ከልጆችዎ ጋር መግባቢያ መንገዶች

ከልጆችዎ ጋር መግባቢያ መንገዶች

ወላጆች ከልጆቻቸው ጋር ለመግባባት ሲቸገሩ መመልከት የተለመደ ነው፡፡ ‹እኔ ልጄ እንዲሆን የምፈልገው እንዲህ ነበር፤ እርሱ ግን እንዲህ ሆኖ ቀረ› ብለው የሚያማርሩ ወላጆችም ቁጥር ቀላል አይደለም፡፡ ወላጅና ልጆች ከማይግባቡባቸው ነገሮች አንዱ ንግግር ነው፡፡  ከልጆች ጋር የሚደረግ ንግግር የዕድሜ ደረጃቸውንና የሚቀለበሉበትን ስነ ልቦናዊ አቅም ግምት ውስጥ የሚያስገባ መሆን አለበት፡፡ ለምሳሌ የሁለት ዓመት ህፃን ልጅን ከስድስት ዓመት ልጅ እኩል ለማናገር ብናስብ ትርፉ ድካም ብቻ ይሆናል፡፡ ስለዚህ ከልጆችዎ ጋር ለመግባባት እንዲችሉ በየዕድሜያቸው መጠን አቀራረብዎና የቃላት አጠቃቀምዎ ሊለያይ እንደሚችል ይገንዘቡ፡፡

ከዜሮ እስከ ሁለት ዓመት

ከሀለት ዓመት በታች ካሉ ህፃናት ጋር የመጀመርያው የመግባቢያ መንገድ መንካት ነው፡፡ ንግግራችሁን በተግባር ለመግለጽ የተለያዩ ድምጸቶችና ቃላትን በሰውነታችሁ እንቅስቃሴ ወይም በምልክት ለመግለጽ ሞክሩ፡፡ በንግግራችሁም ጊዜ በልጆች ዓይነት ቅላጼ ብታወሯቸው መግባባታችሁ ሕይወት ይኖረዋል፡፡ የልጅዎ የመረዳት አቅም አነስተኛ ቢሆንም የሚጠቀሟቸው ቃላት ግን የእርሱን የመናገር ክህሎት የማሳደግ አቅማቸው ከፍተኛ ስለሚሆን ስለሚጠቀሟቸው ቃላት ጤናማነትም ሁለት ጊዜ ማሰብ መልካም ነው፡፡

ከሦስት እስከ አምስት ዓመት

በቻሉት መጠን ለልጅዎ ሙሉ ትኩረትዎን ይስጡት፡፡ አነጋገርዎና የሰውነት ቋንቋዎ ላይ ጥንቃቄ ያድርጉ፡፡ ልጅዎ ስሜቱን በቃላት ለመግለጽ እንዲችልም ድጋፍ ያድርጉለት፡፡ ቀለል ያሉ የማስረዳት መንገዶችንና ውስን ምርጫዎችን ብቻ ይጠቀሙ፡፡

ከስድስት እስከ አሥራ አንድ ዓመት

በዚህ የዕድሜ ክልል ከሚገኙ ልጆችዎ ጋር ለመነጋገር የሚረዳዎት በቂ የግንኙነት ጊዜ ያመቻቹ፡፡ በንግግርዎ ወቅትም ዕድሜያቸውን ከግምት ያስገባ አክብሮት ያሳዩዋቸው፡፡ ከልጆችዎ መረጃ ማግኘት ከፈለጉ ውስን እና ግልጽ ጥያቄዎች ያቅርቡላቸው፡፡ መልስ ለመስጠት ወይም ለማናገር ባይፈልጉ እንኳን እርስዎ ግን ከመናገር ወደኋላ አይበሉ፡፡ በሚያደምጧቸው ወቅትም ለሃሳባቸው አክብሮት በመስጠት በቤተሰብ ጉዳዮች ውስጥ የሚጨምሩት እሴት መኖሩ እንዲሰማቸው ማድረግ ትልቅ ብልህነት ነው፡፡ ቢሳሳቱም ጊዜ ስህተትዎን አምነው ይቀበሉ፡፡

ከአሥራ ሁለት እስከ አሥራ ስምንት ዓመት  

እነኚህ ልጆች ‹አፍላ› በሚባል የዕድሜ ክልል የሚገኙ እንደመሆኑ በእያንዳንዱ ነገር ያለመግባባት አጋጣሚው ሊያድግ ይችላል፡፡ ስለዚህ የመጀመርያው መፍትሔ ልጅዎን ማናገር እና ለልጅዎ መንገር የተለያዩ መሆናቸውን መገንዘብ ነው፡፡ ልጅዎን ሲያናግሩት ለእርሱም ሃሳብ አክብሮትና ዕውቅና መስጠት ተገቢ ነው፡፡ መንገር ካሰቡ ግን የእርስዎ ብቻ መልእክት አድራሽነት የጎላ ስለሚሆን ልጅዎ ተቀባይ ብቻ እንዲሆን ነው የሚያስገድዱት፡፡ የልጅዎን የግል ፍላጎት ያክብሩ፤ ለሚሰነዝራቸው አስተያየቶችም ያለዎትን ክብር ያሳዩ፡፡ በዚህ የአፍላ ዕድሜ ለሚገኝ ልጅዎ ዕምነት ማሳየት በእርስዎ እንዲጠለል የማድረግ ትልቅ ወላጃዊ ጸባይ ነው፡፡ ዕምነት ካሳዩት በእያንዳንዱ ችግሮቹ ከእርስዎ ጋር መማከር ይሻል፡፡ ልጅዎ ራስዎን በመሆንዎ ብቻ ሊያከብርዎ ይፈልጋልና ራስዎን ሆነው ብቻ ይቅረቡት፡፡ በራስ የመተማመን መጠንዎን ከፍ አድርገው በማሳየትም በራስ መተማመኑ ከፍ ያለ ልጅ እንዲኖርዎ ያድርጉ፡፡

 

ምንጭ፡- thecontentedchild.co.uk

 

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትስስር ይፍጠሩ

325,851FansLike
49,039FollowersFollow
13,194SubscribersSubscribe