ኖተርዳም (እመቤታችን) – የፈረንሳያውያን መልክ

ኖተርዳም (እመቤታችን) – የፈረንሳያውያን መልክ

ፈረንሳያውያን ልባቸው በኀዘን ደምቷል፡፡ ፓሪሶች ምልክታቸውን አጥተዋል፡፡ የተባበሩት መንግሥታት የሳይንስ፣ የባህልና የትምህርት ማዕከል (ዩኔስኮ) ቅርሱን በእሳት ተነጥቋል፡፡ ኖተርዳም የተሰኘው ታሪካዊ የቤተክርስቲያን ኪነ ሕንፃ በሺህ የሚቆጠሩ የከተማው ነዋሪዎች ዓይን በኀዘን፣ በቁጭትና፣ በዕንባ እየተመለከተው የእሳት ሲሳይ ኾኗል፡፡ በ12ኛው መቶ ክፍለ ዘመን የተሠራው የኖተርዳም ህንፃ ቤተክርስቲያን የቀደመውን ዘመን አሻራ ለአሁኑ ትውልድ የሚያሳይ የፈረንሳያውያን፣ የአውሮፓውያን፣ ብሎም የመላው ዓለም የስስት ቅርስ ነበር፡፡ በየዓመቱም 13 ሚሊየን ጎብኚዎች ይጎበኙታል፡፡ የሀገሪቱን የወረራ፣ የጦርነትና የነፃነት ታሪኮች ተሻግሮ ለዛሬው ትውልድ ከቀሩት ታላላቅ የዓለማችን ቅርሶች መካከል አንዱ የነበረው ኖተርዳም አሁን የብዙዎችን ልብ በሰበረ የእሳት አደጋ አይኾኑትን ኾኗል፡፡

ቪክቶር ሁጎ የተባለው የፈረንሳይ ዕውቅ ደራሲ እ.ኤ.አ በ1831 ለሕትመት ባበቃው ‘The Hunchback of Notre Dame’ የተሰኘ ልቦለድ መጽሐፉ በሚገባ የጠቀሰውና ናፖሌዎን ቦናፓርቴ እ.ኤ.አ በ1804 የፈረንሳይ ንጉሥ መኾኑን ያወጀበት ቦታም ነው ኖተርዳም፡፡ ታሪካቸው ከመኖር ወደ አለመኖር ሲሻገር በዓይናቸው ከተመለከቱት የሀገሪቱ ዜጎች መካከል አንዱ የኾነው የ50 ዓመቱ ኢማኑኤል ‹‹ቤት መቀመጥ አልቻልኩም፡፡ እዚህ መኾን ነበረብኝ፡፡ ኹላችንም ኖተርዳምን እናውቀዋለን፤ እንወደዋለንም፡፡ እርሱ ቪክቶር ሁጎ ነው፡፡ የባህላችንና የረጅም ታሪካችን አካልም ነው›› በማለት ተናግሯል፡፡ የ25 ዓመት ወጣት የኾነችው ካሚሌም ስሜቷ ተመሳሳይ ነው፡፡ ‹‹ኖተርዳም የፓሪስ ጌጥ ነው፡፡ በከተማዋም የእኔ ተወዳጁ ቦታ ኖተርዳም ነው›› የምትለው ካሚሌ ከኹለት ሳምንታት በፊት ለቡድን ጉብኝት ወደ ስፍራው አምርታ እንደነበር ጠቅሳ የክፍለ ዘመናት ታሪክና ባህል በዚህ ሁኔታ የእሳት እራት ኾኖ መመልከት ልብ የሚሰብር መሆኑን ተናግራለች፡፡

የጋርዲያን ጋዜጣ የቀድሞ ዘጋቢ ለነበረው ሺቭ ማሊክ ደግሞ የኖተርዳም መውደም ‹‹የዓለም ፍጻሜ›› ስሜት ውስጥ የሚከት ነው፡፡ ምክንያቱም ገና ቃጠሎው ሲጀምር ከኖተርዳም ህንፃ ትይዩ በሚገኝ ሌላ ህንፃ ላይ ኾኖ በዓይኖቹ ተመልክቷልና፡፡ ኖተርዳም ከማሊክ የግል ሕይወት ጋር ያለው ትስስር ጥብቅ ነው፡፡ ‹‹ባለቤቴን የሳምኳት በኖተርዳም ጥላ ስር በመኾኑ ሕንፃ ቤተክርስቲያኑ ለእኔ ልክ እንደ ትዳሬ ነው፡፡›› ይላል፡፡ በየጊዜው ልጁንና ሚስቱን ይዞ በዙሪያው ሲመላለስ ለአመል እንኳ ወደ ውስጡ ገብቶ አያውቅም ነበር፡፡ አሁን ቤተክርስቲያኑ መቃጠሉን ሲመለከት ወደ ውስጥ ገብቶ ባለማወቁ ሐፍረት ተሰምቶታል፡፡

