የጅብራልተሩ አለት – ሲታወሱ

የአፍሪካ የስፖርት አባት የሚል ስም የተሰጣቸው ክቡር አቶ ይድነቃቸው ተሰማ እሸቴ ህይወታቸው ካለፈ ባለፈው ሰኞ ነሀሴ 13 2011፤ 32 አመት ሆናቸው፡፡ ይህን ቀን ምክንያት በማድረግ ከተወዳጅ ሚድያና ኮሚኒክሽን የተላከልን ጽሁፍ አለ፡፡
ጋዜጣዊ መግለጫ በኢቲቪ
የዛሬ 33 ዓመት ነበር፡፡ በወቅቱ ሜክሲኮ ያሰናደችውን አስራሦስተኛውን የዓለም እግር ኳስ ዋንጫ የብዙዎችን ትኩረት ስቦ ስለነበር ትንታኔው ከአቶ ይድነቃቸው ይጠበቅ ነበር፡፡
10 የስፖርት ጋዜጠኞች ጋሽ ይድነቃቸውን ለመጠየቅ ቦታቸውን ይዘዋል፡፡ በኢቲቪ እስቱዲዎ የተገኙት አስሩ የስፖርት ጋዜጠኞች ደምሴ ዳምጤ ከኢትዮጵያ ሬድዮ፤ ግርማ ሰይፉ ከአዲስ ዘመን፤ በሃይሉ አስፋው ከዛሬይቱ ኢትዮጵያ፤ ኢብራሂም ሃጂ ከበሪሳ ጋዜጣ፤ ሰለሞን ገብረእግዚአብሕር ከኢቲቪ፤ ይንበርብሩ ምትኬ ከኢትዮጵያ ሬድዮ፤ ሃድጉም መስፍን ከዓልአለም ጋዜጣ፤ ገዛህኝ ፄዮን መስቀል ከኢዜአ እና አዋያዩ ፀጋ ቁምላቸው ነበሩ፡፡
ይሄንኑ ጋዜጣዊ ጉባኤ የሚያሳየውን የአንድ ሰዓት ተኩል ቪዲዮ ሲመለከቱ “አቶ ይድነቃቸው እግር ኳስን ያውቃሉ” ይላሉ፡፡ በአንድ በኩል ደግሞ ሰውየው ለሀገር እና ለአህጉር ያላቸውን ተቆርቋሪነት ይረዳሉ፡፡
በግዜው የሀገራችን ብርቅዬ ጋዜጠኞች የነበሩት እነ ደምሴ ይጠይቃሉ፡፡ አቶ ይድነቃቸውም ደስ በሚል አንደበታቸው የተብራራ ምላሽ ይሰጣሉ፡፡
የበሪሳው ኢብራሂም እጁን አውጥቶ አንድ ጥያቄ ጠየቀ፡፡ ከፔሌና ከማራዶና የቱን ያደንቃሉ? ጋሽ ይድነቃቸውም ፈገግታን አስቀደሙና ‘’አንድ ያልገባችሁ ነገር ፔሌን አናውቀውም ስትሉ እራሳችሁን ልጅ ማድረጋችሁ ነው? ወጣት ነኝ ለማለት ካልፈለጋችሁ በቀር ፔሌ ሲጫወት አይታችሁታል፡፡” በዚህ ጊዜ ጋዜጠኞቹ በሳቅ እስቱዲዮውን ሞሉት፡፡ አሁን ጋሽ ይድኔ ለቤቱ ጥሩ የሳቅ ድባብ ፈጠሩ፡፡
“ማራዶና በአሁኑ ትውልድም እንደምናየው ጥሩ ተጫዋች ነው ግን ግራኝ ነው”
ሲሉ ሳቁ ጋብ ካለ በኋላ ለጥያቄው መልስ መስጠት ጀመሩ፡፡
በአቶ ይድነቃቸው አባባል ማራዶና ሲያቀብል መዝኖ ነው፡፡ በዚህም የሃንጋሪውን ፑሽካሽን ይመስላል፡፡ ለእሳቸው ማራዶና እና ፔሌን ማወዳደር በእጅጉ ይከብዳል “ፔሌ አንደኛ በሁለቱም እግሮቹ ይጫወታል፡፡ ሰውነቱም የተደላደለ፤ ኳስን የመቆጣጠር ብቃቱ በጣም የተሻለ ነው፡፡”ይህን የጋሽ ይድኔን ገለፃ እያደመጡ ፔሌን ሲጫወት ቢመለከቱት ያሉት ግልፅ ይሆንሎታል፡፡ ለጋሽ ይድነቃቸው ማራዶና ብዙ ጊዜ ኳስን በእራሱ አይነካም፡፡ ፔሌ ግን ብዙ ጎሎችን ያስገባው በጭንቅላቱ ገጭቶ ሲሆን ፍጥነቱም የሚደንቅ ነው፡፡
ማራዶና ሰባት የኢንግሊዝ ተጫዋቾችን አብዶ ሰርቶ ማግባቱ አለምን እንዳስደነቀ አቶ ይድነቃቸው ይጠቅሳሉ፡፡ ነገር ግን ፔሌ እስከ ዘጠኝ ተጫዋቾችን አብዶ ሰርቶ አግብቷል፡፡ ይህም አንድ ጊዜ ሳይሆን ከ20/30 ጊዜ በላይ ነው ሲሉ አቶ ይድነቃቸው የፔሌን ሀያልነት ይገልፃሉ::
