‹‹የዓመቱ ሰዎች››

ጌታቸው አሰፋ
ከህዝብ አንደበት ሳይጠፋ አመቱን የዘለቀ ስም ነው፡፡ ጌታቸው አሰፋ፡፡ የቀድሞ የብሔራዊ መረጃና ደህንነት ኃላፊ፡፡ ሰውዬው እምጥ ይግቡ ስምጥ አልታወቀም፡፡ መቀሌ ከተማ እንዳሉ ይታመናል፡፡ ፖሊስም እስካሁን አላገኛቸውም፡፡ በሌሉበት ግን ክስ ተመስርቶባቸዋል፡፡
አቶ ጌታቸው አሰፋን ጨምር በ26 የብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት የሥራ ኃላፊዎችና ሠራተኞች ላይ ክስ መመስረቱን የፌደራል ጠቅላይ አቃቤ ሕግ ያስታወቀው በተጠናቀቀው አመት ነው።
የፌደራል ጠቅላይ አቃቤ ሕግ ይፋ ባደረገው መረጃ መሰረት፤ ከባድ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ፈጽመዋል በሚል በፌደራል ፖሊስ ወንጀል መርማሪዎች፣ በማረሚያ ቤት የሥራ ኃላፊዎች እንዲሁም በብሔራዊ መረጃና ደህንነት የሥራ ኃላፊዎች ላይ የወንጀል ምርመራ ሲያካሂድ ነበር።
በዚህ መሰረት፤ አቃቤ ሕግ በወንጀል መርማሪዎች፣ በማረሚያ ቤቱ የሥራ ኃላፊዎች ላይ እንዲሁም በብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት የሥራ ኃላፊዎችና ሠራተኞች ላይ በሦስት የተለያዩ መዝገቦች ክስ መስርቷል።
በክሶቹ ውስጥ 22ቱ ተከሳሾች በአሁኑ ወቅት በእስር ላይ የሚገኙ ሲሆን፤ በሌላ በኩል የቀድሞ የአገልግሎቱ ዋና ዳይሬክተር አቶ ጌታቸው አሰፋን ጨምሮ አቶ አጽብሃ ግደይ፣ አቶ አሠፋ በላይ እና አቶ ሽሻይ ልዑል በተባሉ የቀድሞ የአገልግሎቱ የሥራ ኃላፊዎች ላይ በሌሉበት ሚያዚያ 29 ቀን 2011 ዓ. ም በከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ችሎት ክስ ተመስርቶባቸዋል፡፡
በአቶ ጌታቸው ላይ፤ በ1996 ዓ. ም የወጣውን የወንጀል ሕግ አንቀጽ 32/1/ (ሀ) (ለ) እና 407/1/ (ለ) (ሐ) እና 407/3/ ላይ የተደነገገውን በመተላለፍ ሥልጣንን ያለአግባብ መገልገል ከባድ የሙስና ወንጀል መፈጸም እንዲሁም በ1996 ዓ. ም. የወጣውን የወንጀል ሕግ አንቀጽ 32 (1) ሀ እና ለ እንዲሁም የሙስና ወንጀሎችን ለመደንገግ የወጣውን አዋጅ ቁጥር 881/2007 አንቀጽ 9 /1/ (ለ) እና (ሐ) እና 9/3/ ላይ የተደነገገውን በመተላለፍ ሥልጣንን ያለአግባብ መገልገል ከባድ የሙስና ወንጀል ፈጽመዋል በሚል ክስ ቀርቦባቸዋል ሲል የፌደራል ጠቅላይ አቃቤ ሕግ አስታውቋል።
ሥልጣንን ያለአግባብ መጠቀም ክስ ሊቀርብባቸው የቻለው ተከሳሾች በግልጽ ከተሰጣቸው ሥልጣን ወይም ኃላፊነት አሳልፈው በመሥራት እንዲሁም ሥልጣናቸው ወይም ኃላፊነታቸው የማይፈቅድላቸውን በተለይም ሥልጣን ወይም ኃላፊነት ሳይኖራቸው በሌላ ሰው መብት ላይ ጉዳት እንዲደርስ በማሰብ በተበዳዮች ላይ ከባድ የሰብዓዊ መብት ጥሰት በመፈጸማቸው ነው ተብሏል።
