ቱርካዊት ሳይንቲስት የፈጠሩት ካንሰርን የሚመረምር ዘመናዊው ጡት መያዣ ለሴቶች ተስማሚ ነው ተባለ

የቱርካዊቷ ሳይንቲስት አዲስ ጡት መያዣ ፈጥረዋል። ይህ ጡት መያዣ በተለይ ለካንሰር ከፍተኛ ተጋላጭ ለሆኑ ሴቶች የሚስማማ ነው ተብሏል።

ጡት መያዣው በጡት መያዣ ላይ ደረብ ተደርጎ ሊጠለቅ ይችላል።አንዲት ሴት ካፌ ቁጭ ብላ ቡና ፉት እያለች ጡት መያዣዋ ሙሉ ምርመራ ሊያጠናቅቅ ይችላል። ቡናዋን እስክትጨርስ ኩባያ ቅርጽ ያለው መመርመሪያ ሥራውን ይሠራል።

ይህን ዘመናዊ ጡት መያዣ የፈጠሩት የቱርክ ሳይንቲስቶችን የሚመሩት ዶ/ር ካናን ዳግዳቫይረን ምርምሩን ያደረጉት በአሜሪካ ማሳቹሴትስ የቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ((MIT) ቤተ ሙከራ እንደሆነ ይናገራሉ።

ዶ/ር ካናን ይህን ዘመናዊ ጡት መያዣ የፈለሰፉት ለአክስታቸው መታሰቢያ ይሆን ዘንድ እንደሆነ ገልጠዋል። የዶ/ር ካናን አክስት የሞቱት በጡት ካንሰር ነበር።

ይህ ጡት መያዣ በስድስት ወር እና በዓመት አንድ ጊዜ በሚደረጉ የማሞግራም (Mammogram) የጡት ካንሰር ምርመራ መሀል ያልታሰበ አደጋ ካለ በፍጥነት እና በጊዜ ለማግኘት ይጠቅማል። የጡት ካንሰር ከካንሰሮች ሁሉ ብዙ ሴቶችን የሚገድል ሁለተኛው የካንሰር ዓይነት ነው።

የዓለም ጤና ድርጅት በ2020 (እአአ) ብቻ በዓለም ላይ 2.3 ሚሊዮን ሴቶች በጡት ካንሰር ተይዘው 685 ሺህ የሚሆኑት ሕይወታቸውን ማጣታቸውን ይናገራል።የጡት ካንሰር በመጀመሪያው ደረጃ ሳይዘገይ ከተደረሰበት ወይም በጊዜ ከተገኘ የመዳን ዕድሉ 99 እጅ ነው ይላል የአሜሪካ ካንሰር ማኅበር። ጡት ካንሰርን ዘግይተው ከደረሱበት ግን የመዳን ዕድሉ 22 ከመቶ ብቻ ነው።

አዲሱ ጡት መያዣ የሚሠራው እንዴት ነው?

የማሳቹሴትስ የቴክኖሎጂ ኢንስቲቲዩት ባልደረባ የሆኑት ሳይንቲስት እና ኢንጂነር ዶ/ር ካናን ይህን የአልትራሳውን ጡት መያዣ የመሥራት ሐሳቡ የመጣላቸው በጡት ካንሰር ታመው የነበሩትን አክስታቸውን በማስታመም ሆስፒታል አልጋ ጎን በነበሩ ጊዜ ነው።

አክስታቸው በተደጋጋሚ ምርመራ ያደርጉ የነበረ ቢሆንም፣ የያዛቸው የጡት ካንሰር ኃያል የሚባል ነበር። ካንሰሩ ከያዛቸው በስድስት ወር ሕይወታቸው ሊያልፍ የቻለውም ለዚሁ ነው።

አሁን የተፈለሰፈው ጡት መያዣ አንደኛ ተለጣጭ ነው። ሁለተኛ ደጋግሞ መጠቀም ይቻላል።

ከጡት መያዣ ጋር በቀላሉ ይለጠፋል። ይህን ለማድረግም ባለሙያ አያስፈልግም።

አልትራሳውንድ ካሜራዎች የተገጠሙለት ሲሆን ካሜራዎቹ በሁሉም አቅጣጫ ጡት ላይ ያለ እብጠት ወይም የጓጎለ ነገርን በቀላሉ ማየት ያስችለዋል።

በተለምዶ አልትራሳውንድ ከቆዳ አልፎ ጠለቅ አድርጎ እንዲመለከት የተለየ ቅባት (ጄል) ያስፈልግ ነበር። ይህ አዲስ መመርመሪያ ግን በጡት መያዣ ላይ ተደርቦም ጡት ውስጥ ያለውን ማየት ይችላል።

መመርመሪያውን የጀሩት ዶ/ር ካናን

የፎቶው ባለመብት,MIመመርመሪያውን የጀሩት ዶ/ር ካናን

ማሞግራም ምንድነው?