ተንታኙThe Giant of Brazil የሚለውን ፊልም ጠቀሱ“ፔሌ በግዜው በ1958 የ17 ዓመት ልጅ ሆኖ ያገባውን ግብ ብትመለከቱ ፔሌን ታደንቃላችሁ” ሲሉ ፔሌ እንደሚበልጥ ተናገሩ፡፡
ከጋዜጣዊ መግለጫው ለአፍታ ወደ ነጋድራስ
የኢትዮጵያ ንጉሣዊ መንግሥት ባልተረጋጋበት ዘመን አንድ ኢትዮጵያዊ ሚንስትር በአይን ቁራኛ ይታዩ ነበር፡፡ ከእኚህ ሰው ጋር አብሬ ነኝ የሚል ሰው ከጥቁር መዝገብ ውስጥ ይገባ የነበረበት ጊዜ ነው፡፡ እኚህ ሚንስትር ከልጅ እያሱ ጋር አብሮ የነበሩት ነጋድራስ ተሰማ እሸቴ ነበሩ፡፡ውጥረቱ ሲበዛ ወደ ጅማ በግዞት መልክ ተላኩ፡፡ ነጋድራስ ተሰማ ጅማ እንደገቡ ክረምቱ አለፈና አዲስ ዓመት ገባ፡፡ በአዲሱ አመት የመጀመሪያው ቀን ነጋድራስ አንድ የምሥራች ሰሙ፡፡
መስከረም 11 ቀን 1914 ባለቤታቸው ወይዘሮ ሙላቷ ገ/ስላሴ ወንድ ልጅ ተገላገሉ ስሙም ይድነቃቸው ተባለ፡፡
ይድነቃቸው እድሜያቸው ለትምህርት ሲደርስ የቄስ ትምህርት ጀመሩ፡፡ የነጋድራስ ተሰማ እሸቴ የግዞት ጊዜ አልቆ ወደ አዲስ አበባ ሲመለሱ ይድነቃቸው ትምህርታቸውን ቀጠሉ፡፡
በዚህም መሠረት ከ6-14 ዓመታቸው ዘመናዊ የፈረንሳይኛ ትምህርት በኣሊያንስ፤ በዳግማዊ ሚኒሊክ፤ እና በተፈሪ መኮንን ትምህርት ቤቶች ተምረዋል፡፡በ14 ዓመታቸው በ1930 ጠላት ሀገራችንን ሲወር ጉለሌ ሚሲዮን ትምህርት ቤት ገቡ፡፡ ይድነቃቸው በዚህ የታዳጊነት ወጣት ዘመናቸው ለእግር ኳስ፤ ለብስክሌት እና ለሩጫ እስፖርት የተለየ ፍቅር ነበራቸው፡፡
ይድነቃቸው ለእስፖርት የነበራቸው ፍቅር ኃያል እየሆነ ሄደ፡፡ የቀን የሌት ሐሳባቸው እስፖርት ሆነ፡፡ እናም አንድ ቁምነገር ማከናወን ሳይኖርብኝ አይቀርም የሚል ሐሳብ ወደ አይምሮዋቸው መጣ፡፡ 22 ዓመታቸውን ባከበሩ ማግስት በ1936 አባኮራን ሰፈር በሁለት ብር ቤት ተከራዩ፡፡ በጊዜው በአቶ አምደ ሚካኤል አቅራቢነት በደጅ አዝማች ከበደ ተሰማ ፈቃድ በጀት የሌለው የኢትዮጵያ የእስፖርት ፅ/ቤት እንዲቋቋም ተደረገ፡፡ የፅ/ቤቱም አላማ የብስክሌት፣ የእግር ኳስና የቦክስ ውድድር ማድረግ ነበር፡፡
ጽ/ቤቱ ይህን አላማውን እያስፈፀመ ሁለት ወር እንደቆየ ወደ ሌላ ጽ/ቤት ተዛወረ፡፡ አቶ ይድነቃቸውም ጎጆ የወጡበት ጊዜ ስለነበር ከሜዳ የሚገኘው ገቢ ደሞዝ ለእሳቸው መክፈል ስላልቻለ ሌላ ዘዴ መቀየስ ነበረበት፡፡
የ22 ዓመቱ ይድነቃቸው በጊዜው የዳግማዊ ሚኒሊክ ሆስፒታል አስተዳደሪ ሆነው ሲቀጠሩ ማታ ማታ ደግሞ አቶ አምደ ሚካኤል በሰጧቸው ጎጆ ቤት ውስጥ የእስፖርት ውድድሮችን ማዘጋጀት ጀመሩ፡፡
4) ይድነቃቸው የአፍሪካ ባለውለታ
