማላደርግበት ብዙ ጊዜ ነበረኝ። አንዳንዴማ የስጋ ፈቃዴ ገንፍሎ ይወጣና የገዛ ንጭንጬን እና ብስጭቴን መቋቋም ያቅተኛል። የምበሳጭበት ምክንያት ባይኖረኝም በውሃ ቀጠነ ትዕግሥት ማጣቴ ሰማይ ይነካል።

የሴትነት ወግ….. አንገቷን የደፋች ሰው ቀና ብላ የማታይ ….. የማትቀመስ….. ክብሯን የጠበቀች በሚባልበት ማህበረሰብ ውስጥ አደኩ። ውስጤ ግን እንደ መብረቅ ሊፈነዳ የደረሰ እብደት…. መነጠል እና ማፈንገጥ እንዳለ አውቃለሁ። እናቴም ብትሆን የዚህን እብደት ጥልቀት ስለተረዳች በየአንዳንዱ እንቅስቃሴና ድርጊቶቼ መሃል በጥብቅ ክትትል ታደርግብኛለች። ለአፍታ ዘንግታኝ እንደማታውቅ ሲገባኝ በንዴት ተንገበገብኩ። ገና ለጋ ነኝ። ያኔ ወንድ ምን እንደሚመስል አላውቅም።………. ወንድነትን ከተረዳሁት እንዳውቅ ያደረገችኝ እሷው ናት። በመከልከል መሃል በጥበቃዋ ውስጥ። እግዜር አዳምን በለስ እንዳይበላ ከከለከለው በኋላ ስንት ጊዜ ደጋግሞ አስጠነቀቀው? በመከልከሉ ውስጥ እያስታወሰው ነበርን? ሲከለከል ምን ተሰማው? በብስጭት ነደደ ወይስ በትህትና ተቀበለ? ትህትናውን ምን ሻረው?
የእናቴ የቁጥጥር ብዛት……. እኔን…. ወደ ተከለከለው አሰመጠኝ…. ይበልጥ ገፋኝ።

ለመጀመሪያ ጊዜ ፍቅር እንዲይዘኝ ስታደርገኝ ቀናት ብቻ ነበሩ…..ያን ስሜት በግድ ወደውስጤ እንዲቀጣጠል እሳቱን የለኮሰችው እሷው ናት።
” አያሳዝንም?….. አየሽው?…… አያምርም? …… ስወደው……. እንደልጄ ነው የማየው”….. የመሳሰለ ቀስ እያለ….. ወደ ውስጥ አንጀቴ እየተሳበ…. እየቀለጠ የሚፈስ የቃላት ማርና ወተቷን…. እንደ ልጅ በስስት የምጠጣ እኔ። መመልከት ማስተዋል እንደጀመርኩ የከንፈሩን ውበት ከወተት የሚነጣ የጥርሱን ውበት አስተዋልኩ። ቆንጆ ነበር እንዴ? አንገቱ ሲያምር…….! እያልኩ የአዳም ፈርጡን እንቅስቃሴ መቁጠር ጀመርኩ። ቅላቱ የገላው ጥራት ቅጥነቱ አረማመዱ…. እንደ ልጅ የነበረው ቡረቃ ሁሉ ልዩ ሆኖ ታየኝ። የሚገርመኝ እኔ እንኳን በሚጢጢ ነፍሴ በሚጢጢ ስጋዬ ውስጥ የሱን ያክል ደስታና ሳቅ አልነበረም። ከትምህርት ቤት ወደ ቤት ሲገባ ዩኒፎርሙን ያወልቅና የምታምረዋን ቲሸርት ይለብሳል።
ደሞ ከቤት ወደ መስኮቱ ስመለከት እሱም በመስኮት ወደ እኔ ይመለከታል። ፈገግ ሲልልኝ ሆዴ ውስጥ የሚፈስ የማላውቀው ትኩስ ጣዕም አለ። እቀልጣለሁ በፈገግታየ መሃል ግራ የተጋባ እኔነቴን ለመሸሸግ እየጣርኩ እሱን ለማየት ያለስራ ከቤት ወደ ቤት…..
ግቢ ውስጥ ስመላለስ እውላለሁ።
ትምህርት ቤት ከሄድኩም ወደ ቤት እስክመለስ ድረስ የምቸኩለው መቸኮል መግለጫ የለውም። እሱ ትምህርት ቤት ሆኖ እኔ ቤት ከሆንኩ እስኪመጣ ደጁን ሳይ እውላለሁ።
መላፋት አልወድም ወንድሜና እህቴ ሲላፉ ሳይ ራሱ ደሜ ይፈላል። አትንኩኝ ባይነቴን ስለሚያውቁ እና ስለሚበሳጩብኝ ሰበብ እየፈለጉ ያስጮሁኛል።

