ኮቢ ብሪያንት አሳዛኙ መጨረሻ

አሜሪካዊው የቅርጫት ኳስ ኮከብ ኮቢ ብራያንት ከሴት ልጁ ጋር ካሊፎርኒያ ግዛት ውስጥ ሲጓዝበት የነበረው ሄሊኮፕተር ተከስክሶ ከሌሎች ሰባት ሰዎች ጋር ህይወቱ ያለፈው በቅርቡ ነበር።
የ41 ዓመቱ ብራያንትና አብረውት የነበሩት ሰዎች ላይ አደጋው የደረሰው ሲጓዙበት የነበረው የግል ሄሊኮፕተር ከተከሰከሰ በኋላ በእሳት ተያይዞ ነው።
ዜናው ብዙዎችን አስደንግጧል፡፡ ከፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ እስከ ባራክ ኦባማ፣ ከእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንጃሚን ኔታንያሆ እስከ የቬንዙዌላው ፕሬዚዳንት ኒኮላስ ማዱሮ ድረስ በዜናው ተደናግጠው ሀዘናቸውንም ወዲያውኑ ገልጸዋል፡፡ ከሴት ልጁ ጋር ወደሳውዘንድ ኦክ ከተማ ሲጓዝ የነበረው ኮቢ ድንገተኛ ሞት እንደተነገረ በመላው አሜሪካ በሚካሄዱ የቅርጫት ኳስ ውድድሮች ላይ ለብርያንት የህሊና ጸሎት ተደርጎለታል።
በርካቶችም በብራያንት ድንገተኛ ሞት ድንጋጤያቸውን የገለጹ ሲሆን ታዋቂ ግለሰቦችም ሃዘናቸውን በተለያየ መንገድ ገልጸዋል፡፡
የአሜሪካ የቅርጫት ኳስ ውድድር የበላይ አካል የሆነው ኤንቢኤ የብራያንትን ሞት ተከትሎ ባወጣው መግለጫ ማህበሩ በስፖርተኛውና በ13 ዓመት ታዳጊ ልጁ ሞት የተሰማውን ሃዘን ገልጿል።
መግለጫው “ላለፉት 20 የውድድር ወቅቶች ኮቤ ተሰጥኦንና ለስፖርቱ ያለውን ሁሉ በማድረግ አሸናፊ መሆን እንደሚቻል አሳይቷል” ሲል ብራያንትን አስታውሶታል።
ስኬት
ብራያንት ለታዋቂው ሎስ አንጀለስ ሌከርስ የቅርጫት ኳስ ቡድን በመጫወት አምስት ጊዜ ሻምፒዮን ለመሆን በመቻሉ በውድድሩ ታሪክ ውስጥም ታላላቅ ከሚባሉ ተጫዋቾች መካከል የሚጠቀስ ስፖርተኛ ነበር።
ብራያንት ለ20 ዓመታት በዘለቀው የቅርጫት ኳስ ህይወቱ የተጫወተው ሎስ አንጀለስ ሌከርስ ለተባለው ቡድን ብቻ የነበረ ሲሆን ከአራት ዓመት በፊት መጫወት አቁሟል።
በተለያዩ ጊዜያት በቅርጫት ኳስ ውድድር ባሳየው ችሎታው የኮከብነት ሽልማቶችን ያገኘ ሲሆን ሁለት ጊዜ በኦሊምፒክ ላይ ተሳትፎ የአሸናፊነትን ክብር ተጋርቷል።
ኮቢ ብራይንት እ.ኤ.አ በ1978 በፊላዴልፊያ የተወለደ ሲሆን ወላጅ አባቱ ጆኢ ብራይንት የቅርጫት ኳስ ተጫዋች ነበር። ኮቢ ማለት በጃፓን ተወዳጅ የስጋ ምግብ ነው። ይህም የቅርጫት ኳስ ፈርጥ ስሙን ከዚሁ አግኝቷል። 1 ሜትር ከ98 ሴንቲ ሜትር የሚረዝው ኮቢ ብራያንት 96 ኪሎ ግራም ይመዝናል። የ41 ዓመቱ ኮቢ አምስት ጊዜ የኤን ቢ ኤ ቻምፒዮን በመሆን በቅርጫት ኳስ ታሪክ ትልቅ ስምና ዝና ማትረፍ ችሏል። በ 20 ዓመት የቅርጫት ኳስ ፕሮፌሽናል ህይወቱ አያሌ ክብሮችን የጨበጠው ኮቢ ሁለት ጊዜ የኦሊምፒክ ቻምፒወን ሲሆን በ 2008 በመድረኩ ውዱ ተጫዋች መሆን ከመቻሉም በተጨማሪ 2006 ላይ ከቶሮንቶ ራፕቶርስ ጋር በገጠመበት ጨዋታ 81 ቅርጫቶችን በማስቆጠር 2ኛው የምንጊዜም ከፍተኛ ቅርጫት አስቆጣሪ ሆኖ በታሪክ ተመዝግቧል።