የአፍሪካ የእግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን በ1949 ካርቱም ላይ በሱዳን በግብጽና በኢትዮጰያ እና በደቡብ አፍሪካ አባልነት ተመሰረተ፡፡ ኮንፌዴሬሽኑ ከአፍሪካ አንድነት በፊት የተቁዋቁዋመ የመጀመሪያው አህጉራዊ ማህበር ነው፡፡ ደቡብ አፍሪካ ትከተለው በነበረው የአፓርታይድ ሥርአት ወዲያውኑ ከአባልነት ስትሰረዝ የተቀሩት ሶስት አገሮች ግን ተጨማሪ አባላትን እየመዘገቡ ካፍ ጠንካራ አህጉራዊ ማህበራዊ እንዲሆን መሠረት ጥለዋል፡፡
ይድነቃቸው ድርጅቱን በመስራች አባልነትና በምክትል ፕሬዚዳንትነት ከ 1950 እስከ 1965 ለ15 አመታት ሲያገለግሉ ቆይተዋል፡፡ በ1965 ፕሬዚዳንትነቱን ተረክበው በተከታታይ ለ4 ጊዜ ህይወታቸው እስካለፈበት እስከ ነሃሴ 13-1979 በካፍ ፕሬዚዳንትነት አገልግለዋል፡፡ አቶ ይድነቃቸው ካፍን ሲመሩ ሙስና በድርጅቱ ውስጥ እንዳይኖር በሚገባ ተዋግተዋል፡፡ አንዳንድ የአፍሪካ የፖለቲካ መሪዎች በተጽእኖ ውሳኔዎችን ለማስለወጥ ያደረጉትን ሙከራ በማጋለጥ ከፍተኛ ሚና ተጫውተዋል፡፡ የትምባሆና የአልክሆል ማስታወቂያዎች በአፍሪካ ስቴዲየሞች እንዳይሰቀሉ አቶ ይድነቃቸው ተከላክለዋል፡፡
6) ይድነቃቸውን ለማስታወስ ምን ተደረገ
እስከ አሁን በሰበሰብነው መረጃ መሠረት የአፍሪካና ኢትዮጰያ የኳስ አባት በመባል የሚታወቁትን ይድነቃቸው ተሰማን ለማስታወስ የሚከተሉት አበይት ነጥቦችን በመዘርዘር ስለ የጅብራልተሩ አለት- ይድነቃቸው ተሰማ እሸቴ ያዘጋጀነውን እንቋጫለን፡፡
• በኢትዮጵያ የባህርዳር ስቴዲየም ዋና በር በስማቸው ተሰይሞአል ፡፡
• ሞሮኮ ካዛብላንካ የሚገኘው የስፖርት ማዘውተሪያ ፍራ በይድነቃቸው ስም ተሰይሞአል፤ እስከዛሬም ድረስ በየዓመቱ ከሚዘጋጁት 3 ጨዋታዎች አንዱ የሚደረገው በይድነቃቸው ኮምፕሌክስ ነው፡፡
• 6ኛው የታዳጊዎች የስፖርት ውድድር በባህር ዳር ስቴዲየም በስማቸውተካሂዶአል፡፡
• መቀመጫው ሰሜን አሜሪካ ያደረገው seed የተሰኘው ድርጅት የ2007 ዓ.ም ሽልማቱን አበርክቶላቸዋል
አቶ ይድነቃቸው በነሃሴ 13 1979 ህይወታቸው አልፋለች፡፡

Kumneger Media
Kumneger Media
Kumneger Media is a News and Entertainment Website & Channel. Kumneger Media in addition to News and Entertainment it is the hub of Politics, Movies, Drama, Music, Comedy, Documentary and More!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትስስር ይፍጠሩ

325,851FansLike
49,039FollowersFollow
13,194SubscribersSubscribe