አንድ ቀን ውሃ ለመቅዳት ስወጣ እንደለመደው ተከትሎኝ መጣ። ልቤ በሀይል ይደልቃል። ቧንቧዋን ለመክፈት ዝቅ ስል አብሮኝ ዝቅ ይላል። በጣም ከተጠጋጋን በኋላ እንተያያለን። ለምን እንደሆነ አላውቅም ትንፋሹ በአፌ ውስጥ ይገባል። ደሞ ትንፋሹ ከወተት የተቀዳ ከወተት የሚጣፍጥ ጣዕም አለው። ደሞ ወደውስጤ እየተሳበ ሲመጣ በደስታ አፌን እከፍትለታለሁ። ትንፋሽ የሚርብ ነገር ነው እንዴ? “ቅደሚ ቅደም” እየተባባልን እየተገባበዝን በመሃላችን ምንም የሌለ እንዲመስል ስንጣጣር ሁሉ… እናቴ በሩቅ ምንም እንደማያውቅ ትከታተላለች።

ሌላ ቀን ደሞ ውሃ እየቀዳሁ ከትምህርት ቤት ሲመጣ ሰላምታ ካለኝ በኋላ እናቴን ጠየቀኝ። ቤት አልነበረችም። ግቢው በትንሹ ፀጥታ ሰፍኖበታል። ደስ የሚል ከስዓት ነበር። ውሃ እየቀዳሁ የሚቅለሰለስ ትልልቅ አይኔን አፍጥጨ ስጠብቅ ወደኔ የውሃ ጆኩን ይዞ መጣ። በዝምታ ከኔ አቋርጦ ውሃ በጆኩ እየቀዳ ብሎ ያየኛል። ከውሃ ቧንቧው ላይ ዝቅ ብያለሁ…. ትንንሽ ለጋ ጡቶቼን እያየ ውሃው እስኪሞላ ጠበቀ። ቀና ሲል በተመስጦ እያየሁት ቆምኩ። አይኑን ከአይኔ ላይ አልነቀለም። በእጁ የያዘውን ውሃ ቀጥታ በአንገቴ ላይ ወደ ጡቶቼ ለቀቀው። ማመን አቅቶኛል። ደንዝዤ በውሃው ቅዝቃዜና ባልጠበኩት የመደፈር ስሜት ተውጬ ውሃውን ገላዬ ላይ እስኪጨርሰው ጠበኩት።
እየሳቀ ጥሎኝ ሲሮጥ ከቀዳሁት ውሃ ላይ እየቀነስኩ እሱን ለመርጨት ስጣጣር ጭራሽ እንደ አዲስ እየቀዳ ከፀጉሬ ጀምሮ ሲያፈስብኝ….. እኔ እሱን ለመርጨት የምቀዳውን ውሃ እያስደፋኝ….. ከፀጉሬ እስከ እግሬ ድረስ……. በዝናብ የበሰበሰ አስመሰለኝ። በእልህ ስሔድ ትንሽዬ ገላዬን ጥምጥም አድርጎ ይይዘኝና…… ለመላቀቅ ስጥር….. በእቅፉ ውስጥ እንድቆይ…… አንዴ ከፊት ለፊት……. አንዴ ከኋላዬ እንቅ አድርጎ ይይዘኛል። በመሃል የልቤ ምት ከደረቴ ፈንቅሎ ሊወጣ ሲደረስ ራሱ አለቀቀኝም። ጭራሽ በመተሻሸት ብዛት ሰውነቴ ጋለ አልፎ አልፎ ቀላ። ከብዙ ልፊያ በኋላ ቤቱ ገብቶ ከውስጥ ዘጋው። መስኮቱን ከፍቶ ገላዬ ላይ የተጣበቀ ልብሴ ያጋለጠውን የሰውነቴን ቅርፅ……. በውሃ የራሰና የተተራመሰ አንገቴን አልፎ የተጠቀለለ ፀጉሬ….. የፈጠረብኝን መልክ በንዴት ከቀላ ፊቴ ጋር እያዬ ይስቃል።
በዚህ የመነካትና የመደፈር ስሜት….. ጥልቅ ፍርሀትና መጠን አልባ ፍቅር ወደ ውስጤ ተለቀቀ። እንደተጣበኩ የተሰማኝ ስፈራ ነበር። ፈራሁ። ፍርሃት ወረረኝ የሚባለው እንዲ ሲሆን ነበር? እንዳፈቀርኩት ያወቀብኝ እና የቀለደብኝ መሰለኝ። የተጠላሁ የተናኩ እንደሆንኩ ጠረጠርኩ። መጠርጠር ለካ ህመም ነው። በለጋነት ብዙ የአዋቂዎች ነገር እያወኩ እንደሆነ ተሰማኝ። መጠበቅ…. መጠርጠር….. መፍራት….. መሸሽ….. መቅረብ…… መመኘት…… የመሳሰለ ጠጣር ነገር። የተቀመመ ውስጡን ያላየሁት….. ጥልቀቱ የማይታወቅ ባህር ውስጥ የሰመጥኩ ዋናተኛ ሆኘ።
እናቴ ስትመጣ በር ከፍቶ በቀስታ ከቤቱ ወጣ። ያንን ፍልቅልቅነት ሳይሸፋፍን ከኔ ውሃ ለማምለጥ በእናቴ ጀርባ ይሸሸጋል? እየሳቀ ” እማማ እማማ ” ይላል እንዳላበሰብሰው ቀድሞ መከላከሉ ነው። አናቴም በቁጣ የያዝኩትን ካስጣለችኝ በኋላ ” ምን አደረገሽ? ” ብላ ጠየቀችኝ አፀፋውን ስላልመለስኩ እና ለሁለት ስለተባበሩብኝ በእልህ ነፍሴን ስቻለሁ ” ቅድም እንዴት እንዳበሰበሰኝ እኮ ፀጉሬ ራሱ መች ተረፈ “አልኩ ድምጼ እየተንቀጠቀጠ። ‘ደሞ አንች ለሱ ማገዝሽ ይባስ አቃጥሎኛል ‘ የምትል ቀጭን ቁጣ ያላት አነጋገር ነበረች። እየሳቀች ነገሩን አረሳሳችኝ።

