የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የምግብ እና መድኃኒት ባለሥልጣን የ’ስፔሻላይዝድ’ እና ‘ኮምፕሪሄንሲቭ’ ሆስፒታሎች አዲስ የብቃት ማረጋገጫ ክፍያ ከ1 ሺህ 600 ብር ወደ 10 ሺህ ብር ከፍ አድርጓል።
አሐዱ ሬዲዮ ከተሻሻለው አዲስ የክፍያ ማሻሻያ ደንብ ሰነድ እንደተመለከተው፣ የአገልግሎት ክፍያ ጭማሪው ከጳጉሜን 2 ቀን 2018 ዓ.ም. ጀምሮ ተግባራዊ መደረግ ጀምሯል።
ባለሥልጣኑ የክፍያ ማሻሻያውን ያደረገው ቀደም ሲል ለሆስፒታሎችና ክሊኒኮች ይጠየቅ የነበረው ክፍያ ለሆቴል እና ሬስቶራንቶች ከሚጠየቀው በእጅጉ ያነሰ በመሆኑ፣ ለአገልግሎቱ የሚያስፈልጉ የስራ ማስኬጃ ወጪዎች በመጨመራቸው እና የከተማዋን የዓመታዊ ገቢ እቅድ ለማሳካት እንደሆነ በሰነዱ መግቢያ ላይ ተብራርቷል።
በአዲሱ ማሻሻያ ደንብ መሰረት ወደ 10ሺህ ያደገው የ’ስፔሻላይዝድ’ እና ‘ኮምፕሪሄንሲቭ’ ሆስፒታሎች የማሳደሻ ክፍያ 5 ሺህ ብር ሆኗል።
በተጨማሪም፤ የጠቅላላ ሆስፒታል ፈቃድ ለማውጣት ከ1 ሺህ ብር ወደ 8 ሺህ ብር፣ የመድኃኒት ቤቶች የብቃት ማረጋገጫ ለማግኘት ከ400 ብር ወደ 2 ሺህ ብር፣ የጤና ጣቢያ ፈቃድ ለማውጣት ከ400 ብር ወደ 2 ሺህ 500 ብር ከፍ እንዲሉ መደረጉ በዝርዝር ተጠቅሷል።
ለፀጉር ንቅለ ተከላ አገልግሎት ተቋማት ፈቃድ ለማውጣት 5 ሺህ ብር የተተመነ ሲሆን፣ የተለያዩ የአምቡላንስ አገልግሎቶች እንደ ደረጃቸው ከ1 ሺህ እስከ 1 ሺህ 500 ብር ተቆርጦላቸዋል።
የጤና ባለሙያዎችን በተመለከተ አዲስ የሙያ ፈቃድ ማውጫ ከ200 ብር ወደ 500 ብር፣ የእድሳት ከ200 ብር ወደ 400 ብር፣ የመልካም ስራ የድጋፍ ደብዳቤ ከ100 ብር ወደ 500 ብር፣ እንዲሁም ለውጭ ዜጎች የህክምና ማስረጃ ማረጋገጫ ከ300 ብር ወደ 1 ሺህ ብር አድጓል።
ሆኖም ህዝቡ በህክምና ሂደት ለሚያጋጥሙ የሙያ ስነ-ምግባር አቤቱታዎች፣ የተቋማት የቁጥጥር ስምሪቶች እና የመጀመሪያ ዙር የቅድመ ፈቃድ ኢንስፔክሽኖች ከክፍያ ነፃ መሆናቸውን አሐዱ ከደንቡ ተመልክቷል።
አዲሱ የክፍያ ማሻሻያ ደንብ ነባሩን ደንብ ቁጥር 117/2013 የሚሽር ነው።

