ተጠራጣሪና አስቸጋሪ ጸባዮች ያሉት ባል ለትዳር አጋሩ ፈተና ነው፡፡ እያንዳንዷ አካሔዱ ትዕግስትን ትፈታተናለች፡፡ ስሜታዊ እንድትሆኚና ድካም እንዲሰማሽ፤ በትዳርሽም ተስፋ እንድትቆርጪ ሊያደርግሽ ይችላል፡፡ ለመሆኑ የተጠራጣሪና አስቸጋሪ ባል ዋነኛ ጸባዮች ምንድን ናቸው?
- ሁሌም ስሜትሽን ጥያቄ ውስጥ ይከታል
አንቺ ሁሌም ባለቤትሽንና ልጆችሽን በጤናማነት ለመምራት ትለፊያለሽ፤ ትደክሚያለሽ፡፡ ለራስሽ የምትሰጪው ጊዜ በቂ አይደለም፡፡ ምንም ያህል ጠንካራ ሴት ብትሆኚ ለእያንዳንዱ ድርጊትሽ ‹ምን አስባ ይሆን?› የሚል ጥያቄ ማንሳቱ አይቀርም፡፡ ጥንቃቄሽንና ኃላፊነት የምትወስጂባቸውን መንገዶች ሁሉ በጥርጣሬ መመልከቱ አይቀርም፡፡
- ነጥብ ይይዛል
አውቀሽም ይሁን በአጋጣሚ ያደረግሻቸውን ነገሮች በጥሞና እየተከታተለ ነጥብ ይይዛል፡፡ ከእርሱ ይልቅ አንቺ በብዙ መሳሳትሽን፣ ከእርሱ ይልቅ አስቸጋሪ ጸባይ ያለሽ መሆኑንና ሌሎች ነገሮችን እየቆጠረ ይቆይና አንድ ቀን ለማሸነፊያ ክርክር ሆን ብሎ ያነሳቸዋል፡፡
- የተደበቀ አጀንዳ እንዳለሽ ያስባል
በቤት ውስጥ የምትሠሪያቸው እያንዳንዱ ሥራዎች በእርግጥም ‹ኃላፊነትሽን ለመወጣት ብቻ የምታደርጊያቸው ናቸው ወይስ በእርሱ ዘንድ የተሻለ ተሰሚነት ለማግኘት› የሚለው ሃሳብ ያስጨንቀዋል፡፡ ከእያንዳንዱ ተግባራት ጀርባ የሆነ የደበቅሽው አጀንዳ ያለ ይመስለዋል፡፡
- ተከላካይነት ያዘወትራል
ከእርሱ ጋር በምትከራከሩባቸው ነገሮች ሁሉ ስህተቱን አምኖ ከመቀበል ወይም የመፍትሔ ሃሳብ ከማፍለቅ ይልቅ ተከላካይነት ማብዛት መለያው ነው፡፡
ባለቤትሽ እንዲህ ዓይነት ጸባይ ያለው ከሆነ በእርግጠኝነት ትዳራችሁ ዕድሜ አይኖረውም፡፡ ስለዚህ ይህን ጸባይ ለማስወገድ እንዲችል ከግል ምክክር ጀምሮ እስከ ጓደኛና ቤተሰብ ምክር፤ ከዚህም ከፍ ካለ በዕምነት አባቶች በማስመከር ጸባዩ እንዲታረም ብርቱ ጥረት ማድረግ ይኖርብሻል፡፡ ከምንም በላይ ደግሞ የትዳር ጉዳዮች አማካሪ ጋር በመሔድ መፍትሔ ለማግኘት ጥረት ማድረግም ብልህነት ነው፡፡