ዜሮ ዓመት የሥራ ልምድና ጋዜጠኝነት

‹‹በቅድሚያ ደራሲ ከበደ አበራ ይህንን ቃለ መጠይቅ ለመስጠት ፈቀደኛ በመሆንዎ  በእኔና በጣቢያው ስም አመሰግናለሁ›› አልኩ፡፡

እሳቸው ግን ፈገግ ብለው ‹‹ምሥጋናህን ተቀብያለሁ፡፡ ስሜ ግን  ከበደ አበራ ሳይሆን  አበራ ከበደ ነው›› አሉኝ፡፡ ይህንኑ በማስታወሻ ደብተሬ ላይ አስፍሬ ተከታዩን ጥያቄ ወረወርኩ የተወለዱት አምቦ ነው? ወደ አዲስ አበባ የመጡት መቼ ነው? ስላቸው ‹‹ድጋሚ ላርምህ፣ የተወለድኩት አምቦ ሳይሆን ጅሩ ነው፣ ወደ አዲስ አበባ የመጣሁት….›› ብለው ቀጠሉ፡፡

ምላሻቸውን ሲጨርሱ ልጅነት የተሰኘውን የመጀመሪያ መፅሐፍዎን ያሳተሙት በስንት ሺሕ ኮፒ ነው?›› የሚል ጥያቄ ሰነዘርኩ፡፡ ደራሲው አሁንም ምላሻቸውን በማረሚያ ነው የጀመሩት፡፡ «የመጀመሪያ መጽሐፌ ርዕስ ‹‹ልጅነት›› ሳይሆን ‹‹የሌሊቱ ሲሳይ›› ነው፡፡ ‹‹ልጅነት›› ሦስተኛ መጽሐፌ ነው፡፡ የሆነ ሆኖ የልጅነት የኅትመት ብዛት…››

ለደራሲው ጥያቄ ካቀረብኩ በኋላ የሚሉትን አልሰማም፡፡ ልክ ሲጨርሱ ጠብቄ ሌላ ጥያቄ ብቻ ነበር የምወረውረው፡፡ አሁንም ዝም ሲሉ መልሳቸውን እንደጨረሱ በመገመት ‹‹በአንድ ወቅት ሲናገሩ ወጣቶች ደራሲ ለመሆን ከፈለጉ ቢያንስ 2000 መጻሕፍትን ማንበብ አለባቸው ብለው ነበር፡፡ ለመሆኑ እርስዎ ስንት መፅሐፍ አንብበዋል?›› አልኳቸው፡፡

የደራሲው ትዕግስተኝነትና እርጋታ ዛሬ ድረስ ይታወሰኛል፡፡ ለአራተኛው ጥያቄ የሰጡኝን ምላሽ የጀመሩት አሁንም በማስተካከያ ሐሳብ ነው፡፡ ‹‹አሁን የጠቀስከውን ሐሳብ የተናገርኩት እኔ ሳልሆን ደራሲ ከበደ ሚካኤል ናቸው፡፡ እኔ ‹ከበደ ሚካኤል እንዲህ ይላሉ› ብዬ ነው የጠቀስኩት፡፡ የሆነ ሆኖ እኔ እስከዛሬ ምን ያህል መጽሐፍ እንዳነበብኩ በቁጥር አላውቀውም፡፡ ግምትህን ንገረኝ ካልከኝ ግን…›› አሉኝ።

ከዚህ ጥያቄ በኋላ «አመሰግናለሁ» ልላቸው ፈልጌ ነበር፡፡ ነገር ግን የማስታወሻ ደብተሬን ስመለከተው አንድ ጥያቄ ብቻ ነው የቀረኝ:: ከመጣሁ አይቀር ለምንድነው ጥያቄዎቼን ጨርሼ የማልሄደው ብዬ «የመጨረሻው ጥያቄዬ ደግሞ ብዙ ሰዎች የድርሰት ሥራን መተዳደሪያ ማድረግ አይቻልም ይላሉ፡፡ እርስዎ ደግሞ ከድርሰት ውጪ ሌላ ሥራ አይሠሩም፡፡ ከዚህ አንፃር በድርሰት ሥራ መተዳደር አይቻልም ለሚሉ ሰዎች ምን መልዕከት ያስተላልፋሉ?›› አልኳቸው፡፡

‹‹በመጀመሪያ ደረጃ በድርሰት ሥራ ብቻ ኢትዮጵያ ውስጥ መኖር ይቻላል የሚል እምነት የለኝም፡፡ ስለዚህ በማላምንበት ነገር ላይ መልዕከት ለማስተላለፍ አልችልም፡፡ ከድርሰት ሥራ ሌላ ተጨማሪ ሥራ ለምን አትሠራም? ለማለት ፈልገህ ከሆነ መልሴ የሚቀጥረኝ አላገኘሁም ነው፡፡›› አሉኝ፡፡