የኖተርዳም ቤተክርስቲያን የበርካታ ከዋጋ በላይ የኾኑ ክቡር ቅርሶችና ንዋያተ ቅድሳት መገኛ ሲኾን ከእነኚህም ውስጥ ኢየሱስ ክርስቶስ ከመሰቀሉ በፊት አድርጎት ነበር ተብሎ የሚታመነው የእሾህ አክሊል ይገኝበታል፡፡ የፈረንሳያውያንና የመላው ዓለም ክርስቲያኖች ምልክት የኾነው የኖተርዳም ካቴድራል መቃጠል ያስደነገጣት ቫቲካን የተሰማትን ከፍተኛ ኀዘን ገልጻለች፡፡

ቃጠሎው በምን ምክንያት ተነሳ የሚለውን የብዙዎች ጥያቄ ለመመለስ ደፋ ቀና ማለት የጀመረው የፈረንሳይ ፖሊስ የካቴድራሉን ጣራ መነሻ በማድረግ እየተካሔደ ካለው የጥገና ሥራ ጋር የሚኖረውን ተያያዥነት ማረጋገጥ ቀዳሚ ተግባሩ መኾኑን ጠቁሟል፡፡ የስምንት መቶ ሃምሳ ዓመታት ባለታሪክ የኾነው ኖተርዳም ቤተክርስቲያን በከባድ የእንጨት ሥራ ውጤቶች የተዋቀረ መኾኑና ውስብስብ የእሳት መከላከያ ሥርዓቶች የተዘረጉለት ባለመኾኑ የተነሳው እሳት በቀላሉ ተቀጣጥሎ ከፍተኛ ውድመት እንዲያደርስ ምክንያት ኾኗል፡፡ የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ‹‹እሳቱን ለማጥፋት በሚደረገው ጥረት የውሃ ጣይ አውሮፕላኖችን መጠቀም የተሻለ ነው›› ሲሉ ያቀረቡት የመፍትሔ ሃሳብ ሙሉውን የካቴድራሉን መዋቅር ያፈርሰዋል በሚል ስጋት ተግባር ላይ ሳይውል ቀርቷል፡፡

በውቧ የፈረንሳይ ዋና ከተማ ፓሪስ ውስጥ ሴይኔ የተባለ ወንዝ ላይ በሚገኘው ሌ ዴ ላቺቴ የተባለ ደሴት ላይ የሠፈረው የኖተርዳም ህንፃ ቤተክርስቲያን ፈረንሳይ በኪነ ህንፃው ዘርፍ ውስጥ ያላትን የቆየ ታሪክ የሚያሳይ የሀገሪቱ ሕዝብ የአንድነት ምልክት ነበር፡፡ ላለፉት 150 ዓመታት የተለያዩ ማሻሻያዎችና ጥገናዎች ሲደረጉለት ቢቆዩም በቅርፁም ኾነ በይዘቱ ላይ የፈጠሩት ለውጥ ግን አልነበረም፡፡ እ.ኤ.አ በ1163 መገንባት የጀመረ ህንፃው በጎንና በጎን ያሉትን አስደናቂ የደውል ማማዎች በ1245 ያካተተ ቢኾንም እስከ 14ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ግን ሥራው ሙሉ በሙሉ አልተጠናቀቀም ነበር፡፡

በ1250 ተተክሎ የነበረው ጉልላት ከአምስት ምዕተ ዓመታ በኋላ እንዲነሳ ቢደረግም በ19ኛው መቶ ክፍለ ዘመን መጨረሻ አካባቢ ግን ኢውጌን ቪዮሌት ሌ ዱክ የተባለ የኪነ ህንፃ ባለሙያ መልሶ ጉልላቱን ማቆሙ ከፍተኛ ነቀፌታ አስከትሎበት ነበር፡፡ ባሳለፍነው ሳምንት በተከሰተው የእሳት አደጋም አንዳንድ ሰዎች ለእሳቱ በከፍተኛ ሁኔታ መቀጣጠል ጉልላቱ አስተዋፅኦ አድርጓል ሲሉ ምሬታቸውን ገልጸዋል፡፡

