ወደ አዲስ አበባ ሊጓዝ ሲል ሞቃዲሾ ላይ ተይዞ እስር ቤት የነበረ የብሪታኒያ ዜጋ አብረውት በነበሩ እስረኞች በምላጭ ከተፈጸመበት ጥቃት መትረፉን የእስርቤቱ ባለስልጣናት ለቢቢሲ ተናገሩ።
ለግል የደህንነት ጥበቃ ተቋም የሚሰራው አንቶኒ ቶማስ ኮክስ ላይ በሞቃዲሾ በሚገኘው ማዕከላዊ እስር ቤት ከተፈጸመው ጥቃት ጀርባ በእስር ቤቱ የሚገኙ ተጠርጣሪ የጽንፈኛ እስላማዊ ቡድን አባላት ይኙበታል ተብሏል።
አንቶኒ ቶማስ ኮክስ ለእስር የተዳረገው ከአስር ቀናት በፊት ከሞቃዲሾ ወደ አዲስ አበባ ለመጓዝ አውሮፕላን ማረፊያ ውስጥ በተደረገ ፍተሻ ወቅት የአስለቃሽ ጋዝ ተተኳሾች ሻንጣው ውስጥ በደህንነት ባለስልጣናት ስለተገኘበት ነው።
ግለሰቡ የያዘውን ነገር ባለማሳወቁ የሕዝብን ደህንነት አደጋ ላይ በመጣል ወንጀል ይከሰሳል ተብሏል።
የሞቃዲሾ ማዕከላዊ እስር ቤት ምክትል አስተዳዳሪ የሆኑት አብዲካሪም አሊ ፍራህ እንደተናገሩት፤ ታሳሪው ላይ ጥቃቱ በተፈጸመበት ጊዜ በአንገቱ ላይ ቀላል የመቆረጥ ጉዳት ደርሶበታል ብለዋል።
አስተዳዳሪው ጨምረውም የእስር ቤቱ ጠባቂዎች ስለጥቃቱ ወዲያውኑ መረጃ በማግኘታቸው ግለሰቡን ከከፋ አደጋ ለማዳን ችለዋል ሲሉ ተናግረዋል።
“ከተጠርጣሪዎቹ አንዱ የግለሰቡን አንገት በምላጭ ለመቁረጥ ሲሞክር ልናስቆመው ችለናል። በዚህም መካከልም በጣም ቀላል ቁስለት ደርሶበታል። ነገር ግን አሁን ደህና ነው” ሲሉ አፍራህ ለቢቢሲ ሶማሊኛ ተናግረዋል።
በጥቃቱ ተሳትፈዋል የተባሉት ሁለት ግለሰቦች የእስላማዊ ታጣቂ በቡድኖች አባላት እንደሆኑ እንደሚጠረጠር የእስር ቤቱ ምክትል አስተዳዳሪ ተናግረዋል።
አንደኛው የአል ሻባብ አባል እንደሆነ ሲታሰብ ሌላኛው ደግሞ የእስላማዊው መንግሥት (አይሲስ) አባል እንደሆነ ይታመናል። ሁለቱም በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሚደገፈውን የሶማሊያ መንግሥት የሚወጉ ቡድኖች ናቸው።
የኤምባሲ ባለስልጣናትና ግለሰቡ ይሰራበታል የተባለው የአሜሪካ የግል የደህንነት ተቋም የሆነው ባንክሮፍት ሰራተኞች እስር ቤቱን መጎብኘታቸው ተገልጿል።