ኬቭን ደ ብሩይነ ‹የተናቀው ኮከብ›

ኬቭን ደ ብሩይነ ‹የተናቀው ኮከብ›

አሁን በእንግሊዙ ክለብ ማንቼስተር ሲቲ ቤት ጥሩ ጊዜን እያሳለፈ የሚገኘው ቤልጅዬማዊው የአማካይ ስፍራ ተጫዋች ኬቭን ዴ ብሩይነ በሌላኛው የእንግሊዝ ክለብ ቼልሲ ለሁለት ዓመታት ያህል ቆይቷል፡፡ ነገር ግን ለምዕራብ ለንደኑ ክለብ ያደረገው ጨዋታ ብዛት በፕሪምየር ሊጉ ሶስት በአጠቃላይ ደግሞ ዘጠኝ ብቻ ነው፡፡ ከዚያም በውሰት ለጀርመኑ ክለብ ቨርደር ብሬመን ተሰጥቷል፡፡ በ2014 ጥር ወር ደግሞ ቼልሲዎች በ18 ሚሊዮን ፓውንድ ለሌላኛው የጀርመን ክለብ ሸጠውታል፡፡

ተጫዋቹ በቼልሲ ቤት በቂ የመሰለፍ እድልን ሳያገኝ ወደሌላ ክለብ ለመዘዋወሩ ዋና ምክንያት በጊዜው የክለቡ አሰልጣኝ የነበሩት ጆዜ ሞሪንሆ ናቸው ተብሎ ይታመናል፡፡ ተጫዋቹ ከሰሞኑ ፕሌየርስ ትሪቡን ከተባለ ድረ ገጽ ጋር ባደረገው ቃለ ምልልስ ስለሁኔታው የተብራራ መረጃ ሰጥቷል፡፡

‹ሁለቴ ብቻ ተነጋግረናል›

‹ከሞሪንሆ ጋር ስለነበረን ሁኔታ መገናኛ ብዙሀኑ የተለያዩ ሃሳቦችን ጽፈዋል› ሲል አስተያየቱን ይጀምራል የ27 ዓመቱ ቤልጅየማዊ ኬቭን ደ ብሩይነ፡፡ ‹‹እውነታው ግን እኔ ጋ ነው ያለው፡፡ እኔ እና ሞሪንሆ የተነጋገርነው ሁለት ጊዜ ብቻ ነው፡፡ በቼልሲ ቤት ስለኔ የነበረው እቅድ ለተወሰነ ጊዜ ለሆነ ክለብ ማዋስ ነበር›› ሲል ይቀጥላል፡፡

ለአንድ ዓመት በጀርመኑ ክለብ ቨርደር ብሬመን በውሰት ቆይታ ሲያደርግ ተጫዋቹ 33 ጊዜ ተሰልፎ 10 ግቦችን ማስቆጠር ችሏል፡፡

‹‹አንድ ቀን ሞሪንሆ የጽሁፍ መልዕክት ላከልኝ፣ እዚህ ትቆያለህ፤ አንተ የዚህ ክለብ አባል እንድትሆን እፈልጋለሁ አለኝ፤ እኔም በጊዜው እንዲህ አሰብኩ፤ በቃ የእሱ እቅድ ውስጥ ተካትቻለሁ፤ ይሄ በጣም ጥሩ ነው አልኩ›› ይላል ኬቭን፡፡

በ2013/14 የውድድር ዓመት መጀመሪያ ላይ አሰልጣኝ ጆዜ ሞሪንሆ ቤልጅየማዊውን አማካይ በሁለት የፕሪምየር ሊግ ጨዋታዎች በቋሚነት አሰልፈውት ነበር፡፡ ግን ወዲያው ወደ ተጠባባቂ ወንበር አወረዱት፡፡ ከዚያ በኋላ እስከ ታህሳስ ወር ድረስ በዚያ ሁኔታ ቆየ፡፡ ተጫዋቹ እንደሚለው እስከዚያ ጊዜ ድረስ ከሞሪንሆ ጋር ምንም አላወሩም፡፡