የጡት ካንሰርን ለመመርመር የተለመደው መንገድ ማሞግራም ይባላል። በዚህ ዘዴ ጡት በራጅ (X-rayed) ይነሳል። ይህም ማለት ጨረር ወደ ሰውነት ዘልቆ በመግባት ምሥል ያነሳል ማለት ነው። ይህ የሚሆነው በጡት ውስጥ ያለን ትክክለኛ ምሥል ለማግኘት ነው።

በማሞግራም ምርመራ ጊዜ የራጅ ባለሙያው ጡቶችን ተራ በተራ ሁለት የማሽኑ ሳህኖች ላይ እያስቀመጠ ይመረምራል።

ሳህኖቹ አንድ ጡትን መሀል አስገብተው ይጫናሉ። ይህ የሚሆነው ለተወሰኑ ደቂቃዎች ብቻ ነው።

በምርመራ ላይ ያለችው ሴት መጠነኛ የጫና ስሜት (Pressure) ሊሰማት ይችላል። አንዳንድ ሴቶች ላይ ሂደቱ ሕመም ይፈጥራል። ደግነቱ ምርመራው በአጭር ደቂቃ ይጠናቀቃል።

የማሞግራም ምርመራን ወጪ በብዙ አገራት ያሉ የጤና መድኅን ሰጪ ድርጅቶች አይሸፍኑትም። ዋጋውም ወደድ ይላል።

የጡት ካንሰር መመርመሪያ ራጅ

ሴቶች በማሞግራም ወቅት ለምን ሕመም ይሰማቸዋል?

ሄደለን ዩሌ የራዲዮግራፊ ባለሙያ ናቸው።“የሁሉም ሴት ጡት አንድ አይደለም። እያንዳንዱ ጡት የያዘው ግላንዱላር የተባለው ኅብረ ሕዋስ (glandular tissue) እና የስብ ኅብረ ሕዋስ ቲሹ (Fatty Tissue) መጠኑ ይለያያል። በዚህ የተነሳ የተለያዩ ሴቶች ለማሞግራም ምርመራ የሚሰማቸው ስሜት ይለያያል’’ ይላሉ።

ጡቶቻቸው በርከት ያለ ግላንዱላር ኅብረ ሕዋስ ያላቸው ሴቶች በማሞግራም ጊዜ ስብ ከበዛበት ጡት ይልቅ ሕመም ይሰማቸዋል።

በማሞግራም ምርመራ ጊዜ ሕመምን ለመቀነስ ሴቶች ከወር አበባ አንድ ሳምንት ወይም በወር አበባ ወቅት ምርመራውን አለማድረግ ነው። ከምርመራ በፊት ፓራሲታሞል መውሰድም ሕመም ይቀንሳል።

ይህ አዲሱ የአልትራሳውን ጡት መያዣ ለማን ይበልጥ ይስማማል?

ጥናቶች እንደሚያሳዩት የካንሰር ዕጢዎች በመደበኛ የማሞግራም ምርመራ ጊዜ የሚስተዋሉት ከ20 እስከ 30 በመቶ ይሆናሉ። አዲሱን መመርመሪያ የፈጠሩት የኤምአይቲ ሳይንቲስቶች እነዚህ በማሞግራም ጊዜ የሚደበቁ ዕጢዎችን ይህ አዲሱ ጡት መያዣ በቀላሉ ያገኛቸዋል።

በተለይም በከፍተኛ ተጋላጭነት ላይ የሚገኙ ሴቶች እነዚህን የአልትራሳውንድ ጡት መያዣዎችን እንዲጠቀሙ ይመከራል።

በተለይም በሁለት ማሞግራም ምርመራ መሀል የሚከሰቱ አደጋዎችን ለማግኘት ሁነኛ መሣሪያ ነው።

አዲሱ የጡት ካንሰር መመርመሪያ ጡት መያዣ

አዲሱ ጡት መያዣ የት ተሠራ?

የኤምአይቲ ሳይንቲስቶች መሣሪያውን ለመሥራት 6 ዓመት ተኩል ወስዶባቸዋል። በአሜሪካ የፈጠራ ባለቤትነት መብት የተጎናጸፉ ሲሆን፣ በሰዎች ላይ የሚደረጉ ሙከራዎች ተጠናክረው ቀጥለዋል።

አንዱ የጡት መያዣ ዋጋው እስከ አንድ ሺህ ዶላር ያስወጣል። ነገር ግን ይህ ዋጋ ጡት መያዣው በስፋት ሲመረት እየቀነሰ ይመጣል።

ጡት መያዣው ወደ ገበያ ለመውጣት እስከ አምስት ዓመታት ሊወስድበት ይችላል።

በታዳጊ አገሮች የጤና ምርመራ ዝቅተኛ ደረጃ ላይ ስላለ በጡት ካንሰር በቀላል ምርመራ መዳን የሚችሉ ሴቶች ዘግይተው የካንሰር ዕጢ እንዳለባቸው ስለሚደርሱበት ከፍተኛ ሞት ይመዘገባል።

ለዚህም ነው አዲሱ የምርመራ ዘዴ ትልቅ ተስፋ የተጣለበት።

ይህን የፈጠሩት ዶ/ር ከናን “አክስቴ 49 ዓመቷ ነበር። ሞት በጭራሽ አስባው የምታውቀው ነገር አልነበረም። ምን ነበረበት ይህን ጡት መያዣ አግኝታው ቢሆን?” እያሉ ይቆጫሉ።

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትስስር ይፍጠሩ

325,851FansLike
49,039FollowersFollow
13,194SubscribersSubscribe