ሌላ ቀን በሃሳብ ሰምጬ ሽሮ የሚዘጋጅበት እህል በረንዳ ላይ ቁጭ ብዬ እለቅማለሁ። ጊዜው መርዘሙን አስተዋልኩ። ሰልችቶኛል። ያለ ማቋረጥ እተነፍሳለሁ። በዝምታ ቁጭ ብለናል። የተቀመጥነው የሱ በር ፊት ለፊት ነው። ቦታው ይመቻል ከፀሀይ ተከልለን ትልልቆቹ ዛፎች ስር ነው የተቀመጥነው። ሁሌም እንዲ ነበር የምናደርገው።
‘ምነው አልመጣ አለ? ኡፍፍፍፍፍፍፍ ‘ ሰዓቱ ተንገላጀጀብኝ ‘ ለአፍታ ወደ በሩ ስመለከት ገና አይኔን ሳልመልስ ” ዛሬ ደሞ ዘገዬ አይደል? ምን ነክቶት ይሆን ልጄን? ” አለችኝ ፈገግ ብላ በትኩረት ስሜቴን መደበቅ የማይችል አሳባቂ ፊቴን እያጠናች።
አፈርኩ በተመሳሳይ ሰዓት ፈራሁ በዚሁ ቅፅበት ናፈቀኝ ወዲያም ተበሳጨሁ። ለምን ተበሳጨሁ? ስሜቱን አላውቅም….. ፍቅር ከኔ ብቻ ያለ መሰለኝ…… ትንሽዬ ቦታዬ ተለጥጣ ሀገር የማከሏ እና የልቤን ነግሬው መፍትሔ የሚሰጠኝ ሰው ሳይኖረኝ እሱ ካወቀብኝ እና ከሸሸኝ የተከራዮች መሳቂያ ስሆን…….. ታየኝ
_ _ _ ‘ ይቺ ጩጬ ገና ጡት ሳትጥል አፈቀርኩ እያለች ነው? ሂሂ ‘ ሲሉ …… ለጋነቴን ትተው በደብዳቤ እና ከእናቴም ከአባቴም በስውር ከትምህርት ቤት ስመለስ መንገድ ላይ እየጠበቁ የአፈቀርን የዘወትር ፀሎታቸውን የደገሙ ሁሉ….. መሳለቂያ አገኘን ብለው በሀሜት የገማ አፋቸውን ሞልተው ለመሳደብ ሲያሰፈስፋ እየታየኝ ፈራሁ።

በመሃል የሚወደኝ የሚፈልገኝ እንዲመስለኝ……. በውስጤ የተቀጣጠለችዋን የፍቅር እሳት እፍፍፍፍፍፍፍፍፍፍፍፍ እያለ ያጋግላታል። ውስጤ ገለባ የሞላው ነበር እንዴ?

በምን ያህል ጊዜ ውስጥ እንደሆነ በማላስታውሰው ጊዜ….. ግቢው ፀጥጥታው የሚያቃጥር በመሰለ…… ከሰዓት ስንገናኝ በብዛት እና በውበት የተፃፈ ውብ ደብዳቤ ……. በፍርሃት ሊሟሟ የደረሰ መስሎ…..
“በእመብርሃን ለማንም እንዳታሳይ …. እማማም ወንድምሽም እንዳያገኙት ካነበብሽው በኋላ ቀደሽ ጣይው ” ብሎ ሰጠኝ። እጄን አያልበኝም …. ለምን ደብዳቤውን አራስኩት?