‹‹በወርሃ ታህሳስ ሞሪንሆ ወደቢሮው አስጠራኝ፤ ምናልባትም ያ ቀን ህይወቴን የቀየረ ውሳኔ የተላለፈበት ቀን ነው፤ ከሞሪንሆ ፊት ለፊት ብዙ ወረቀቶች ይታዩኛል፤ እነሱን እያገለባበጠ ‹አንድ ለግብ የሚሆን ኳስ አቀብለሃል፤ አስር ጊዜ ከተቃራኒ ተጫዋቾች ኳስ ነጥቀሃል፣ ግን አንድም ግብ አላስቆጠርክም› አለኝ፣ የሚለውን ለመረዳትና ምን እያደረገ እንደሆነ ለማወቅ ደቂቃ ፈጅቶብኛል፤ እሱም ወረቀቶቹን ማገላበጡን ቀጥሎ ሌሎች ተጨማሪ ነገሮችን መዘርዘር ጀመረ፤ በክለቡ ውስጥ ያሉት የአጥቂ አማካዮች ያስመዘገቡትን ቁጥር ነገረኝ፤ እነ ዊሊያን፣ ማታ፣ ኦስካር እና ሹርለን የመሳሰሉ ተጫዋቾች አምስት ግቦችን አስቆጥረው አስር ለግብ የሚሆኑ ኳሶችን እንዳቀበሉ ዘረዘረልኝ›› ይላል ደ ብሩይነ በወቅቱ የተከሰተውን በማስታወስ፡፡

‹‹ይህንን ካለ በኋላ እኔ የምለውን መጠበቅ ጀመረ፤ እንዲህ አልኩት፣ ‹አሁን የጠቀስካቸው ተጫዋቾች እኮ አብዛኞቹ ከ15 እና ከ20 በላይ ጨዋታዎችን አድርገዋል፤ እኔ ግን የተሰለፍኩት በሶስት ጨዋታዎች ብቻ ነው፤ ይሄ ልዩነት አይፈጥርም?› ያልተለመደ ነገር ነው፤ ከምር ነው የምናገረው፤ ደግሜ እንዲህ አልኩት ‹አሁን የሚሰማኝ ክለቡ ለእኔ ፍላጎት እንደሌለው ነው፤ እኔ ደግሞ እግር ኳስ መጫወት እፈልጋለሁ፤ ስለዚህ ለሌላ ክለብ ሸኙኝ› አልኩት›› ይላል ኬቭን፡፡

ተጫዋቹ ከሞሪንሆ ጋር ይህንን ከተነጋገረ ከአንድ ወር በኋላ ለጀርመኑ ክለብ ወልፍስበርግ በ18 ሚሊየን ፓውንድ የዝውውር ዋጋ ተሸጠ፡፡

ከአንድ ዓመት በላይ በዚህ ክለብ ውስጥ ሲቆይ 55 ጨዋታዎች ተሰልፎ 13 ግቦችንም አስቆጥሯል፡፡ ባለድንቅ ተሰጥኦ ተጫዋች መሆኑንም አስመስክሯል፡፡ የታላላቅ የአውሮፓ ክለቦች አይን ማረፊያ ሆኗል፡፡ በቼልሲና በአሰልጣኝ ጆዜ ሞሪንሆ ያልተፈለገው፣ የተናቀው ልጅ የክለቡ ክብረ ወሰን በሆነ ዋጋ አሁን ያለበትን ማንቼስተር ሲቲን ተቀላቀለ፡፡ በወቅቱ የስድስት ዓመታት ውልን ከክለቡ ጋር ሲፈራረም ለዝውውሩ የወጣበት ገንዘብ ደግሞ 55 ሚሊየን ፓውንድ ነበር፡፡

