ይልቅ ወሬ ልንገርህ –
የመንጃ ፈቃድ የማሰልጠን ስራ ለቴክኒክና ሙያ ኤጀንሲ ሊሰጥ ስለመሆኑ
የአሽከርካሪ ብቃት ማረጋገጫና የመንጃ ፈቃድ አሰጣት ስርዓቱ ከጊዜ ወደ ጊዜ በብልሹ አሰራር የተያዘ ከመሆኑ ጋር በተያያዘ የመኪና አደጋን ለመቀነስ ባለመቻሉ የተሸከርካሪ ማሰልጠኛ ተቋማትን ከግል ወደ መንግስት በማዛወር ስልጠናውን የቴክኒክና ሙያ ማሰልጠኛ ኤጀንሲ ሊሰጥ እንደሆነ ተገለፀ፡፡
የትራንስፖርት ሚኒስትር ወ/ሮ ዳግማዊት ሞገስ ባለፈው ሳምንት አጋማሽ ላይ የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱን የ2011 ዘጠኝ ወራት የስራ ሪፖርት ለተወካዮችም ምክር ቤት ባቀረቡበት ወቅት የአሽከርካሪ ተቋማትን የብቃት ማረጋገጥን በተመለከተ በስድስት ክልሎች በተደረገው ጥብቅ ክትትልና ቁጥጥር ስራ በ266 የግል አሽከርካሪ ተቋማት ላይ በተደረገው ቁጥጥር 253ቱ ላይ ጉድለት መገኘቱን ጠቅሰዋል፤
በመሆኑን የግል የአሽከርካሪ ብቃት ማሰልጠኛ ተቋማት የሚያስተምሯቸው ወጣቶች የመንገድ ደህንነት ህግጋትን በአግባቡ የማያውቁና የብቃት ችግር እየታየባቸው በመሆኑ ከመንጃ ፈቃድ አሰጣጥ ጋር በተያያዘ ያለውን ችግር ለመፍታት ከተለመደው አሰራር በመውጣት ከቴክኒክና ሙያ ኤጀንሲ ጋር በመነጋገር ስልጠናውን በተሸለ መልኩ ለማስኬድ ጥናት መደረጉን ገልፀዋል፡፡
ወ/ሮ ዳግማዊት እንደጠቀሱት በመስኩ የሚሰማራውን የሰው ሀይል ጥራት ያለውና ብቃቱ የተረጋገጠ በማድረግ በውጭ ሀገር ተወዳዳሪ ለማድረግ የሚያስችል ጥናት ተደርጎ የመግባቢያ ሰነድ መፈረሙን አስታውቀል፡፡
ትራንስፖርት ሚኒስቴር የአሽከራካሪነት ማሰልጠን ስራን በቴክኒክና ሙያ ኤጀንሲ ሲሰጥ በዘርፉ ንግድ ፈቃድ አውጥተው እየሰሩ ያሉ የግል ማሰልጠኛ ተቋማት ዕጣ ፈንታ እንዴት እንደሚሆን በምክር ቤት አባላት በኩል ቀረበ ጥያቄ አለመኖሩ አነጋጋሪ ሆኗል፤

