‹‹የዓመቱ ሰዎች››

ሀይሌ ገ/ስላሴ
በአትሌቲክሱ መድረክ ለረጅም ዓመታት የነገሰው ሻለቃ ሀይሌ ገ/ስላሴ በ2011 ዓ.ም አንድ ትልቅ ተግባር ፈጽሟል፡፡ በኢትዮጵያ የዳስ ውስጥ ትምህርትን በማስቀረት ወደተሻለ የመማሪያ ክፍል ለማሸጋገር መሰራት አለበት የሚለው ሻለቃ አትሌት ኃይሌ ገብረስላሴ ወደአንድ ገጠራማ ስፍራ አምርቶ ትምህርት ቤት ገንብቶ አስረክቧል፡፡
ከዚህ ቀደም በበጎ አድራጎት ስራ እምብዛም አይሳተፍም በሚል የሚተቸው አትሌት ሀይሌ ገ/ስላሴ የዳስ ትምህርት ቤትን በመማሪያ ክፍሎች ለመተካት የመሰረት ድንጋይ ሲያስቀምጥ ብዙዎች በተለያየ መንገድ አድናቆታቸውን ገልጸዋል፡፡
ሚያዚያ 27 ቀን 2011 ዓ.ም በዋግ ኸምራ ብሔረሰብ አስተዳደር ፃግብጂ ወረዳ የሚገኘውን የገልኩ የዳስ ትምህርት ቤት ሙሉ በሙሉ ደረጃውን የጠበቀ አድርጎ ለማስገንባት ቃል ገባ፡፡ በወቅቱ “ትምህርት ቤቱን ለ2012 የትምህርት ዘመን ሙሉ በሙሉ ከዳስ ለማላቀቅ ጥረት አደርጋለሁ” ብሎ እንደነበርም የሚታወስ ነው፡፡
በዚህም ግንባታው አራት ወራት ባልሞላ ጊዜ ተጠናቆ ለምርቃትና ለማስተማርም ተዘጋጅቷል። ሻለቃ አትሌት ኃይሌ ገብረስላሴም በፃግብጂ ወረዳ ገልኩ ትምህርት ቤት በመገኘት ትምህርት ቤቱን አስመርቋል።
ኃይሌ ገብሥላሴ በሦስት ወራት ውስጥ በሁለት ሕንፃዎች የተከፈሉ ስምንት ክፍሎችን ማስገንባቱ ነው የተገለጸው፡፡
በትምህርት ቤቱ ምርቃ ስነ ስርዓት ላይም የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ይልቃል ከፋለ እና የሻለቃ አትሌት ኃይሌ ገብረስላሴ ባለቤት ተገኝተው ነበር፡፡
ሻለቃ አትሌት ኃይሌ ገብረስላሴ ከትምህርት ሚንስትሩ ዶክተር ጥላዬ ጌቴ ጋር የዳስ ትምህርት ቤቶች እንዴት ደረጃቸውን በጠበቁ ትምህርት ቤቶች መቀየር እንችላን በሚለው ጉዳይ ዙሪያም መወያየቱ ይታወሳል፡፡
አትሌት ሀይሌ እንደሚለው ትምህርት ቤቶቹን ለመስራትና ማህበረሰቡን ለማገዝ ያነሳሳው እነዚህን የመማሪያ ዳሶች በቴሌቪዥን መስኮት መመልከቱ እንደሆነ ገልጿል።
በተመለከተው ነገር ማዘኑን የገለፀው አትሌት ሀይሌ የኔ አንድ ትምህርት ቤት መስራት ብቻ በቂ አይደለም በሀገራችን ያሉትን የዳስ ትምህርት ቤቶች ሁሉም ሊረባረብ ይገባልም ነው ያለው፡፡
አትሌት ኃይሌ እነዚህን ትምህርት ቤቶች ለመስራት ፈቃደኛ በመሆኑ የትምህርት ሚንስትሩ አድንቀው እንደሱ አይነት ታዋቂ ሰዎች በእንዲህ አይነቱ ተግባር መሳተፍና መደገፍ አለባቸው ብለዋል።
መካከለኛ ኢኮኖሚ ካላቸው ሀገሮች ተርታ ለመመደብ እየሰራች ባለች ሀገር እንደነዚህ አይነት ትምህርት ቤቶች ማየት እጅጉን ያማል ያሉት ሚንስትሩ፤ በርካታ ችግሮች አሉብን ችግሮችን ለመቅረፍ በጋራ መስራት ይኖርብናል ብለዋል፡፡
የዳስ ትምህርት ቤቶቹን ለመቀየር የቀዳማዊት እመቤት ቢሮና አትሌት ሀይሌ ገብረስላሴ ፈቃደኝነታቸውን ያሳዩ ሲሆን በተለይ አትሌት ሀይሌ በየአመቱ ከሚዘጋጀው የታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ከሚሰበሰበው ገቢ እነዚህ ትምህርት ቤቶች ተሰርተው እስኪያልቁ ድጋፍ እንደሚያደርግ ተናግሯል።

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትስስር ይፍጠሩ

325,851FansLike
49,039FollowersFollow
13,194SubscribersSubscribe