ደብዳቤው….. ውበቱ….. የእጁ ፅሁፍ ጥራቱ…. ተጠንቅቆ እያሰበ እንደፃፈው ይታወቃል። ያልጠበኩት እና የፈለኩት…. በመፈለግ የጠበኩት ነበር።
ተደብቄ የማነብበት ምቹ ቦታ ስፈልግ አላገኘሁም። በመጨረሻም ከለበስኩት ቀሚስ ስር ወገቤ መሃል አጣብቄ ምቹ ሁኔታ ስጠብቅ ቆየሁ…… የማወቅ ጉጉቱ እና ወረቀቱ ገላዬን እየነካካ የሚፈጥረው ስሜት ሰላም ስለነሱኝ…….. ብዙ ሳልቆይ ሽንት ቤት ገባሁ።

” የእኔ ፍቅር የኔ ውድ…… ይህንን ደብዳቤ የፃፍኩልሽ ላንቺ የሚሰማኝ ስሜት ከአቅሜ በላይ ስለሆነብኝ እና ትምህርት ቤት እየመጣሁ ባይሽም ቤት ውስጥም አንቺን ለማናገር ብዙ ብሞክርም አንድም ምቹ ሁኔታ ስላላገኘሁ ነው።
የኔ ፍቅር:- ውዴ ላንቺ ያለኝ ፍቅር ከምችለው በላይ ሆኖብኛል….. አቅቶኛል። እባክሽ ፍቅሬን ተረጅልኝ። ሳይሽ አንችም ለኔ ፍቅር ያለሽ ይመስለኛል። የኔ ፍቅር እመብርሃንን እልሻለሁ እምልልሻለሁ ከልቤ አፈቅርሻለሁ!!! አንቺም ለኔ ተመሳሳይ የፍቅር ስሜት ካለሽ አሳውቂኝ እና ለቤተሰቦችሽ ሽማግሌ እልካለሁ። አገባሻለሁ። እማማን በጣም እንደምወዳት ታውቂያለሽ እሷም እኔን በጣም ነው የምትወደኝ። እማማን ባናግራት እሺ እንደምትል አውቃለሁ ምክንያቱም እኔን ስለምትወደኝ ነው። ግን አንቺን መጀመሪያ መጠየቅ አለብኝ። ታፈቅሪኛለሽ ወይ? ሳትፈሪ ሳታፍሪ ንገሪኝ በእመብርሃን? እኔ ትምህርቴን መማር እያቃተኝ ነው። ታውቂያለሽ ወደ ዮኒቨርስቲ የምገባበት አመት እንደሆነ? በዚህ ሁኔታ ከቀጠልኩ ግን መውደቄ አይቀርም። የኔ ውድ:- በማይረባ ነገር የሚያማምሩ አይኖችሽን አደከምኳቸው አይደል። ይቅርታ የኔ ቆንጆ። መልስሽን በጉጉት እጠብቃለሁ ያንችው ውድ አፍቃሪ። ”

F.A(ሚያዝያ 21ቀን 1997ዓ.ም)
ለ ውድ S.W

ደብዳቤውን ሽንት ቤት እየገባሁና እየወጣሁ ደጋግሜ አነበብኩት። ባነበብኩት ቁጥር ደሞ እንደ አዲስ ሰውነቴን ያልበኛል……. እንደ ኤለክትሪክ መያዝ የመሰለ የሚነዝር…… በሙሉ ነፍሴ የሚሰራጭ ሃይለኛ መጋጋል ይፈጥርብኛል። የዛን ቀን ሰው ሁሉ የሚያውቅብን እየመሰለኝ ስቁነጠነጥ …….. እሱም በፍርሃት ተውጦ መስኮት ላይ ተቀምጦ ስወጣ ስገባ ስሜቴን ሲያጠና ዋለ። ሳየው እየባባሁ ሰውነቴ እየራደ በስሜት ስተራመስ እንደ ኤሊ እያዘገመ ቀኑ እንደምንም መሸ። ሁሉም ከተኙ በኋላ እኩለ ሌሊት ድረስ እሱን እያሰብኩ እንቅልፍ አልወስድ ብሎኝ ስቸገር ቆየሁ። ለደብዳቤው ምላሽ ለመስጠት አሰብኩ እና መፃፍ ጀመርኩ። እሱ የፃፈውን እያነበብኩ ለያንዳንዱ ጥያቄ መልስ እየሰጠሁ ፃፍኩለት። መጨረሻ ላይ ” እመብርሃን እኔም አፈቅርሃለሁ ” ይላል።

