በተለያዩ መጽሔቶችና ድረገጾች ላይ ጽሑፎቿን የማውጣት ልምድ ያላት አኔ ሮድሪክ ጆንስ ለአሥራ አምስት ዓመታት ኔት ከተባለ የትዳር አጋሯ ጋር ከቆየችበት የትዳር ሕይወት የቀሰመቻቸውን ልምዶች self.com በተባለ ድረገጽ ላይ አጋርታለች፡፡ ‹የ24 ዓመት ወጣት ሆኜ ከኔት ጋር ስንገናኝ ወደ ትዳር ለመግባት ምንም ዓይነት ዝግጁነት አልነበረንም፡፡ ነገር ግን በትዳሬ ውስጥ ብዙ ነገሮች እንዲኖሩ እፈልግ ነበር› ትላለች፡፡ አኔ በአሥራ አምስት ዓመታት ተማርኳቸው ከምትላቸው ትዳር – ነክ ዕውቀቶች መካከል ጥቂቶቹን እነኾ!
አንዳንድ ዓመታት ‹የተረገሙ› ይኾናሉ፡- ይህን ልብ በሉ፡፡ በትዳራችሁ ፈጽሞ የማትገምቷቸውና ነገሮች ሁሉ ግራ ግራውን የሚጓዙባቸው ዓመታት ሊመጡ ይችላሉ፡፡ አንዳንድ ሰዎች ትዳር በመጀመርያው ዓመት አስቸጋሪ ነው ሲሉ ሌሎች ደግሞ ትዳር አስቸጋሪ የሚኾነው በሁለተኛ ዓመት ቆይታ ውስጥ መኾኑን ይናገራሉ፡፡ እኔ የማውቃት ሴት ደግሞ ሙሉ የትዳር ሕይወቷ የተመሰቃቀለ ነበር፡፡ በእኔም ሕይወት ውስጥ የኛ የባለትዳሮቹ ጸባይ ሳይኾን የሁኔታዎች አለመስተካከል ፈተና ኾኖብን ነበር፡፡ ለምሳሌ ከወዳጅ ዘመድ ተለይተን መኖሪያ ቦታ የቀየርንበት እና አባቴ የሞተበት ዓመት ከባድ ጊዜያት ነበሩ፡፡ እነኚህ ጊዜያት ግን ከባለቤቴ ጋር ይበልጥ ተቀራርበን ችግሮቻችንን ማለፍ የምንችልበት ጉልበት ሰጥተውን አልፈዋል፡፡
አብሮ መጓዝ ፍቅራችሁን ያጠነክረዋል፡- ከባለቤቴ ጋር በጋራ በመኾን የተለያዩ ቦታዎችን ጎብኝተናል፡፡ ቋንቋዎቻቸውን በማንናገርባቸው ሀገራት ውስጥ ምርጥ ጊዜያት አሳልፈናል፡፡ አብሮ መጓዝ አንዳችን ሌላችንን እንድናምን እና አንዳችን በሌላችን ጥንካሬ እንድንደገፍ አድርጎናል፡፡ ከዚህ ጎን ለጎን ግን የየራሳችንን ፍላጎት ተግባራዊ ማድረጋችን አይዘነጋም፡፡ ይህም አያጣላንም፡፡ የሱን የምግብ፣ የሥራ ሰዓት እና ብቻውን ለመኾን የመሻት ምኞት አከብርለታለሁ፡፡ እርሱም ይህን ያደርጋል፡፡
እኩል መኾን አይጠበቅብንም፡- አያቴ ‹የትኛውም ትዳር ሃምሳ ሃምሳ አይደለም› ትለኝ ነበር፡፡ ምንም እንኳ በሥራው ስኬታማና የተመሰገነ ሰው ባገባም በቤት ውስጥ ሥራዎች ላይ ግን እኩል ድርሻ የለንም፡፡ ኃላፊነትን መወጣት፣ የቤት ውስጥ ክንውኖች፣ ገቢ ማስገኘትና ሌሎችም ተግባራት ላይ አንዳችን ከሌላችን እንበልጥ ይኾናል፡፡ ይህ ደግሞ መረዳዳታችንን ይበልጥ ሊያጎላ እንጂ የዝቅተኝነት ስሜት ሊፈጥርብን አይገባም፡፡ ትዳር ውስጥ አንደኛና ሁለተኛ የሚባል ሰው ሊኖርም አይገባም፡፡
እንደ የሥራ አጋራችሁ ተመልከቱት፡- አንዳንዴ ባለቤታችሁን እንደ ሥራ አጋር መመልከት መልካም ነው፡፡ ለምሳሌ እኔ በተደጋጋሚ በር መዝጋቴን እረሳለሁ፡፡ እርሱ ደግሞ አብሮኝ ከቤት ለመውጣት ረጅም ጊዜ ሊወስድበት ይችላል፡፡ በእነኚህ እልህ አስጨራሽ ጊዜያት እንደ ሥራ ባልደረባ በአክብሮት ዓይን መተያየት ያስፈልጋል፡፡ የሥራ ባልደረባችሁ ቢያጠፋ በይቅርታ በማለፍ ሥራችሁ ጤናማ ሆኖ እንዲቀጥል እንደምታደርጉ ሁሉ የትዳር አጋራችሁንም በዚህ ዓይን መመልከት ተገቢ ነው፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ባለቤቴ ኔት ብቻውን ቡና እየጠጣ ጋዜጣና መጽሔቶች የሚያገላብጥባቸው ጊዜያት እንዲኖሩት ይፈልጋል፡፡ ይህን ስለማውቅ እኔም ቡናዬንና የማነበውን መጽሐፍ ይዤ አጠገቡ እቀመጣለሁ፡፡ አብረን እንሆንና ጣፋጭ የዝምታ ጊዜ እናሳልፋለን፡፡
ምንጭ፡- self.com
ከትዳሬ የተማርኳቸው ዕውነታዎች
