ተከታዮችዎን የመጠበቅ ጥበብ

ማኅበራዊ ሥነ ልቦና ‹አስተሳሰባችን፣ ተፅዕኗችንና አንዳችን ከሌላችን ጋር ያለን ግንኙነት  በሳይንሳዊ መንገድ የሚጠናበት› በመሆኑ እኛም የማኅበረሰቡ አንድ አካል መሆናችንን የሚያስረዳ የሳይንስ ዘርፍ ነው፡፡ የሰው ልጅ የአንድ ቀን ሕይወቱን 70 እና 80 በመቶ ከሌሎች ጋር በመገናኘት የሚያሳልፍ እንደመሆኑ አንዱ በሌላው ተፅዕኖ ስር መውደቁ አይቀሬ ነው፡፡ ታዲያ እርስዎ በአንድም ይሁን በሌላ መልኩ በርካታ ተከታዮች ያሉዎት ከሆነ እነኚህን ተከታዮች ጠብቀው ማቆየት የሚችሉት ምን ሲያደርጉ ይሆን?

  1. ዕምነት

ዕምነት የሁሉም ግንኙነቶች መሠረት ነው፡፡ መሪን መከተል የምንጀምረው ስናምነው ነው፡፡ ማመን ስንጀምር የመሥራትና ስኬታማ የመሆን አቅማችን ይጨምራል፡፡ ኃላፊነታችንን በአግባቡ ማከናወንና ያመንናቸውን መሪዎች ለማስደሰት ከፍተኛ ጥረት እናደርጋለን፡፡ በርግጥ መሪዎችን መከተል ቀላል አይደለም፡፡ የሚጠይቃቸው ቅድመ ሁኔታዎች አሉ፡፡ ማንኛውንም መሪ ከመከተል በፊት በፈጸማቸው ተግባራት መርካት አለብን፡፡ ይህ ደግሞ የራሱን ጊዜ ይጠይቃል፡፡ መሪዎች በሥራቸው ላይ የሚያሳዩት መሠጠትና ተጠያቂነት በተከታዮቻቸው ዘንድ ከፍተኛ መተማመን ይፈጥራል፡፡ ከሌሎች ጋር አብረው የሚሠሩ፣ በውሳኔዎቻቸው ሌሎችን የሚያሳትፉ፣ ጽኑ አቋም ያላቸው፣ ንግግራቸውን በተግባር መግለጽ የሚችሉና ሕግና ሥርዓትን የሚያከብሩ ሲሆኑ በደጋፊዎቻቸው ይወደዳሉ፡፡ የሚመሯቸው ሠራተኞች ወይም ሕዝቦች ክፉ እንዳይነካቸው የሚጨነቁ፣ ተስፋ በቆረጡና በአልችልም ሃሳብ ሲያዙ ‹አይዟችሁ!› በማለት ቀድመው የሚደርሱ ሲሆኑ በደጋፊዎቻቸው ዘንድ ይበልጥ ይታመናሉ፤ ይወደዳሉም፡፡

  1. ርኅራኄ

ሰዎች ፍላጎታቸውን የሚረዱላቸውና የሚጠነቀቁላቸው ሰዎች እንዲመሯቸው ይሻሉ፡፡ ጋሉፕ የተባለው የጥናት ማዕከል በሠራው ጥናት መሠረት 10 ሺህ ሠራተኞች ከመሪዎቻቸው የሚፈልጓቸውን ነገሮች ተጠይቀው ‹‹እንክብካቤ፣ ወዳጅነት፣ ደስታና ፍቅር›› እንሻለን ብለዋል፡፡ ሰዎች የሚጠነቀቅና ጉዳዬ ብሎ የሚያስባቸው መሪ መኖሩን ካረጋገጡ በሥራቸው ትርፋማ ይሆናሉ፡፡ በተቋሙ ለረጅም ጊዜ የመቆየት ዕድላቸውም ሰፊ ይሆናል፡፡

  1. እርጋታ

ማንኛውም ሰው በሀገሩም ሆነ በሚሠራባቸው ተቋማት የተረጋጋ ነገር እንዲኖር ይፈልጋል፡፡ በነውጥ ጊዜያት ታዲያ መሪዎች ይህን እርጋታ የማስፈን ከፍተኛ ፈተና ውስጥ ይወድቃሉ፡፡ ይህን ፈተና የመቋቋም ተነሳሽነትና ብቃት ያላቸው መሪዎች ለተከታዮቻቸው መከታ ናቸውና በማንኛውም ወቅት ከደጋፊዎቻቸው የሚያገኙት ድጋፍ ጠንካራ ሆኖ ይቀጥላል፡፡

  1. ተስፋ

ተከታዮች ከፊታቸው ተስፋ እንዳለና እዚያም የሚያደርስ ጥርት ያለ ጎዳና ላይ እየተራመዱ መሆኑን ማረጋገጥ ይፈልጋሉ፡፡ የመሪያቸውን ራእይ የሚጋሩ ሠራተኞች ወይም ዜጎች አዎንታዊ አስተሳሰባቸው ከፍተኛ ስለሚሆን የማምረት አቅማቸውም በዚያው መጠን ይጨምራል፡፡ ተስፋ ከሌለ ጥርጣሬና አቅምን በሚገባ አውቆ አለመጠቀም ይነግሣሉ፡፡ ይህ ደግሞ በመሪዎችና በተከታዮቻቸው መካከል የሚኖረውን ግንኙነት ጥያቄ ውስጥ ሊከተው ይችላል፡፡

Kumneger Media
Kumneger Media
Kumneger Media is a News and Entertainment Website & Channel. Kumneger Media in addition to News and Entertainment it is the hub of Politics, Movies, Drama, Music, Comedy, Documentary and More!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትስስር ይፍጠሩ

325,851FansLike
49,039FollowersFollow
13,194SubscribersSubscribe