በ1239 ንጉሥ ሉዊስ 9ኛ የኢየሱስ ክርስቶስን የእሾህ አክሊል በቤተክርስቲያኗ ውስጥ አስቀምጧል፡፡ ይህ የእሾህ አክሊል ለንጉሡ በስጦታ የተበረከተው ከኮንስታንቲኖፕል ንጉሥ ሁለተኛ መኾኑ ይነገራል፡፡ የእሾህ አክሊሉ በየወሩ በሚውለው የመጀመርያ ዐርብ ለሕዝበ ክርስቲያኑ ዕይታ የሚቀርብ ሲኾን በዐቢይ ጾም ወቅት ደግሞ በየሳምንቱ ዐርብ ዕለት በአደባባይ ለዕይታ ይቀርባል፡፡ ይህ ቅዱስ ነዋይ ከእሳት ቃጠሎው ከተረፉት ክቡር ቅርሶች መካከል አንዱ ሆኗል፡፡

በመካከለኛው ክፍለ ዘመን በርካታ የፍትሐትና የሠርግ ሥነ ሥርዓቶች ሲካሔዱበት የነበረው የኖተርዳም ካቴድራል በኋላ ፍራንሲስ ኹለተኛ ተብሎ የነገሠው ልዑል ፍራንሲስ የስኮትስ ንግሥት ከነበረችው ሜሪ ጋር ጋብቻውን የፈፀመበት መኾኑ ይነገራል፡፡ በፈረንሳይ አብዮት ወቅት ለከፍተኛ ጉዳት ተጋልጦ የነበረው የኖተርዳም ካቴድራል በፈረንሳያውያን የሃይማኖትና የፖለቲካ ሕይወት ውስጥ ያለው ስፍራ ይህ ነው ተብሎ በጥቂት ቃላትና በቀላል ቋንቋ የሚገለጽ አይደለም፡፡

በኹለተኛው የዓለም ጦርነት ሀገሪቱ በጀርመን ቅኝ ከተያዘችበት ነፃ መውጣቷ ነሐሴ 24 ቀን በ1944 ለፈረንሳያውያን የተበሠረው ከዚህች ቤተክርስቲያን በተደወለ ደውል ነው፡፡ እ.ኤ.አ በ1863 ለሕትመት የበቃው የቪክቶር ሁጎ ልቦለድ ለህንፃ ቤተክርስቲያኑ የሰጠው ትኩረት የሀገሪቱ ዜጎችና የወቅቱ ባለስልጣናት ለቤተክርስቲያኑ ተገቢውን ትኩረት በመስጠት ፊታቸውን ወደ ጥገናና እንክብካቤ ሥራዎች መልሰዋል፡፡ ከቪክቶር ሁጎ ድርሰት በኋላም ኖተርዳም የተለያዩ ፊልሞችና የህፃናት መጻሕፍት ማዕከል ሆኖ ለጥበብ ሥራዎች በግብአትነት ይውል ነበር፡፡ የኖተርዳም ህንፃ ቤተክርስቲያን በቀደመ ታሪኩ ብቻ ሳይኾን ቃጠሎው ከመድረሱ በፊት እስከነበሩት ቀናት ድረስ የአምልኮ ሥነ ሥርዓት ሲካሔድበት የቆየ መኾኑም የተለየ ያደርገዋል፡፡

እንደ ልዩ ምልክት በሚታይ ቅርሳቸው ላይ የደረሰው ውድመት እልህ ውስጥ የከተታቸው ፈረንሳያውያን በፕሬዚዳንታቸው በኩል ቤተክርስቲያኑን መልሰው እንደሚሠሩት ተናግረዋል፡፡ ፕሬዚዳንት ኢማኑኤል ማክሮን ‹‹ኖተርዳምን ከዚህ የበለጠ አሳምረን እንሠራዋለን፡፡ በአምስት ዓመት ውስጥ እንዲጠናቀቅ እፈልጋለሁ፡፡ መሥራት እንችላለን›› ብለዋል፡፡ ፈረንሳይ እ.ኤ.አ በ2024 ለምታስተናግደው የኦሎምፒክ ጨዋታዎች ውድድር የኖተርዳምን ምትክ አቁማ እንግዶቿን የመቀበል ሀሳብ አላት፡፡ ብዙዎች ግን ላለፉት 850 ዓመታት በርካታ ችግሮችን ተጋፍጦ እስከዚህ ዘመን ድረስ የቆየው ውብ ህንፃ ቤተክርስቲያን ከነግርማ ሞገሡ በድጋሚ መሠራት መቻሉን ይጠራጠራሉ፡፡

 

 

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትስስር ይፍጠሩ

325,851FansLike
49,039FollowersFollow
13,194SubscribersSubscribe