‹‹ዮጋ ሰውነትን የማሳሳብ ልምምድ ብቻ ሳይሆን የሕይወት ፍልስፍናም ነው››
ከ80 በላይ መጽሐፍትን ለንባብ ያበቁት ታዋቂው የዮጋ መምህር ስዋሚ ሳትያናንዳ ሳራስዋቲ ‹‹ዮጋ በዝንጋታችን ውስጥ የተቀበረ ጥንታዊ አፈታሪክ አይደለም፤ ይልቅስ ዛሬም ድረስ በዘረመላችን ውስጥ ያለና ዋጋው የበዛ ጥበብ ነው፤ አሁን በእጅጉ ያስፈልገናል፣ ነገ ደግሞ ባህላችን ይሆናል›› ብለው ነበር፡፡ እንዳሉትም ባህል ሆኗል፡፡ በዚህ ወቅት ዓለም ላይ 300 ሚሊዮን ሰዎች ዮጋን እንደሚሰሩ ይገመታል፡፡ በአሜሪካ ብቻ ደግሞ ከ36 ሚሊዮን በላይ ሰዎች ዮጋን የህይወት ዘይቤያቸው አካል አድርገውታል፡፡
የዮጋ ጽንሰ ሀሳብ በኢትዮጵያ ከተዋወቀ ረዘም ያለ ጊዜ ያስቆጠረ ቢሆንም በዚያው ልክ እየተዘወተረ ነው ለማለት ግን ይከብዳል፡፡ በእርግጥ ከቀደሙት ዓመታት ሲነጻጸር ለውጥ አለ ማለት እንችላለን፡፡ በጣት የሚቆጠሩም ቢሆኑ ዓለም አቀፍ ስልጠናዎችን የተከታተሉ የዮጋ መምህራን በተለያዩ ስፖርት ማዘውተርያዎችና በግል ስልጠናዎችን እየሰጡ ነው፡፡
<45 ከመቶ መራጮች የመረጃ ምንጫቸው ቴሌቪዥን መሆኑን አንድ ጥናት አመለከተ …>
ከነዚህ ጥቂት የዮጋ መምህራን መካከል አንዷ ሜሮን ማሪዮ ናት፡፡ ኢንተርናሽናል ዮጋ ኢንስትራክተር የሆነችው ሜሮን ከሀገር ውስጥ በተጨማሪ በኬንያና በህንድ የዮጋ ትምህርቶችን በከፍተኛ ደረጃ በመከታተል በስኬት ጨርሳለች፡፡
ከህንዱ S-VYASA Yoga University አለም አቀፍ ስልጠናዋን ካጠናቀቀች በኋላ በሀገር ውስጥ በተለያዩ የማሰልጠኛ ተቋማትና በግል ስልጠና በመስጠት ትውልድን የመቅረጽ ስራ እየሰራች ነው፡፡ በተለያዩ ማረሚያ ቤቶች ለሚገኙ ታራሚዎች በስፍራው በመገኘት የዮጋ ስልጠና ከመስጠት ባለፈ ቪዲዮዎችን በማዘጋጀት በእሱ ታግዘው ሁሌም ዮጋን እንዲሰሩ በማመቻቸት ማህበራዊ ሀላፊነቷን እየተወጣች ነው፡፡ በሚሊኒዬም አዳራሽ የኮቪድ – 19 ጽኑ ህሙማንን በማከም ላይ የሚገኙ ባለሙያዎችን በሳምንት ለሶስት ቀናት ዮጋ በማሰራት ከሚፈጠርባቸው መረበሽና ጭንቀት እንዲላቀቁ የበኩሏን ድርሻ ስታበረክት ቆይታለች፡፡ ‹ዮጋ ለኔ ጓደኛዬ፣ ሚስጥረኛዬ እና የመንፈሴ ፈዋሽ ነው› የምትለው ዓለም አቀፍ ዮጋ ኢንስትራክተር ሜሮን ማሪዮ ከቁም ነገር መጽሔት ጋር ተከታዩን ቃለ ምልልስ አድርጋለች፡፡