ፅፌ ከጨረስኩ በኋላ ደብዳቤውን አቅፌው ሊነጋጋ ሲል እንደምንም ተኛሁ። እናቴ በጠዋት ስለምትነቃ ድምጿን በመስማት የመንቃት ልምድ ነበረኝ። ተነሳሁና ትምህርት ቤት ከመሔዱ በፊት እንዴትም ብዬ ደብዳቤውን ለመስጠት ሰው እንዳያየን ስቁነጠነጥ ቆየሁ። ተሳካልኝ።
ከዛች ቀን በኋላ ፍቅራችን አይን እያወጣ…… እግር እያበጀ መሄድ ጀመረ። በጣም ብዙ ደብዳቤዎች ይፅፋል።” ናፍቀሽኛል የኔ ፍቅር ” እኔም ብዙ እፅፋለሁ ” እኔም ናፍቀኸኛል ” እና አጠር አጠር ያሉ መልዕክቶች ለምሳሌ”የኔ ፍቅር ….. 4:30 ላይ ለእረፍት ስንወጣ በቤት ስልክ ስለምደውል አንቺ እንድታነሺው። ቤት ውስጥ ሰው ካለ የምልሽን በዝምታ ታዳምጪ እና ቁጥር ተሳስተዋል ብለሽ ዝጊው ።ሰው ከሌለ ደሞ እናወራለን እሺ! አፈቅርሻለሁ የኔ ፍቅር ” ይቺን የመሰለች ነገር….. ትንሽዬ ወረቀት በስርዓቱ በልክ የተቆረጠች…….. በንፅህና የተፃፈባት ትሆናለች። የመከላኪያ ፓስታችን ነገር የተለየች እና ማንም የማይገምታት የ ቢክ ስክሪፕቶ ክዳን ናት። ክዳኗ ከሆዷ ሰፋ ስለምትል መልዕክታችንን ጠቅልላ እንዳይታይ የምትሰውርልን ናት። ለመወርወር ትመቻለች እናም የታለመው ቦታ ላይ ትደርሳለች። ብዙ ቀናትን በዚህ መልክ ስንፃፃፍ…… የሱ መስኮት ላይ የምትቀመጥ የስክሪፕቶ ክዳን አትጠፋም። አንዳንዴማ ይፅፍልኝና ከቤቱ ሳይወጣ በመስኮት ሲወረውርልኝ ድንገት እግሬ ላይ እንዳረፈች( ወይ እቃ ትመታና ጠጠር የተወረወረ ታስመስላለች) የሆነ ሰው ብቅ ይላል። እና በእግር ስትመታ የሆነ ጥግ ስትይዝ አያታለሁ። እንደ ጠባቂ መላክ በንቃት ስጠብቃት እቆያለሁ። ከአሁን አሁን ወንድሜ “ምንድነው ይሄ ደሞ ” ብሎ ገላልጦ አነበባት እያልኩ ስሸማቀቅ እቆይና አፍታ እንዳገኘሁ በሩጫ ይዣት ወደ ሽንት ቤት እገባለሁ። ካነበብኳት በኋላ ሸረካክቼ እዛው እጨምራታለሁ። መደበቂያ ቦታ ስለሌለኝ ( ደጋግሜ ማንበብ ብፈልግም )አስቀምጬ እረፍት አላገኝም። ግቢያችን ውስጥ ተከራይቶ መኖር ከጀመረ አንድ አመት አልፎ ሁለተኛ አመት ጀመረ። ቤተሰቡ ጋር ያለው ቅርበትም በጣም እየጠበቀ መጣ።

የመጨረሻዋ ምሽት ….. ዛፎች በነፋሻማው ምሽት ደስታ የተሰማቸው ይመስላል። ፀጥታ ነግሷል። እናቴና አባቴ የእራት ግብዣ ሄደዋል ቤት እኔና ወንድሜ ብቻ አለን። መስኮት በሩ ሁሉ ተዘግቷል። ናፈቀኝ። ሰበብ ፈጥሬ ለመሄድ ስላሰብኩ ወንድሜን ፈርቼ እየተቁነጠነጥኩ ነው። ዘወትር እሱን ለማየት ስፈልግ የምፈጥራት አስፈላጊ የምትመስል ስራዬ ውሃ መቅዳት ናት።
ወጣሁ። ልክ መውጣቴን እንደሚያውቅ እና እየጠበቀኝ እንደነበር ሁሉ በምሽት መስኮት ከፍቶ ተቀምጧል። ይቀዘቅዛል አይበርደውም? ስንተያይ ፈገግታ ተለዋወጥን። አልፌ ከመሔዴ በፊት ትንሽዬዋ ደብዳቤ እንደተለመደው በስክሪፕቶ ክዳን ውስጥ እንደሆነች ሰጠኝ። ውሃውን እየቀዳሁ በደብዛዛው የምሽት ብርሃን አነበብኳት። ልቤ መደለቅ የጀመረውን ከበሮውን አላቋረጠም። ” የኔ ፍቅር በጣም ናፍቀሽኛል ቤት ማንም የለም። ከመጣሽ እቅፍፍፍፍፍፍ አደርግሻለሁ!!! እባክሽ ነይ እመብርሃንን ሌላ ምንም አላደርግሽም። ቶሎ ነይ የኔ ቆንጆ ” ይላል። ሰውነቴን እኔ እያንቀሳቀስኩት እንደነበር አላወኩም። ደጋግሜ አነበብኳት እመብርሃንን የምትለዋን አስምሮባታል።
ወደ ክፍሉ ገባሁ።…….