የቀረኝ አመስግኜ መሰነባበት ብቻ ነው፡፡ ‹‹ደራሲ አበራ ከበደ ይህንን ቃለ መጠይቅ እዚህ ስቱዲዮአችን ድረስ መጥተው ስለሰጡን በድጋሚ አመሰግናሁ›› አልኩ፡፡

ደራሲው አሁንም የሚያርሙኝ ነገር አላጡም ‹‹ቃለ መጠይቁን ያደረግነው እዚሁ እኔ መኖሪያ ቤት እንጂ ሬዲዮ ጣቢያው ስቱዲዮ ውስጥ አይደለም፡፡ ለማንኛውም ግን እኔም አመሰግናለሁ›› አለኝ፡፡

አለቃዬ የሠራሁት ቃለ መጠይቅ ቢሰሙ ምን ሊሉኝ እንደሚችሉ እያሰብኩ ነበር መሥሪያ ቤት የደረስኩት፡፡ ቢሮ ገብቼ እንዴት አድርጌ መግቢያ እንደምዕፍ መጨነቅ ጀመርኩ፡፡ ለመግቢያ የሚሆን ሐሳብ ከቃለ መጠይቃቸው ውስጥ አገኝ ይሆን? ብዬ ቴፑን ስከፍተውና አለቃዬ በሩን ከፍተው ሲገቡ አንድ ሆነ፡፡

አለቃዬ ያደረኩትን ቃለ መጠይቅ ከሰሙ በኋላ ‹‹ቃለ መጠይቅ እንዴት እንደሚሠራ ጥሩ ምሳሌ በመሆኑ ጀማሪ ጋዜጠኞችን ለማስተማሪያነት ይውላል›› ብለው ካሴቱን ይዘው ወጡ፡፡

ታሪኩ ‹‹ዜሮ ዓመት የሥራ ልምድና ሌሎች ወጎች›› ከሚለው የአጭር ልብ ወለድ መጽሐፍ ስብስብ በገጽ ሁለት ‹‹ሽልማት›› በሚል ርዕስ ከሰፈረው ተቀንጭቦ የተወሰደ ነው፡፡

የመጽሐፉ ደራሲ ጋዜጠኛ ታምራት ኃይሉ ሲሆን መጽሐፉ ሰኞ ግንቦት 26 ቀን 2016 ዓ.ም. በርካታ የሙያ አጋሮቹና ታዳሚያን በተገኙበት በጊዮን ሆቴል ተመርቋል፡፡

በ131 ገጾች ተቀንብቦ የመጽሓፉ ርዕስ ሆኖ ከቀረበው ‹‹ዜሮ ዓመት የሥራ ልምድና ሌሎች ወጎች›› ከሚለው ጋር 20 አጫጭር ልብ ወለዶችን የያዘ ሲሆን፣ መታሰቢያነቱ ለእናቱ ለወ/ሮ በለጡ ሄይ (እማሆይ ወለተ ትንሳዔ) መሆኑን ጸሐፊው በምረቃ ሥነ ሥርዓቱ ወቅት ተናግVል፡፡

ከ20 ዓመታት በላይ በጋዜጠኝነት ሙያ ያሳለፈው ታምራት በነበረበት የሙያ ዘርፍ የነበሩትን ውጣ ውረዶች፣ ልምዶችና ተሞክሮዎች መነሻ በማድረግ መጽሐፉ የብዙ ዓመታት የሐሳብ ስብስቦች ውጤት መሆኑን ጠቁሟል፡፡

የቁም ነገር መጽሔት አሳታሚና ዋና አዘጋጅ የሆነው ታምራት ‹‹ተማር ታውቃለህ፣ ሞክር  ትችላለህ›› የሚል መርህ እንዳለው በቅርብ የሚያውቁት ይመሰክራሉ፡፡

የኅትመት ዋጋ መናር ስብስቦቹ በወቅቱ በመጽሐፍ መልክ እንዳይዘጋጁ አድርጎት እንደቆየ የተነገረ ሲሆን በመጨረሻም ‹‹የ50 ሎሚ ዘመቻ›› በሚል በማኅበራዊ ሚዲያ በተደረገ የቅድመ ህትመት ግዥ ዘመቻ ለኅትመት እንደበቃ ዘመቻውን ያስጀመረውና ያስተባበረው አቶ ቴዎድሮስ ተክለ አረጋይ ተናግሯል፡፡

በማኅበራዊ ሚዲያ በተሰባሰበ ገንዘብ ለኅትመት የበቃው መጽሐፍ በ275 ብር ዋጋ ለአንባቢያን የቀረበ ሲሆን፣ በርካታ የኪነ ጥበብ አፍቃሪዎች፣ የደራሲው የሙያ አጋሮችና ሌሎች የማኅበረሰብ ክፍሎች በማኅበራዊ ዘመቻው በመሳተፍ መጽሐፉን አስቀድመው መግዛታቸው ታውቋል፡፡

SourceReporter

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትስስር ይፍጠሩ

325,851FansLike
49,039FollowersFollow
13,194SubscribersSubscribe