ቁም ነገር፡- ከዮጋ ጋር እንዴት ተዋወቅሽ? ለኢትዮጵያውያን ሩቅ የሆነ ጥበብ ይመስለኛል…
ሜሮን፡- ስለ ዮጋ ብዙም እውቀት አልነበረኝም፡፡ ከዮጋ ጋር ለመጀመሪያ ጊዜ እንድትዋወቅ ያደረገኝ ዓለም አቀፍ የዮጋ ኢንስትራክተር የሆነው ዮፍታሔ ማንያዘዋል ነው፡፡ አጋጣሚው ሕይወቴን ቀይሮታል፡፡ ዮጋ መማር ጀመርኩ፡፡ ሁሉም ነገር በፍጥነት ተቀየረ፡፡ ያለማቋረጥ የማደርገው የዮጋ ልምምድ አዕምሯዊ፣ አካላዊና መንፈሳዊ ብቃቴን አሳደገው፡፡
እንደ ዕድል ሆኖ ደግሞ ኬንያ ከሚገኘው አፍሪካ ዮጋ ፕሮጀክት የትምህርት ዕድል አገኘሁ፡፡ በወቅቱ ከኢትዮጵያ ይህንን ዕድል ማግኘት የቻልኩት እኔ ብቻ ነበርኩ፡፡ ሕይወቴን ከቀየሩት ገጠመኞች መካከል አንዱ ሆነ፡፡ በዚያም ለ200 ሰዓታት የዘለቀ የተግባር እና የቲወሪ ትምህርት ተከታትያለሁ፡፡ ከመመረቄ አስቀድሞም ወደኢትዮጵያ በመምጣት በአዲስ አበባ ከተማ ልደታ አካባቢ በሚገኘው የወጣት ጥፋተኞች ማረሚያ ማዕከል የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ሰጥቻለሁ፡፡
<ይልቅ ወሬ ልንገርህ:- ስለ ታማኝ በየነ ‹ሿ ሿ›>
ሌላኛው ህይወቴን የቀየረ አጋጣሚ የተፈጠረው ደግሞ ከስድስት ዓመታት በፊት ነበር፡፡ ዮጋን በዩኒቨርስቲ ደረጃ ተምሬ ዓለም አቀፍ ኢንስትራክተር የምሆንበትን የትምህርት ዕድል አገኘው፡፡ የዮጋ መፈጠሪያ ምድር በሆነችው ህንድ ወደሚገኘው S-VYASA Yoga University ገብቼ ተማርኩ፡፡ ከዚያም ዓለም አቀፍ የዮጋ ኢንስትራክተር ሆኜ ወደ ሀገሬ ተመለስኩ፡፡
ዮጋ የሕይወቴ አካል ከሆነ ከሰባት ዓመታት በላይ ተቆጥሯል፡፡ ከዚያ ጊዜ ጀምሮ አሁንም ድረስ ዮጋን አስተምራለሁ፤ በኔ ሕይወት ውስጥ የፈጠረውን ለውጥ ለሌሎች አጋራለሁ፡፡
ቁም ነገር፡- ዮጋን መስራትሽ እንጀራ ከመሆን ባለፈ ምን ጠቀመሽ?
