የብዝሃ ሕይወት ሳይንቲስት ሎሬት ዶ/ር ተወልደብርሃን ገብረእግዚአብሔር ከዚህ ዓለም በሞት ተለዩ

በብዝሃ ሕይወት ሳይንቲስትነት አንቱታን ያተረፉት ሎሬት፣ ዶ/ር ተወልደብርሃን ገብረእግዚአብሔር ባደረባቸው ሕመም በ83 ዓመታቸው ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዉናል።
የአካባቢ ጥበቃ ተቆርቋሪ እና ተከራካሪ የነበሩት ዶ/ር ተወልደብርሃን ገብረእግዚአብሔር ከአባታቸው ከቄስ ገብረእግዚአብሔር ዮሐንስ እና ከእናታቸው ወ/ሮ መዓዛ ወልደ መድኅን በትግራይ ክልል ዐድዋ፣ ርባገረድ መንደር የካቲት 12 ቀን 1932 ዓ.ም ተወለዱ።
የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርታቸውን በንግሥተ ሳባ 1ኛ ደረጃ እንዲሁም ወደ ጀኔራል ዊንጌት 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በማምራት በ1959 ዓ.ም በከፍተኛ ውጤት ወደ ቀድሞው ቀዳማዊ ኃ/ሥላሴ የአሁኑ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ገብተዋል። የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን በባዮሎጂ የወርቅ ሜዳሊያ በመሸለም ጭምር አጠናቀዋል።
የሁለተኛ እና ዶክትሬት ዲግሪያቸውን በዩናይትድ ኪንግደም ስር ከዌልስ ዩኒቨርሲቲ አግኝተዋል፡፡ ሎሬት (ከአንድም ሁለቴ የሎሬት ማዕረግ አግኝተዋል) ፥ በብዝሃ ሕይወት ጥናት እና ምርምርም በርካታ ዓለም አቀፍ ሽልማቶችን ማግኘት ችለዋል።
በአካባቢ ጥበቃ ዘርፍ አገልግሎት የተከበረ ሥም ያላቸው ዶክተር ተወልደ በዘርፉ ላደረጉት ምርምርና በጉዳዩ ዙሪያ ከፍተኛ ግንዛቤ እንዲፈጠር ላደረጉት ጥረት በፈረንጆቹ 2000 Right Livlihood Award (አማራጭ የኖቬል ሽልማት) ስቶኮልም፣ ስዊዲን አግኝተዋል፡፡
በፈረንጆቹ 2006 ዓመት የተባበሩት መንግሥታት በአካባቢ ጥበቃ ዙሪያ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ላደረጉ ሰዎች የሚሰጠውን Champions of the Earth (የምድራችን ጀግና ሽልማት) ሲንጋፖር አግኝተዋል፡፡
የተማሩበት የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ደግሞ በ1997 የክብር ዶክትሬት ዲግሪ ሰጥቷቸዋል፡፡
ዶ/ር ተወልደ በ1970ዎቹ መጀመሪያ ላይ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሳይንስ ፋኩልቲ ዲን ሆነው ያገለገሉ ሲሆን፣ ከ1975 እስከ 1983 በነበረው ዘመን ደግሞ የአሥመራ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ነበሩ፡፡
ከደርግ መንግሥት መውደቅ በኋላ ለብዙ ዓመታት በሚታወቁበት የአካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ጀነራል ሆነው አገልግለዋል፡፡
ከአካባቢ ጥበቃና ብዝሃ ህይወት ጋር የሚያያዝ ከ30 በላይ ጥናቶችን አሳትመዋል።
በተመሳሳይ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ መጽሐፍትንም ጽፈዋል።
የአካባቢ ጥበቃ ስታራቴጂ በመንደፍና በኢትዮጵያና በተቀረውን ዓለም የሥነ ህይወት ሃብቶች ላይ የሚያተኩሩ ጽሑፎችን አዘጋጅተዋል።
የአካባቢ ጥበቃ ባለሙያው ዶክተር ተወልደ ታላላቅ አበርክቶዎች እንዳሏቸው በሳይንቲስቱ ህይወት ላይ ከሁለት አስርት አመታት በላይ የፈጀና “የምድራችን ጀግና” የሚል መጽሐፍ ደራሲና ጋዜጠኛ ዘነበ ወላ አሳትሟል።
በብዝሃ ሕይወትና የዓለም አርሶ አደሮችን መብት ለማስከበር ያደረጉት ድርድር (community right negotiation) ከአበርከቷቸው መካከል የሚጠቀስ ነው። በተለይ በሁለተኛው ድርድር ከ1.4 ቢሊዮን በላይ አርሶ አደሮችን ተጠቃሚ እንዳደረገ አመላክቷል።
ይህ ድርድር መነሻው የእህል ዘሮች የባለቤትነት መብት (Patent right) ጋር የሚያያዝ ነው።
“የእህል ዘር የባለቤትነት መብት የኛ ነው የሚሉ ሰዎች ተነሱ። ይኼኔ ዶክተር ተወልደ ‘ገበሬው ጠብቆ ያቆየልን ነገር ለናንተ የባለቤትነት መብት ሊሆን አይችልም’ ብሎ አሳምኖ ይህንን ውጤት አስገኝቷል”
በሌላ በኩል የዘረ መል ማሻሻያ በተደረገባቸው ወይም የGMO ምግቦች ያላቸውን ተጽዕኖ በተመለከተ ውጤት ያስገኘ ድርድር አድርገዋል።
ዶክተር ተወልደ ገብረእግዚአብሔር የደራሲ ስብሐት ገብረእግዚአብሔር ወንድም መሆናቸው ይታወቃል።
ሎሬት ፣ ዶ/ር ተወልደ ብርሃን የሦስት ሴቶች ልጆች አባት ሲሆኑ ከ60 በላይ ሌሎች ልጆችን ያሳደጉ ልበ ቀና፤ ደግ ሰው ነበሩ።
ኢትዮጵያ ሆይ! – ደስ ይበልሽ
በልጅሽ፤ በእርሱ ቤተሰብ ውስጥ በልተው፣ ጠጥተው፣ ተምረው ጨርሰው፣ ወጥተው ራሳቸውን ችለዋል።
ከሦስቱ ልጃቸው ታላቋ ሮማን ተወልደ ብርሃን ደራሲ እና የንግድ አስተዳደር ባለሞያ ሲሆኑ፤ በእንግሊዘኛ ቋንቋ «Reflections» የተባለ የግጥም መድብል ማሳተምን ጨምሮ በአማርኛ ልቦለዶችን ጽፈዋል ።
ባለቤታቸው ሱ ኤድዋርድስ በትውልድ እንግሊዛዊ ቢሆኑም በዜግነት ኢትዮጵያዊ ናቸው። “ዳግም ተጠምቃ የኢትዮጵያን ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስትያን እምነት ተከትላ በመንበረ ጸባኦት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ሥርዓተ ቀብሯ ተፈጽሟል።
የምድራችን ጀግና፤ የታዋቂው ሳይንስቲስት ሎሬት ዶክተር ተወልደ ብርሃን ገብረእግዚአብሔር ቀብር ፥  መጋቢት 13 ቀን 2015 ዓ.ም በመንበረ ጸባኦት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል በ 9:00 ሰዓት ተፈጸማል፡፡

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትስስር ይፍጠሩ

325,851FansLike
49,039FollowersFollow
13,194SubscribersSubscribe