ስለ የቀድሞ የመረጃና ደኅንነት አገልግሎት ኃላፊ አቶ ጌታቸው አሰፋ የሚታወቀው ነገር እጅግ በጣም ጥቂት ነው። ስለግለሰቡ መረጃ ለማግኘት ቢቢሲ የቀድሞ የትግል አጋሮቻቸውን እና የሥራ ባልደረቦቻቸውን ጠይቋል። በተጨማሪም ከቢቢሲ ዜና ክትትልና ክምችት ክፍል (ሞኒተሪንግ) እንዲሁም ዊኪሊክስ ላይ የወጡ መረጃዎች ዋቢ ተደርገዋል። ቢቢሲ ሞኒተሪንግ የብሪቲሽ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን /ቢቢሲ/ አካል ሲሆን ከ1931 ጀምሮ በመላው ዓለም የሚገኙ የመገናኛ ብዙኃንን ዘገባዎች በመከታተል መዝግቦ ያስቀምጣል።
አቶ ጌታቸው አሰፋ 1940ዎቹ መጨረሻ ላይ በመቀሌ ከተማ፤ ቀበሌ 14 በተለምዶ ‘እንዳ አቦይ ፍቐዱ’ የሚባል ሰፈር ነው የተወለዱት።
እስከ 8ኛ ክፍል እዚያው መቀሌ ከተማሩ በኋላ 9ኛ ክፍል ወደ አዲስ አበባ ሄዱ። ትምህርታቸውን በዊንጌት ትምህርት ቤት መከታተል ጀመሩ። የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በማቋረጥ 1969 ላይ የትጥቅ ትግሉን ተቀላቀሉ። ትጥቅ ትግሉን ከተቀላቀሉ በኋላ በመሪዎቻቸው አማካኝነት በመንግሥት ላይ ድንገተኛ ጥቃቶችን የሚሰነዝር ቡድንን እንዲቀላቀሉ ተደረጉ።
ትግል ላይ በነበሩበት ወቅት አቶ ጌታቸው በአልታዘዝም ባይነታቸው እና ግትር አቋማቸው ሦስት ጊዜ ከደረጃቸው ዝቅ ተደረገው እንዲሠሩ ተደርገው ነበር።
1980ዎቹ መጀመሪያ ላይ የህወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴ አባል ሆነው መመረጥም ችለው ነበር። የደርግ መንግሥት ከተገረሰሰ በኋላ፤ 1983 ላይ አቶ ጌታቸው በአገር መከላከያ ኃይል ውስጥ የኦፕሬሽን ኃላፊ ሆነው ተሹመዋል።ከአምስት ዓመታት በኋላ ደግሞ የፌደራል ፖሊስ ምክትል ኮሚሽነር ሆነው አገልግለዋል።
በኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት ወቅት የወቅቱ ጠቅላይ ሚንስትር መለስ ዜናዊ ለሚሰበስቡት የመከላከያ ማእከላዊ እዝ አዛዥ ሆነው ተሹመውም ነበር። ግንቦት 1993 ላይ የብሔራዊ መረጃ እና ደኅንነት ኃላፊ የነበሩት አቶ ክንፈ ገብረመድህን መገደልን ተከትሎ አቶ ጌታቸው አሰፋ የደኅንነት ቢሮ ኃላፊ ሆነው ተሾሙ።
ይህ ሹመታቸውም የጠቅላይ ሚንስትር መለስ ዜናዊ ቀኝ እጅ አድርጓቸዋል ተብሎ ይታመናል። አቶ ጌታቸው አሰፋ በጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ ከሥልጣናቸው እንዲነሱ እስከተደረጉበት ዕለት ድረስ የደኅንነት መሥሪያ ቤቱን ለ17 ዓመታት ያህል አስተዳድረዋል። አቶ ጌታቸው ለረዥም ዓመታት የመሩትን ተቋም ለጄኔራል አደም መሐመድ ካስረከቡ በኋላ በጥቂት ሳምንታት ውስጥ የትግራይ ክልላዊ መንግሥት የክልሉ የደኅንነት አማካሪ አድርጎ ሹመት ሰጥቷቸዋል።
ከዚህ በተጨማሪ አቶ ጌታቸው በአሁኑ ሰዓት የሕወሃት እና የኢህዴግ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል ናቸው። አቶ ጌታቸው የሁለት ሴት ልጆች አባት ናቸው።

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትስስር ይፍጠሩ

325,851FansLike
49,039FollowersFollow
13,194SubscribersSubscribe