ሜሮን፡- እንደ አንድ የዮጋ ኢንስትራክተር፣ ዮጋ በማስተምራቸው ሰዎች ላይ ብቻ ሳይሆን በኔ ሕይወት ላይም ያመጣቸውን አስደማሚ ለውጦች ወደኋላ መለስ እያልኩ ለመመርመር እሞክራለሁ፡፡ በአካላዊ፣ አዕምሯዊና መንፈሳዊ ደህንነቴ ላይ የተጫወተው ሚና ከፍተኛ ነው፡፡ ከቤተሰቦቼና ጓደኞቼ ባሻገር ዮጋ ሁሌም የማይለየኝና በሀይል የሚሞላኝ የሕይወቴ አንድ አካል ነው፡፡
ውጣ ውረዶችንና የሕይወትን ውጥረቶች አልፌበታለሁ፤ ከስብራቴ አገግሜበታለሁ፡፡ ሚዛናዊ የሕይወት ዘይቤ እንዲኖረኝ ረድቶኛል፡፡ ከፀሀይ በታች ያሉ ሁሉንም ስሜቶች የማራግፍበት፣ ለቅሶዬን፣ ወዜን፣ ጩኸቴን፣ ሳቄን፣ እያንዳንዱን ስሜቴን ይዤ የምወድቅበት ምቹ ምንጣፍ ሰጥቶኛል፡፡ ከምንጣፉ ስነሳ ሁሌም አዲስ ሰው ሆኜ ነው፡፡ ዮጋ ለኔ ጓደኛዬ፣ ሚስጥረኛዬ እና የመንፈሴ ፈዋሽ ነው፡፡ በቀላል ቋንቋ ዮጋ ሕይወቴን ቀይሮታል፡፡
ቁም ነገር፡- ዮጋ ምንድነው? እንዴት ነው የምትገልጭው? ሳይንሱን ንገሪን እስኪ?
ሜሮን፡- ዮጋ ከዕለት ተዕለት ሕይወታችን ጋር ሊቆራኝ የሚገባው የትክክለኛ አኗኗር ሳይንስ ነው፡፡ በአንድ ግለሰብ ሁሉንም አቀፍ ስብዕና ላይ ማለትም በአካሉ፣ በአዕምሮው፣ በንቃቱ፣ በስሜቱና በመንፈሳዊ ሁለንተናው ላይ ለውጥ ይፈጥራል፡፡ ዮጋ ማለት አንድነት (Unity) ወይም አንድ መሆን (Oneness) ማለት ነው፡፡ በመንፈሳዊ መንገድ ስንመለከተው ደግሞ ግለሰባዊ ንቃት (self consciousnesss) ከመላው ዓለም ንቃት (Universal consciousness) ጋር ሲዋሀድ እንደማለት ነው፡፡የአካል፣ የአዕምሮና የስሜት መጣጣምና ህብር መፍጠር ዮጋ ይባላል፡፡ ነገሩን በተሻለ ሁኔታ ለመረዳት ይመች ዘንድ በምሳሌ እንመልከተው፡፡
አንድ ሰው ዮጋን መስራት ሲጀምር ሙሉ ትኩረቱ የሚሆነው አካሉ ላይ ብቻ ነው፡፡ በዚህ ምክንያት ሚዛኑን ለመጠበቅ ይቸገራል፡፡ ምክንያቱም የውስጥ አካላቶቻችን፣ ጡንቻዎቻችን እና ነርቮቻችን በህብር መንቀሳቀስ አይችሉም፡፡ እንዲያውም እንቅስቃሴያቸው አንዱ ሌላውን በሚቃረን መልኩ ይሆናል፡፡ የዮጋ አላማው እነዚህን የተለያየ ጥቅም ያላቸው የሰውነት ክፍሎች አንድ ላይ ተጣምረው የተሳካ ስራን እንዲያከናውኑ ማድረግ ነው፡፡ ዮጋ ከዚህ ይነሳና ወደ አዕምሯዊና ስሜታዊ ደረጃ ከፍ ይላል፡፡
ቁም ነገር፡- እንደምታውቂው አሁን ዓለም ትርምስ ውስጥ ነው ያለው፤ የተረጋጋ ነገር አይታይም፤ ይህ ደግሞ በሰዎች ላይ ጭንቀት ይፈጥራል፤ ከዚህ አንጻርስ ዮጋ ምን አይነት ጥቅም ይሰጣል?