ልክ ወደ ክፍሉ እንደገባሁ ቀጭን ወገቤን ጥምጥም አድርጎ ያለኝና። ወደ ሆዱ ወስዶ ለጠፈኝ። የአስተቃቀፉ ጥብቀት ከውስጡ ያለውን ፍቅር ያገረሸበት ይመስል…. በቅፅበት የክፍሉን በር ቆለፈና እጆቼን እየጎተተ የፍራሹ ደርዝ ላይ ጠቀመጠ። እኔ ከሱ ጭን ላይ እንድቀመጥ ተመቻችቶ….. በቀጭን ሰውነቱ ላይ መቀመጥ ያን ያክል ሰላም አልነሳኝም። መስኮቱ እና በመስኮቱ የሚገባው ብርሃን ግን ሀሳቤን ደጋግሞ እየነጠቀኝ ነበር። አንገቴን አቀፈ አንገቱን አቀፍኩ። ጉንጬ ላይ ሳመኝ። ጉንጬ ላይ ሳምኩት። ከዛ የቀጠለውን ምን እንደነበር ያወኩት ቆይቶ ነው። አንገቴ ውስጥ ገብቶ…. በማላውቀው በማይገባኝ መንገድ ሲስመኝ ቆዬ…… ወዲያው ቀና ብሎ በስሜት የቀላ ቀይ ፊቴን እና ከትንሹ የተከፈተ ትንንሽ የከንፈሬን ጠርዝ አጠና….. ፈጠን ብሎ አፌን በአፉ እንዳይናገሩ አደረጋቸው። ከሁኔታው ምንም የማላውቅ መሆኔን ተረድቷል። አልተቃወምኩትም። ያለ ንግግር ያለፈውን አመት ቤተሰቦቹ ጋር ለእረፍት ሲሄድ ያሳለፍኩትን የናፍቆት ዝምታ የሚያፈነዳልኝ ብቸኛው መንገድ አፉ ውስጥ ያለ መስሎኝ ነበር።

የ97 ምርጫ እና የወጣት ተማሪዎች አመፅ ሲፋፋም ብዙ ተከራዮች ቤት ውስጥ እየተቆለፈባቸው ቤት ውስጥ እንደሌሉ የምታስመስልልላቸው እናቴ ነበረች። በተለይ ለሱ የነበራት ፍቅር የተለየ የነበረው ለእናቱ ብቸኛ ልጅ መሆኑን ስላጫወታት….. የምትፈልገውን ነገር እንዲያደርግላት ስለምታውቅ ነበር። ቀስ በቀስ ከአባቴም ጋር የነበራቸው ቅርበት እየጨመረ “የት የሄደ ያ ልጅ” ማለት ጀምሮ ነበር።
እናቴ ለኔ አብዝታ ከመጨነቋ የተነሳ ቶሎ ትዳር እንድይዝና ከእራሷ ጭንቀት እንድትገላገል ትፈልጋለች።” ሞኝ ናት እሷ በከረሜላ ትታለላለች “……. ትለኛለች። ምኔ ነው ሞኝ? ስለ ውበቴ ከተወራ ጭራሽ አትወድም። ተከራዮች ጠባዮን ስለሚያውቁ ሆን ብለው ” ይቺ ልጅ ግን እንዴት አድርጎ ነው የፈጠራት ከሰው አትነጋገር ዝም ብላ ቆንጆ ብቻ ስታድግ ደሞ ለቁንጅና ስትደርስ ወንዱን ሁሉ ታጋድለዋለች እማማ ጉድሽ ነው!” ይሏታል። እሷም ድምጿን ከፍ አድርጋ ” ኧረ እነዚህ ቡዳ አይኖች ልጄን ለምን አይተዋትም? አይቶ አያውቅ ሁሉ! አሁንስ ትምህርት ቤት አላስሄድ ብለዋት የለም። ደሞ ከዚህም አሉ አውቃለሁ ከቤቴ ሆነው ልጄን ማባለግ የሚፈልጉ! እንም ነቅቻለሁ። ቆንጆ ባል አግኝቸላታለሁ በወግ በማዕረግ ነው ልጄን የምድራት ” ትላለች እሱን ማለቷ እንደሆነ እሷም እኔም እናውቃለን። አንድ ነገር ከተናገርኩ ምላሹን ስለማልችለው….. በተለይ ሰው ፊት ከሆነ አንድ ነገር አልናገርም።

ብዙዎቹ ወንዶች ከወደዷት የሚጠብቁት ምላሽ መገፋትን….. አለመፈለግ ሆኖ አገኘሁት። ያልወደድኩትን ልቀርበው…. ያቀረብኩትን ላርቀው እንዴት ይቻለኛል። እነሱስ ቢሆኑ ይሄን የሚመርጡት በምን አይነት ሳይንስ ነው!? አልጋ ላይ ከመሮጥ የምቆጠበውም ላደክማቸው ስለማስብ….. የደከሙባትን የመተው አቅም እንደሌላቸው ስለማውቀው ነው። በሰውነቴ ተገፍቼ በችኮላ የተኛሁት ወንድ በችኮላ እንደመጣው ሆኖ ይሄዳል። መንገድ ላይ ቢያየኝ እንደማያውቀኝ ሆኖ ይሄዳል። በዚህ የወንዶች ፀባይ የተማረርኩ እኔ ስከተላቸው የሚሮጡት…… ስሸሻቸው የሚንገበገቡ እንደሆኑ አውቄያለሁ። በምን ቀመር እንደሆነ ግን እስካሁን ሊገባኝ አልቻለም።