‹እንደቆሻሻ ጥላችሁኛል›

ኬቭን ደ ብሩይነ ህይወቱ የተቀየረበትን የመጀመሪያ ቅጽበት ያስታውሳል፡፡ ያኔ ገና ታዳጊ ነበር፡፡ የ14 ዓመት ልጅ እያለ ጌንክ የተባለውን የሃገሩን ክለብ ተቀላቀለ፡፡ ከመኖሪያ ከተማው ለቆ የወጣው ደ ብሩይነ በጊዜያዊነት ከሚያርፍበት ቤተሰብ ጋር መኖር ጀመረ፡፡ ነገር ግን ከአንድ ዓመት በኋላ ጊዜያዊ ቤተሰቦቹ አንፈልግህም አሉት፡፡

እናቱ ሁኔታውን ታስታውሳለች፡፡ ‹ሰዎቹ ልጄን ያልፈለጉት በባህሪው ምክንያት ነበር፤ ዝምተኛ ነው፤ ከማንም ጋር አይግባባም›› ትላለች፡፡

ኬቨን በጌንክ ክለብ የነበረውን ቆይታ ሲናገር ‹ለአንድ ሰዓት ወይም ከዚያ በላይ ለሚሆን ጊዜ ኳሷን ከአጥሩ ጋር እያጋጨሁ እጫወታለሁ፡፡ እናም አንዴ ድምጼን ከፍ አድርጌ እንዲህ አልኩ ‹ሁሉም ነገር ጥሩ ይሆናል፣ በሁለት ወራት ውስጥራሴን አሻሽዬ ለዋናው ቡድን መጫወት እጀምራለሁ፣ ምንም ነገር ቢከሰት ወደኋላ አላፈገፍግም፤ ሳይሳካልኝ ቀርቶ ወደቤቴ መመለስ አልፈልግም›

ለክለቡ ሁለተኛ ቡድን ተመርጦ መጫወት ከጀመረ በኋላ በአንድ ጨዋታ ከእረፍት በፊት ብቻ አምስት ግቦችን አስቆጠረ፡፡ ነገሮች ተቀየሩ፡፡ በፍጥነት ዋናውን ቡድን ተቀላቀለ፡፡

‹‹በእግር ኳስ ውስጥ ጥሩ መጫወት ስትጀምር ሰዎች ላንተ ያላቸው አመለካከትና የሚያደርጉልህ እንክብካቤ በፍጥነት ተቀይሮ ታየዋለህ፡፡ ይሄ በጣም ያስቀኛል›› ይላል ደ ብሩይነ፡፡

እነዚያ ባህሪው አስቸጋሪ ነው፣ ዝምተኛ ልጅ ነው ብለው ያባረሩት ጊዜያዊ ቤተሰቦች ወደዋናው ቡድን ማደጉን ሲሰሙ ‹እኛ ጋ መምጣትና መኖር ይችላል› አሉ፡፡

‹‹በጣም ጎድተውኛል፤ እኛ ጋ ተመልሰህ ና ሲሉኝ ‹ያኔ እንደ ቆሻሻ ጥላችሁኛል፤ አሁን ጥሩ ደረጃ ላይ መድረሴን ስታዩ ግን ፈለጋችሁኝ? አመሰግናለሁ፤ አሁን የናንተ እርዳታ አያስፈልገኝም› አልኳቸው፤ ያ ሁኔታ ለህይወቴ እንደ ነዳጅ አገልግሎኛል፤ ግን ያ የመገፋትና ያለመፈለግ ደመና እስከቅርብ ጊዜ ሲከተለኝ ነበር›› በማለት ደ ብሩይነ አስተያየቱን ያጠቃልላል፡፡

ኬቭን ደ ብሩይነ ማንቼስተር ሲቲን ከተቀላቀለበት ጊዜ አንስቶ በሁሉም ውድድሮች 165 ጨዋታዎችን አድርጎ 40 ጊዜ ኳስና መረብን አገናኝቷል፡፡

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትስስር ይፍጠሩ

325,851FansLike
49,039FollowersFollow
13,194SubscribersSubscribe