‹‹የዓመቱ ሰዎች››

ብርጋዴር ጄኔራል አሳምነው ፅጌ
በተጠናቀቀው ዓመት እጅግ አነጋጋሪ የነበረው ጉዳይ በአማራ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (አዴፓ) አመራሮች ላይ የተፈጸመው ጥቃት ነው፡፡ ሰኔ 15 ቀን 2011 ዓ.ም የተሞከረውና የክልሉ ፕሬዝዳንት ዶ/ር አምባቸው መኮነን፣ የኢትዮጵያ ጦር ኃይሎች ኤታማዦር ሹም ጄኔራል ሰዓረ መኮንንና ጓደኛቸውን እንዲሁም ሌሎች ሁለት ከፍተኛ የአማራ ክልል ባለስልጣናትን ህይወት ከቀጠፈው የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ ጀርባ ብርጋዴር ጄኔራል አሳምነው ፅጌ እንዳሉ የክልሉ ገዢ ፓርቲ የአማራ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (አዴፓ) እና የፌዴራሉ መንግስት ያሳወቀው ወዲያው ነበር፡፡
ጄኔራል አሳምነው እርምጃ መውሰዳቸውን ሊያረጋግጥ ይችላል የተባለ የድምፅ ቅጂም ይፋ ሆኗል። የድምፅ ቅጂውን ይፋ ያደረጉት የአማራ ብዙኃን መገናኛ ድርጅት ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ሙሉቀን ሰጥየ ናቸው። አቶ ሙሉቀን ሰጥየ ጥቃቱ በተፈጸመበት ሰኔ 15 ቀን 2011 ዓ.ም ከብርጋዴር ጄኔራል አሳምነው ጽጌ ጋር ቢያንስ ሶስት ጊዜ በስልክ መነጋገራቸውን ገልጸዋል። ብርጋዴር ጄኔራል አሳምነው እንደሆነ በተነገረለት የመልዕክት ልውውጥ ክልሉን በሚያስተዳድረው የአማራ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ አመራሮች ላይ እርምጃ መወሰዱን ሲናገሩ ይደመጣል።
በቴሌቭዝን ጣቢያው በተላለፈው ድምፅ ብርጋዴር ጄኔራል አሳምነው መሆናቸው የተገለጸው ሰው «በአዴፓ አመራሮች ላይ የሕዝቡ ሰላማዊ እና የመኖር መብቱ ጥያቄ ውስጥ ስለገባ፤ የሕዝብን ጥያቄ ለማንሳት በመቸገራቸው፤ የሕዝቡን ጥያቄ በመቀልበሳቸው በድርጅቱ አመራሮች ላይ እርምጃ ተወስዷል። እንዳትደነግጥ» ሲሉ ይደመጣል። አቶ ሙሉቀን ግን በወቅቱ በመደናገጣቸው ምክንያት «እርምጃ የተወሰደው እነ ማን ላይ ነው?» ብለው አለመጠየቃቸውን ለአማራ ቴሌቭዥን ጋዜጠኛ ተናግረዋል።
በመልዕክት ልውውጡ «ሁሉም ከጸጥታ ቢሮ የሚሰጠውን መመሪያ እንዲጠብቅ» ትዕዛዝ ሲተላለፍ ይደመጣል። በዚሁ የድምፅ ቅጂ «እዚህ አካባቢ ማኅበረሰቡ ወደ ቤቱ እንዲገባ፤ የአካባቢው የጸጥታ ኃይል እና ሚሊሻ ደግሞ ራሱን እንዲቆጣጠር» የሚል ትዕዛዝ ጭምር ይገኝበታል።
የአማራ ክልል እና የፌድራል መንግሥት ባለሥልጣናት ተሞክሮ ከሽፏል በተባለው መፈንቅለ-መንግሥት የጥቃት ዒላማ ከነበሩ ተቋማት መካከል የአማራ ብዙኃን መገናኛ ድርጅት እንደሚገኝበት በተደጋጋሚ ተናግረዋል።
የአማራ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ ማዕከላዊ ኮሚቴ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ዮሐንስ ቧያለው ደግሞ ጥቃቱ «የአማራ ሕዝብ መንግሥት፣ ጠንካራ ፓርቲ እና አመራር እንዳይኖረው» የተፈጸመ ነው ሲሉ ኮንነዋል። ድርጊት አቀነባብረዋል የተባሉትን ብርጋዴር ጄኔራል አሳምነው ከሰላም ግንባታ እና ደሕንነት ቢሮ ኃላፊነታቸው የማንሳት ውሳኔ ነበር የሚለውንም አስተባብለዋል።
ብርጋዴር ጄኔራል አሳምነውን «በግሉ ሳይሆን ተቋሙን ገምግመናል» ያሉት አቶ ዮሐንስ የክልሉ የሰላም ግንባታ እና ደሕንነት ቢሮ «ከውስጥም ከውጭም ያንዣበቡብንን አደጋዎች ለመከላከል በተለይ ደግሞ ሕግ እና ሥርዓት እንዲጠበቅ ለማድረግ» በፓርቲው እና በመንግሥት ድጋፍ ቢደረግለትም ስኬታማ አልሆነም ሲሉ ተችተዋል።