በዛች የፀጥታ ምሽት አንገት ለአንገት እንደተናነቅን….. ጭኑ ላይ እንደተቀመጥኩ…. ከንፈሬን እንግዳ የማበጥ ስሜት አንደተሰማኝ ሳንላቀቅ እንደተቀመጥን…. ወንድሜ በዝምታ መስኮቱ ላይ አስግጎ አየን። ሁለታችንም ድንጋጤና በሀፍረት አፈጠጥንበት “አንቺ እስካሁን እዚ ምን ትሰሪያለሽ? አሁን ነይ ቶሎ! ደሞ ለእማማ እነግርልሻለሁ ቆይ!!!” አለ ብድግ አልኩ። ፍርሃቴ መሞት ድረስ የሚያስመኝ ነበር። ቤት ከገባሁ በኋላ ቤተሰቦቼ እስኪመጡ ድረስ ከወንድሜ ጋር በዝምታ ተቀመጥን። እንዳትናገር ብዬ አለመንኩትም። ሲነግራት ብቻ ምን እንደምትለኝ እና ምን እንደምላት ሳስብ ቆየሁ ። ቤት ከመጡ በኋላ እንደተለመደው ለእኔና ለወንድሜ እራት ቀርቦልን ነካክተን ጠግበናል ብለን ተኛን።

ሲነጋ ጠዋት ትምህርት ቤት ሄድኩ። ከትምህርት ቤት ስመለስ ገና ልብሴን ሳልለውጥ እናቴ እሳት ሆና ጠበቀችኝ። ” ምንድነው ያደረገሽ ምን አረገሽ ንገሪኝ ” አለች ከተከሻዬ ላይ ይዛ እየወዘወዘች ና በሀይል እየጮኸች። ” ምንም አላደረገኝም ” አልኩ በፍርሃት እየተንቀጠቀጥኩ ። እናቴ እንዲ ትሆናለች ብዬ አላሰብኩም ነበር። የምትፈልገው ነገር በዚህ መንገድ መሄዱ ያስደነግጣል እንጂ ምንም እንዳልፈለገች እና እንዳልተባበረች ሆና እኔ ላይ በማበዷ የተፈጠረውን ነገር ለሷ ለማስረዳትና ለማሳመን መሞከር እንኳን አይቻልም። ለረጅም ሰዓት ብዙ ጥያቄዎች አከታትላ ስትጠይቀኝ ቆየች። ከጩኸት ጋር ስለሆነ የብዙዎቹን ጥያቄዎች መልስ አልሰጠሁም።

እየቆየች እንደገና የማታለል ጥያቄዎቿን መጠየቅ ጀመረች ” ማሬ የእኔ እናት እኔ’ኮ እናትሽ ነኝ እወድሻለሁ ምንም እንድትሆኝብኝ….. የማንም መጫወቻ ሆነሽ…. የማንም መሳቂያ ሆነሽ እንድትቀሪብኝ ስለማልፈልግ ነው። በይ ንገሪኝ አሁን ደፍሮሻል? ” አለች። “ኧረ በፍፁም ከንፈሬ ላይ ብቻ ነው የሳመኝ ” አልኳት ልትበሳጭ ልትቆጣኝ ትሞክርና ስሜቷን ትቆጣጠራለች። ” ትወጅዋለሽ!? አለች ምላሼን ብታውቅም ” አወ እወደዋለሁ!” አልኩ በትንሹ ፈርጠም ብዬ ” እሱስ ይወድሻል? ”
“አወ ይወደኛል ”
“በምን አወቅሽ? ”
“አገባሻለሁ ብሎኛል ” በዚህ ሰዓት እናቴ ከት ብላ የንዴት ሳቅ ሳቀችና
” አንቺ ገና ልጅ ነሽ የወንዶችን ውሸት በምን አምነሽ ነው አገባሻለሁ ሲልሽ እሺ ብለሽ የተቀበልሽው? ”
“አምነዋለሁ እመብርሃንን ብሎኛል” አልኩ
ትንሽ ዝም አለች ውስጧ የተቀጣጠለውን ቁጣ ለማብረድ ይመስላል
” እሺ እና ምን አደረጋችሁ እስቲ ንገሪኝ? አሁን እውነቱን ከነገርሽኝ ቀስ ብዬ ለአባትሽ እነግረዋለሁ አሳምነዋለሁ። ድል ያለ ድግስ ደግሼ ትጋባላችሁ። እኛም በልጅነታችን ነው የተዳርነው። ምን ትሆኛለሽ! ” አለች
” እሺ መጀመሪያ ደብዳቤ ፃፈልኝ እና እንደሚወደኝ ነገረኝ እኔም እወድሃለሁ አልኩት። ከዛ አንዴ ልቀፍሽ አለኝ እመብርሃንን አልነካሽም አለኝ እና እሺ ብዬ ክፍሉ ሄድኩ እና አቅፎኝ ከንፈሬ ላይ እየሳመኝ እያለ ወንድሜ መጣ ድንገት ወጣሁ”
” አሃ ያ ሁሉ ጊዜማ ክፍሉ ቁጭ ብለሽ ዝም ብሎ አይለቅሽም። አሁን እሱን አሳስረዋለሁ ህፃን ልጅ በማባበል ብለው ሲገርፉት እውነቱን ይናገራል!!” አለች
ያልጠበኩት መልስ ነበር። ተርበተበትኩ እናቴን መለመን ለማሳመን መሞከር ጀመርኩ። መጨረሻ ላይ አንቺ እሱን አንድ ነገር ካስደረግሽው እኔ ራሴን አጠፋልሻለሁ አልኳት። አነጋገሬ የተመታች አስመሰላት። ዝም ብላ ስታስብ ቆየች።