ሜሮን፡- ሰዎች በየዕለት የሕይወት መስተጋብር ውስጥ በሚያጋጥማቸው የተለያየ ነገር ሳቢያ ለጭንቀት እና ለፍርሃት ብሎም ለአዕምሮ መቃወስ ሊጋለጡ ይችላሉ፡፡ ዮጋ ለዚህ ፈውስ ባይሰጥም ሁኔታዎቹን መቋቋም የምንችልባቸው እርግጠኛ የሆኑ ዘዴዎችን እንድናዳብር ይረዳናል፡፡
ዮጋ ሰውነትን የማሳሳብ ልምምድ ብቻ ሳይሆን የሕይወት ፍልስፍናም ነው፡፡ ሰዎች የተረጋጋ አዕምሯቸውን ተጠቅመው ያላቸውን ኃይል በአካላቸው ላይ እንዴት መግለጥ እንደሚችሉ ያስተምራቸዋል፡፡ የመፈወስ ጥበቡ ደግሞ የትኛውንም አይነት ሰው ተጠቃሚ ያደርገዋል፡፡ የዕድሜ፣ የእምነት፣ የሀብትና የአካላዊ ብቃት ገደብ የለውም፡፡ ውጤቱም ከአወንታዊነት ሀሳብ ተነስቶ በዐይን እስከሚታይ አካላዊ ለውጥ ድረስ የዘለቀ ነው፡፡
<በአማራ ህዝብ ላይ እየደረሰ ያለውን ግድያ እና መፈናቀል የሚያወግዙ ሰልፎች ተካሄዱ>
እነዚህ የፈውስ ጥበቦች በተለይ በብርሃን ፍጥነት እየተምዘገዘገ ባለው በዚህ የዘመናዊ ዓለም ሕይወት ውስጥ በእጅጉ ያስፈልጋሉ፡፡ ፍላጎቶች በበዙበት አሁን ባለንበት የግርግር ዓለም ዮጋ መዝናናትን የምናገኝበት የማስታገሻ መድሃኒት ነው፡፡ የተረበሸውን የሕይወት ዘይቤ ሚዛኑን እንዲጠብቅ ያደርግልናል፡፡ ለአዕምሮ ዝምታን በመስጠት ሰዎች እንዲረጋጉና ከሚኖሩበት እያንዳንዱ ቅጽበት ጋር ተግባብተው እንዲጓዙ ይረዳቸዋል፡፡
ቁም ነገር፡- ዮጋ ከሌሎቹ የአካል ብቃት እንቅስቃሴዎች በምንድነው የሚለየው? ከሐይማኖት ጋር የሚያይዙትም አሉ…
ሜሮን፡- አንዳንድ ሰዎች ዮጋን ከአካል ብቃት እንቅስቃሴ ጋር ያምታቱታል፡፡ አንዳንዶች ደግሞ እንደ ሐይማኖታዊ ተግባር የሚቆጥሩትም አሉ፡፡ በነዚህ ምክንያቶች የዮጋ ጽንሰ ሀሳብ ግራ በተጋቡ ምስሎች እንዲሞላ ሆኗል፡፡
ዮጋ ሳይንስ ነው፡፡ በተግባር የሚገለጥ፣ የአሠራር ዘዴዎች ያሉትና ስልታዊ ዲስፕሊኖች ወይም ቴክኒኮች ተጠቅሞ ሰዎች ጥልቁን ተፈጥሯቸውን እንዲረዱ የሚያስችል ሳይንስ ነው፡፡ ጥልቁን ተፈጥሯችንን ለመረዳት የሚደረግ ተግባር ሀይማኖታዊ ሊሆን አይችልም፡፡ ይልቅስ ራስን ለማጥናት የሚደረግ ሳይንሳዊ ምርምር ነው፡፡
ዮጋ ከየትኛውም ሀይማኖት ጋር አይጋጭም፤ በየትኛውም እምነት ውስጥ ጣልቃ አይገባም፡፡ ሀይማኖት የለኝም የሚል ሰውም ይሁን የአንድ ሀይማኖት ጥልቅ አማኝ ዮጋን ከመስራት የሚያግዳቸው ነገር የለም፡፡
ቁም ነገር፡- ዮጋ የሚሰጣቸው የጤና በረከቶች ብዙ እንደሆኑም ይታወቃል፤ እስኪ የተወሰኑትን እናንሳ?
