ኬፓ አሪዛባላጋ አነጋጋሪው የቼልሲ ግብ ጠባቂ

“ከዚህ በኋላ ኬፓ የቼልሲን ማልያ ለብሶ መጫወት የለበትም። ያደረገው ነገር ክብረ ነክ ነው፡፡ ተቀይሮ እንዲወጣ ሲጠየቅ ፍቃደኛ አለመሆኑ ለአሰልጣኙ ያለውን ንቀት ያሳያል። ለአንድ አሰልጣኝ ደግሞ ከዚህ በላይ ውርደት የለም፡፡ አሁን ከቼልሲ ቤት መባረር ያለበት አሰልጣኝ ማውሪዚዪ ሳሪ ሳይሆን ኬፓ አሪዛባላጋ ነው”

ይህን ያለው የቀድሞው የቼልሲ ተጫዋችና በአሁኑ ወቅት የእግር ኳስ ተንታኝ ሆኖ የሚሰራው ክሪስ ሰተን ነው፡፡ ሰተን እንዲህ አምርሮ ትችቱን የሰነዘረው ባሳለፍነው ሰኞ ነበር፡፡

በሊግ ካፕ የፍፃሜ ጨዋታ ቼልሲና ማንቼስተር ሲቲ ባደረጉት እልህ አስጨራሽ ፍልሚያ መካከል የተከሰተው የኬፓ አወዛጋቢ ድርጊት በተለያየ መንገድ መነጋገሪያ ርዕስ ሆኖ ቆይቷል፡፡ እስከ ጭማሪ ሰዓት የዘለቀው ጨዋታ ወደመለያ ምት ከመግባቱ አስቀድሞ የቼልሲው አሰልጣኝ ማሪዚዮ ሳሪ ግብ ጠባቂው ኬፓ አሪዛባላጋን ለመቀየር አስበው ትዕዛዝ ቢያስተላልፉም እሱ ግን አሻፈረኝ ብሏል።

ጨዋታው ወደ ፍጹም ቅጣት ምት ሲያመራ፣ አሰልጣኙ የፍጹም ቅጣት ምት ኳሶችን የማዳን ብቃቱን በ2016 ማንቸስተር ሲቲ ከሊቨርፑል ጋር ባደረጉት ጨዋታ ባዳናቸው ሦስት ኳሶች ብቃቱን ያስመሰከረውን የቀድሞው የማንቼስተር ሲቲ ግብ ጠባቂ ዊሊ ካባልሮን ለማስገባት ፈለጉ።

ሆኖም ኬፓ ቦታውን ለመልቀቅ ፈቃደኛ አልነበረም። አሰልጣኙ ቢጮሁ፣ እጃቸውን ቢያወናጭፉ ኬፓ የሚሰማ አልነበረም። ስለዚህም ኬፓ በግብ ጠባቂነቱ ቀጠለ። አሰልጣኙ ሳሪ በብስጭት ነደዱ።

በፍጹም ቅጣት ምቱ ኬፓ ማዳን የቻለው አንድ ኳስ ብቻ ነበረ። በደንብ ዝቅ ቢል መመለስ የሚችለውን ኳስ ሳያድን ቀርቶ ማንቼስተር ሲቲ ድል ተቀዳጀ። ዋንጫው ወደ ኢቲሃድ ተጓዘ፡፡

ከጨዋታው መጠናቀቅ በኋላ አሰልጣኙ ሁሉም ነገር የተፈጠረው ባለመግባባት ነው ሲሉ ተናግረዋል፡፡ በ71 ሚሊዮን ፓውንድ ከአትሌቲክ ቢልባኦ ቼልሲን የተቀላቀለው ኬፓ አሪዛባላጋ ባደረገው ነገር ይቅርታ የጠየቀ ሲሆን ክለቡም የአንድ ሳምንት ደመወዙን ቀጥቶታል፡፡ ገንዘቡ በክለቡ ስም ለተቋቋመው ፋውንዴሽን ገቢ ይሆናል፡፡ የ24 ዓመቱ ግብ ጠባቂ በሳምንት 190 ሺህ ፓውንድ እንደሚከፈለው ይታመናል፡፡

በስፖርቱ ዓለም የአሰልጣኛቸውን ትእዛዝ አልቀበልም ያሉ ሌሎችም ታዋቂ ስፖርተኞች አሉ።

Kumneger Media
Kumneger Media
Kumneger Media is a News and Entertainment Website & Channel. Kumneger Media in addition to News and Entertainment it is the hub of Politics, Movies, Drama, Music, Comedy, Documentary and More!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትስስር ይፍጠሩ

325,851FansLike
49,039FollowersFollow
13,194SubscribersSubscribe