አቶ ዮሐንስ «ከፖሊስ፣ የልዩ ኃይል እና የሚሊሻ መደበኛ አደረጃጀት ውጪ ያለ ኃይል ሕጋዊ እና ሥርዓት ያለው ሆኖ እንዲንቀሳቀስ ፍላጎት ነበረን። ግን ኢ-መደበኛ የሚመስሉ እንቅስቃሴዎች ይደረጋሉ። ይኸ ልክ አይደለም መስተካከል አለበት ብለን ነው። በአጠቃላይ በየአካባቢው በተለያየ ሥም የተደራጁ እንዲሁም ደግሞ ከመንግሥት መዋቅር ጎን ለጎን ታጥቀው ለመንቀሳቀስ የሚሞክሩ ኃይሎች በተለያየ ቦታ ሲንቀሳቀሱ እነዚህ መቆም አለባቸው፤ ወንድሞቻችን ናቸው፤ ማስተማር እና ወደ ትክክለኛው አቅጣጫ መግባት አለባቸው፤ የማንም መሳሪያ መሆን የለባቸውም፤ ከዚህ ውጪ ደግሞ ሕግን የሚጥሱ ካሉ ሕግ እና ሥርዓት እንዲይዙ እና መልክ መያዝ አለበት የሚል ነገር በተደጋጋሚ ለተቋሙ ተነግሮት ተቋሙ ኢንኢፊሸንት የመሆን ወይም ደግሞ የማስፈጸም አቅሙ ዝቅተኛ የመሆን ሁኔታ ተከስቷል» ሲሉ ለአማራ ቴሌቭዥን ጣቢያ በጊዜው ተናግረዋል።
ብርጋዴር ጄኔራል አሳምነው ፅጌ ተወልደው ያደጉት ወሎ ላስታ ውስጥ ነው። አሳምነው ወደ ትግል በመግባት የወቅቱን ኢህዴን በኋላ ብአዴን የተባለውን የአማራ ድርጅትን ከመቀላቀላቸው በፊት በደሴ ከተማ በሚገኘው የመምህራን ኮሌጅ ውስጥ መምህር ሆነው አገልግለዋል።
ወታደራዊው መንግሥት በአማጺያኑ ከስልጣን ከተባረረ በኋላ በትውልድ አካባቢያቸው አስተዳዳሪ ሆነው ተሹመው ነበር። በማስከተልም ወደ መከላከያ ሠራዊቱ ገብተው በኢትዮጵያና በኤርትራ መካከል የድንበር ጦርነት ውስጥ ተሳታፊ ሆነው ነበር። ወደ አሜሪካ በመሄድ ወታደራዊ ትምህርት የተከታተሉት አሳምነው ከጦርነቱ በኋላ የጄኔራልነት ማዕረግ አግኝተው በሠራዊቱ ውስጥ በኃላፊነት ሲያገለግሉ ቆይተዋል።
ብርጋዴር ጄኔራል አሳምነው የመከላከያ ሠራዊቱን ኮሌጅ በበላይነት በመምራትና በማስተማር እንዳገለገሉ ይነገርላቸዋል። ብርጋዴር ጄኔራል አሳምነው በ2001 ዓ.ም ከሌሎች ወታደራዊ መኮንኖች ጋር መፈንቅለ መንግሥት ለማድረግ በማሴር ታስረው ነበር።
ጄኔራሉ በቀረበባቸው ክስ ጥፋተኛ ስለተባሉ ማዕረጋቸው ተገፎ የእድሜ ልክ እስራት ተፈርዶባቸው ለዘጠኝ ዓመታት በእስር ላይ ከቆዩ በኋላ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ ወደ ስልጣን ከመጡ በኋላ ከእስር ተፈትተው ለአገራቸው የከፈሉት መስዋዕትነትን እውቅና በመስጠት ማዕረጋቸው እንዲመለስና የሚያገኙት ጥቅም እንዲከበርላቸው አድርገዋል።
የአማራ ክልልም ብርጋዴር ጄኔራል አሳምነው ፅጌን ተጠሪነታቸው ለክልሉ ፕሬዝዳንት ሆኖ ለአጭር ጊዜ በቆዩበት የአማራ ክልል የጸጥታ ቢሮ ኃላፊ ሆነው እንዲያገለግሉ ሹመት ሰጥቷቸው ነበር።

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትስስር ይፍጠሩ

325,851FansLike
49,039FollowersFollow
13,194SubscribersSubscribe