ሜሮን፡- ለአካል እና ለአእምሮ ፈውስ መስጠቱ ከዮጋ ዋና በረከቶች መካከል አንዱ ነው፡፡ እንደ አስም ፣ የስኳር በሽታ ፣ የደም ግፊት፣ የምግብ መፈጨት ችግር እና ሌሎች ሥር የሰደደ በሽታ ያለባቸውና በዘመናዊ ሳይንስ መፍትሔ ላጡ ህመሞች ዮጋ እንደ አማራጭ ህክምና ሆኖ ይተካል፡፡ የህክምና ጠበብት እንደሚናገሩት የዮጋ ልምምድ በስርዓተ ነርቭ እና በስርዓተ ዝግ እጢ መካከል ሚዛን እንዲጠበቅ የማድረግ አቅም አለው፡፡ ይህም በሌሎች ስርዓቶችና የውስጥ አካል ክፍሎች ላይ ቀጥተኛ ተጽዕኖ ያሳድራል፡፡
ለአብዛኞቹ ሰዎች ደግሞ ዮጋ ማለት ጭንቀት በሞላበት በዚህ ወቅት ጤንነትን እና ደህንነትን ጠብቆ ለመዝለቅ የሚያገለግል ዋና ዘዴ ነው፡፡ በቢሮ ውስጥ ወንበር ላይ ተቀምጦ ሙሉ ቀን ለሚያሳልፍ የዚህ ዘመን ሠው የተከማቸውን አካላዊ ድካምና ምቾት ማጣትን ያስወግዳል፡፡
ቁም ነገር፡- ዮጋ በኢትዮጵያውያን ዘንድ የሕይወት ዘይቤ እንዲሆን በአንች በኩል ምን እያደረግሽ ነው?
ሜሮን፡- በአሁኑ ወቅት ዮጋን በተለያዩ ቦታዎች ከማስተማርም በተጨማሪ መጽሐፍም እያዘጋጀሁ ነው፡፡ ይህንን መጽሐፍ ለማዘጋጀት ስነሳ ከላይ የዘረዘርኩልህ የዮጋ በረከቶች ለሰው ልጆች ሁሉ የሚገቡ መሰረታዊ ነገሮች ናቸው ከሚል እምነት በመነጨ ነው፡፡ እንደምታውቀው በውጭ አገራት ቋንቋዎች የተጻፉና ዮጋን የሚያስተምሩ መጽሀፍት በብዛት አሉ፡፡ ይሁን እንጂ በአማርኛ ቋንቋ በቀላሉ የተዘጋጁና ሰዎች በቤታቸው ወይም በሚመቻቸው ቦታ ያለ ኢንስትራክተር ዮጋን እንዲለማመዱ የሚያደርጉ መጽሐፍት ግን በበቂ ሁኔታ የሉም፡፡ ኢንተርናሽናል የዮጋ ኢንስትራክተር ከሆንኩ በኋላ ስልጠና በሰጠሁባቸው ያለፉት ስድስትና ሰባት ዓመታት ውስጥ በተደጋጋሚ ከሚቀርቡልኝ ጥያቄዎች መካከልም ዋነኛው ‹‹ለምን መጽሐፍ አታዘጋጂልንም?›› የሚለው መሆኑ ይህንን ያሳያል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ በዩቲዩብና በሶሻል ሚዲያው በኩል የምችለውን እያደረኩ ነው፡፡ ሰዎች በቀላሉ የሚሰሩበት የዮጋ ሲዲም እያዘጋጀሁ ነው፡፡
ቁም ነገር፡- አመሰግናለሁ፡፡