ከሰዓት በኋላ ለብቻው ጠርታ አናገረችው። ደሞ እሱን ስታናግረው ሳትቆጣ በእርጋታ ነበር። ምን እንደጠየቀችም ምን እንደመለሰላት ዛሬም ድረስ አላውቅም። ብቻ በሆነ ነገር እንደተስማሙ ሁሉ ሰላም አውርደዋል። ለኔ ግን “ቀና ብለሽ ብታይው እንኳን!!!” የምትል ማረፊያ የሌላት ቀጭን ትዕዛዝ ተሰጥቶኛል። ለምን እንደሆነ አላውቅም እሱ ከሁሉም ጋር ሰላምታ ይባባላል። በመሃከላቸው ምንም የተፈጠረ አይመስልም። እንደተለመደው የስክሪፕቶ ክዳን ውስጥ መልዕክት ፅፎ ላከልኝ። ስለተፈጠረው ነገር ይቅርታ የሚጠይቅ እና ግንኙነታችንን በድብቅ ማድረግ እንደምንችል ለማሳመን የሚጥር። እኔ ግን ከሱ ፍቅር የበለጠ የእናቴን ቁጣ ፈርቼ ወደ መስኮት ላለማየት ስታገል የትምህርት አመቱ አለቀ። የመጨረሻ ቀን ለብቻዬ ለማግኘት ሲሞክር ሆን ብዬ ስርቀው ዋልኩ። ከቤተሰቤ ጋር ፎቶ ልነሳ ብሎ ከመሃከላቸው እየተቀመጠ እየተቃቀፋ ፎቶ ሲነሱ እኔ በሩቅ ተመልካች ሆንኩ። መረሳቴ ሆን ተብሎ የተጠና ነበር።
ከግቢያችን ከለቀቀ ስድስት ወር እንደሆነውና ስልክ መደወል እንዳቆመ እናቴ ስትናገር ሰማኋት። ጊዜው እርቋል። ትዝታው ና ናፍቆቱ ግን የዝምታየን መጠን ከፍ አድርጎት ብዙ ጊዜ ተጫዋች አልነበርኩም። “ዝምተኛዋ ልጅ” እየተባልኩ እንደምጠራ አወኩ።
ከአንድ አመት በኋላ’ በፓለቲካ አመፅ አለህበት….. አመፅ እንዲነሳሳ በራሪ ወረቀት ትበትናለህ….. ከህዝብ ስልክ ላይ ገንዘብ ትዘርፋለህ ‘ የመሳሰሉ ክሶች ቀርበውበት ለሁለት አመት እንደተፈረደበት ሰማሁ።
ማረሚያ ሄጄ ለማየት ብሞክርም አልተሳካልኝም። እናቴም ደጋግማ” ልጄን ” ስትል ሰነባበተች። በጊዜ ሁሉም ተረሳ።

ከ 9 አመት በኋላ በኋላ ድንገት መንገድ ላይ ስንገናኝ ….. ለዘመናት ተዳፍኖ የቆየውን ፍርሃቴን አስታወሰኝ። መንገድ ላይ በመገረም ለረጅም ጊዜ ተቃቅፈን ሰላምታ ተባባልን። መልኩ ብዙ አልተለወጠም። ስለ ትዳር ሂወቱ ስለ ልጆቹ ፈገግ ብሎ አጫወተኝ። በትዳሩ ደስተኛ እንደሆነ ከሁኔታው ከንግግሩ ተረዳሁ። ……. ትዝታን መቀስቀስ ትርፍ እንደሌለው ደጋግሞ ነግሮኛል። መገናኘታችን የሚፈጥረው ጥሩ ስሜት ስለማይሆን መልካም ሂወት እንዲገጥመኝ ተመኝቶልኝ ተለየኝ።
አሁንም ገና ያልተፈታ ብዙ ጥያቄ ቢኖረኝም …… መንገዶቻችን ጥንድ ሆነዋልና የማይገናኙ መስመሮችን ስንከተል እንዳንደክም አርፈናል።

ትንሳኤ ካሳሁን

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትስስር ይፍጠሩ

325,851FansLike
49,039FollowersFollow
13,194SubscribersSubscribe