ከጅቡቲው የጀልባ አደጋ የተረፉት 16ቱ ኢትዮጵያዊያን ናቸው

በጂቡቲ ሁለት ጀልባዎች ተገልብጠው እስካሁን 52 ሰዎች መሞታቸውን ዓለም አቀፉ የስደተኞች መርጃ ድርጅት (IOM) አስተወቋል።

ዓለም አቀፉ የስደተኞች መርጃ ድርጅት (IOM) ትናንት ሁለቱ ጀልባዎች ወደ የመን ጉዞ እያደረጉ ሳሉ መገልበጣቸው ከተሰማ በኋላ ተጎጂዎችን እያፈላለገ እንደሆነ አስታውቆ ነበር።

ድርጅቱ እንደሚለው ከሆነ በጀልባዎቹ ላይ ተሳፍረው የነበሩት በርካቶቹ ኢትዮጵያውያን መሆናቸውን ነው። የስደተኞች መርጃ ድርጅቱ ዛሬ ላይ ባወጣው መረጃ መሰረት ከአደጋ እስካሁን ህይወታቸው መትረፉ የተረጋጋጠ 16 ሰዎች በሙሉ ኢትዮጵያውያን ናቸው።

”የጓደኞቻቸው አስክሬን ላይ ተራምዶ እንደ ማለፍ ነው”

ከጅቡቲ በስልክ ያነጋገርነው ኢትዮጵያዊው ነቢል ኑር ”ሰኞ ዕለት ከ20 የሚበልጡ ልጆች ከዚህ ነው ተነስተው የሄዱት። ከዚህ የሄዱት 20ዎቹም በተገለበጠችው ጀልባ ውስጥ እንዳሉ አውቄያለሁ። ወደ የመን የሚሄዱ ሰዎች ተራ የሚጠብቁት እዚሁ ነው” ሲል ለቢቢሲ ተናግሯል።

ነቢል በዚህ አደጋ ሁለት የቅርብ ጓደኞቹን እንዳጣ ይናገራል።

”ከዚህ ቀደም በኢትዮጵያ ሰዎች በነበሯቸው የፖለቲካ አመለካካቶች ሳቢያ ከሚደርስባቸው ጫና ለማምለጥ ወደ ጅቡቲ ከመጡ በኋላ ወደ የመን በዚሁ በኩል ያልፉ ነበር። አሁን ግን ወደዚህ የሚመጡት ከዚህ ቀደም አረብ ሃገር ሄደው የነበሩ ሰዎች ናቸው” ሲል ነቢል ያስረዳል።

”በጣም የሚያሳዝነው ግን አሁንም ከጅቡቲ ወደ የመን ለመሄድ ወረፋ እየጠበቁ ያሉ ሰዎች በርካታ መሆናቸው ነው። አሁን ላይ ደግሞ ወጀቡ ከፍ ስላል በጣም አደገኛ ጉዞ ነው የሚሆነው። አሁን ጉዞ ለማድረግ መነሳት የጓደኞቻቸው አስክሬን ላይ ተራምደው እንደማለፍ ነው” ይላል ነቢል።

የዓለም አቀፉ የስደተኞች መርጃ ድርጅት (IOM) የጅቡቲ ተወካይ ላሊኒ ቬራሳሙደ ”የተሻለ ህይወት ፍለጋ በማሰብ በሰው ልጆች ላይ እንዲህ አይነት አሰቃቂ አደጋ ሲደርስ በጣም ያሳዝናል። የጅቡቲ መንግሥት ድጋፍ እንደሚያደርግ አሳውቆናል። እኛም እንዲህ አይነት አሰቃቂ አደጋ እንዳይደርስ እንሰራለን” ብለዋል።

በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ላይ ዓለም አቀፉ የስደተኞች መርጃ ድርጅት በየመን የሚገኙ ወደ 350 የሚጠጉ ፍቃደኛ ኢትዮጵያውያን ስደተኞችን ወደ ሃገራቸው ለመመለስ ዝግጅቱን ማጠናቀቁን አሳውቆ ነበር።

”ስደተኞችን ወደ ሃገራቸው የመመለስ አማራጮች ጠባብ ቢሆኑም የሁለቱ ሃገራት መንግሥታት አብረው በመስራት ስደተኞችን የመመለስ ሥራ እየተሰራ ነው” ሲሉ በየመን የዓለም አቀፉ የስደተኞች መርጃ ድርጅት ኃላፊ ዴቪድ ዴርቲክ ተናግረዋል።

በየመን አደን ከተማ የኢትዮጵያውያን ማህብረሰብ ተወካይ የሆኑት አቶ ዛይድ ዳውድ ሲራጅ ”የመን ፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ ቀውስ ውስጥ ስለምትገኝ በርካታ ስደተኞች ወደ ሃገራቸው የመመለስ ፍላጎት አላቸው፤ ይሁን እንጂ ወደ ሃገራችን ምን ይዘን ነው የምንመለሰው? ተመልሰን ምን አንእሰራለን? በሚሉ ጥያቄዎች ተወጥረው ይገኛሉ” በማለት ያስረዳሉ።

Sourceቢቢሲ
Kumneger Media
Kumneger Media
Kumneger Media is a News and Entertainment Website & Channel. Kumneger Media in addition to News and Entertainment it is the hub of Politics, Movies, Drama, Music, Comedy, Documentary and More!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትስስር ይፍጠሩ

325,851FansLike
49,039FollowersFollow
13,194SubscribersSubscribe