የሀብት መጠኑ እስከ 650 ሚሊየን ዶላር የሚገመተው ኮቢ ብራያንት ለበርካታ ክዋክብት ስፖርተኞች እውነተኛ አርዓያ በመሆን መነሳሳትን የፈጠረ ታሪክ አኑሮ በካሊፎርንያ በደረሰው የሄሊኮፕተር መከስከስ አደጋ በ 41 ዓመቱ ህይወቱ አልፏል። ሁነቱን አስከፊ የሚያደርገው ደግሞ በአደጋው ወደፊት የአባቷን ሌጋሲ ለማስቀጠል ተስፋ የተጣለባት የ 13 ዓመቷ ጂያና ብራያንት ከአባቷ ጋር ህይወቷ ማለፉ ነው። ሌሎች ሰባት ሰዎችም በአደጋው ህይወታቸው አልፏል። የ 13 ዓመቷ ታዳጊ ጂያና ለመምባ ስፖርትስ አካዳሚ እየተጫወተች የምትገኝ ሲሆን በታሪካዊው የቅርጫት ኳስ ባለሟል በሆነው አባቷ እየሰለጠነች ጨዋታዋን ለማከናወን አገር አማን ብላ እየበረረች ባለበት ሰዓት ያልታሰበውና የሚሊዮኖችን ልብ የሰበረው የእርሷንና አባቷን ህይወት የቀጠፈው መሪር አደጋ ተከሰተ። ከ 4ቱ ልጆች 2ኛ የሆነችው ጂያና ፈጣን ፣ ቀልጣፋና ለቅርጫት ኳስ ጥልቅ ፍቅር የነበራት ሲሆን ከአባቷ የወረስችው እምቅ የክህሎት ሀብት ወደፊት የአባቷን ሌጋሲ ከማስቀጠልም ባለፈ ለቅርጫት ኳሱ አዲስ አብዮት እንደምታመጣ በርካቶች አመኔታ ጥለውባት ነበር።
ብራያንት ከሁለት ዓመት በፊት ‘ዲር ባስኬትቦል’ በሚል ለቅርጫት ኳስ ስፖርት ያለውን ፍቅር በሚያሳየውና በእራሱ በተጻፈው አጭር ፊልም የኦስካር ሽልማትን ለማግኘት ችሎ ነበር።
ኮቢ ብራያንት በአደጋው አብራው ህይወቷ ካለፈው ሴት ልጁ በተጨማሪ የሌሎች ሦስት ሴት ልጆች አባት ነው።
ልቤ ተሰብሯል
ባለቤቷና ልጇ አሰቃቂ በተባለው የሄሊኮፕተር አደጋ መሞት ተከትሎ ስሜቷን ለመግለጽ ተቸግራ የቆየችው የኮቢ ብሪያንት ባለቤት ቫኔሳ ለመጀመሪያ ጊዜ ስሜትዋን ያጋራችው በቅርቡ ነው፡፡ “ልቤ ተሰብሯል፤ የሚሰማኝን ሃዘንና ህመም ሊገልፅልኝ የሚችል ቃል አይገኝም” ብላለች።
በኢንስታግራም ገጿ ላይ የቤተሰባቸውን ፎቶ በመለጠፍ ሐዘኗን የገለፀችው ቫኔሳ “ድንቅ አባትና አፍቃሪ ባሌን እንዲህ ድንገተኛ በሆነ ሁኔታ በማጣቴ ሐዘኔ ጥልቅ ነው። አሳቢ፣ ቆንጆ፣ ትሁትና ግሩም የሆነ ባህርይ የነበራትን ልጄን ማጣቴ ደግሞ ሃዘኔ ድርብ እጥፍ ያደርገዋል” ብላለች።
አክላም “ለዘላለም አብረውን ቢኖሩ ምኞቴ ነበር። በአጭሩ ተቀጩ፤ እኔም ምርቃቶቼን ተነጠቅኩኝ። ህይወትን ያለነሱ ማሰብ አዳጋች ነው። የነገውን ሳስብ ይጨልምብኛል፤ ያስፈራኛል።”
ኮቢና ቫኔሳ በአደጋው የሞተችውን የአስራ ሦስት ዓመቷን ጂያናን ጨምሮ አራት ልጆችን አፍርተዋል።
ጭጋጋማ በነበረው የአየር ጠባይ በምዕራብ ሎስ አንጀለስ የተከሰተው የሄሊኮፕተር አደጋ ሲከሰት ኮቢ የልጁን ቅርጫት ኳስ ቡድን ለማሰልጠን ወደ ማምባ ስፖርት አካዳሚ እያቀና ነበር ።
አድናቂዎቹ በዚህ ፈታኝ ወቅት ላሳዩት ድጋፍ ያመሰገነችው ቫኔሳ በአደጋው ህይወታቸውን ያጡትን ለመዘከር እንዲሁም ቤተሰቦቻቸውን ለመደገፍ ማምባ ስፖርት የሚባል ድርጅት እንደሚመሰረት ገልፃለች።
በአደጋው ኮቢና ልጁን ጨምሮ፣ ፓይለቱ፣ ሁለት የአስራ ሦስት ዓመት እድሜ ያላቸው የቅርጫት ኳስ ተጫዋቾች፣ ሦስት ወላጆችና አሰልጣኙ ህይወታቸው አልፏል።
በቅርጫት ኳሱም ሆነ በስፖርቱ ዓለም ስመ ገናና የነበረው ኮቢ ክለቡን ሎስ አንጀለስ ሌከርስን አምስት ጊዜ የሻምፒዮንነት ስፍራን ያስጨበጠና ሁለት ጊዜም የኦሊምፒክ ወርቅ ሜዳሊያን ማሸነፍ ችሏል።

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትስስር ይፍጠሩ

325,851FansLike
49,039FollowersFollow
13,194SubscribersSubscribe