ዲስ ክብረወሰኖችን በማይጠበቁ ርቀቶች ሰብረዋል፡፡ በኢትዮጵያውያን እጅ ውስጥ የሚገኙ ክብረወሰኖችን ብዛትም 24 አድርሰውታል፡፡ ዮሚፍ ቀጀልቻና ሳሙአል ተፈራ፡፡
ዮሚፍ
አሜሪካ ቦስተን ውስጥ በተካሄደ የአንድ ማይል (1.6 ኪሎ ሜትር) የቤት ውስጥ ውድድር ከ22 ዓመታት በፊት በሞሮኳዊው አትሌት ሂሻም ኤልግሩዥ ተይዞ የነበረውን ሪከርድ ኢትዮጵያዊው አትሌት ዮሚፍ ቀጀልቻ ሰብሮታል።
ከስድስት ቀናት በፊት እሁድ እለት በተደረገው በዚህ የቤት ውስጥ ውድድር 3፡47፡01 በመግባት ሪከርዱን አሻሽሏል። በዚህ ውድድር ላይ አሜሪካዊው ጆኒ ግሬጎሬክ 3፡49፡98 በመግባት በሁለተኛነት አጠናቋል። “ሪከርድ መስበር በጣም ደስ ይላል፤ አንድ ሰው የሚሮጠው የሆነ ነገር ለማግኘት ነው” የሚለው አትሌቱ ለሯጭም ከፍተኛ ደረጃ እንደሆነ ይናገራል።
“አንድ አትሌት በህይወቱ የሚያስደስተው ነገር ኦሎምፒክ ማሸነፍና የአለም ሪከርድ መስበር ነው። ስለዚህ በጣም ደስ ብሎኛል” በማለት ለቢቢሲ ገልጿል።
ሪከርድ በመስበሩ የሚያገኘው ገንዘብ ምን ያህል እንደሆነ ከቢቢሲ ለቀረበለት ጥያቄም ከዚህ ቀደም ሪከርድ የሚሰብር የሚያገኘውን ያህል እንደሆነ ተናግሯል። በኤልግሩዥ ተይዞ የነበረውን ሬከርድ በአንድ ደቂቃ በአርባ አራት ሰከንዶች ያሻሻለው ዮሚፍ በሶስተኛው ሙከራ ሪከርድ መስበር እንደቻለም ተዘግቧል።
የ21 አመቱ ዮሚፍ ከሶስት ሳምንታት በፊት ኒውዮርክ ውስጥ በተመሳሳይ ርቀት ውድድር ያደረገ ሲሆን፤ በወቅቱም በ0.01 ሰከንድ ዘግይቶ ሪከርዱን ሳይሰብር ቀርቷል። በወቅቱ ስለነበረው ስሜትም አትሌቱ ለቢቢሲ ተናግሯል ” ያኔ በጣም ተሰምቶኝ ነበር፤ ውድድሩን ስጨርስ ዝቅ ብየ ቢሆን ኖሮ ሪከርዱን እሰብረው ነበር።” የሚለው አትሌቱ በቀጣይነትም ረጅምና መካከለኛ ርቀት የመሮጥ እቅድ እንዳለው ተናግሯል።
“ትልቁ ሀሳቤ ከቤት ውጭ በአምስት ሺ ሜትር ሪከርድ መስበር ወይም ፈጣን ሰአት ማስመዝገብ እፈልጋለሁ” ብሏል። ዮሚፍ ያስመዘገበው ሰአት በኢትዮጵያም ውስጥ ፈጣኑ ሲሆን ይህም በአማን ወጤ 3፡48፡60 ተይዞ የነበረውን አሻሽሎታል ማለት ነው፡፡
ሳሙኤል
የ19 ዓመቱ አትሌት ሳሙኤል ተፈራ ከሶስት ሳምንታት በፊት በበርሚንግሃም እንግሊዝ ተካሂዶ በነበረው የቤት ውስጥ የሩጫ ውድድር የዓለም ክብወሰንን በማሻሻል አሽንፏል።
በ1500 ሜትር የቤት ውስጥ ውድድር በሞሮኳዊው አትሌት ሂሻም ኤልግሩዥ እአአ 1997 ተይዞ የነበረዉን 3፡31፡18 ክብረ ወሰን በ14 ማይክሮ ሰከንዶች በማሻሻል አትሌት ሳሙኤል ተፈራ አሸናፊ መሆን ችሏል።
አትሌቱ የቤት ውስጥ ሩጫን ከዚህ በፊት አሸንፎ ስለማያውቅ የማሸነፍ ግምት አልተሰጠውም ነበር። ይልቁንም ባለፉት ሳምንታት ውድድሮቹን በድል ሲያጠናቅቅ የቆየው ዮሚፍ ቀጄልቻ ከፍተኛ የአሸናፊነት ግምት ተሰጥቶት ነበር። ዮሚፍ በዚህ ውድድር 3፡31፡58 በመግባት በርቀቱ የግሉን ምርጥ ሰዓት ማስመዝገብ ችሏል።
“በጣም ደስተኛ ነኝ፤ ደስታዬ ይሄ ነው ለማለት ይከብደኛል። ወደዚህ ውድድር የገባሁት በግፊት እንጂ የራሴ ሃሳብ ኖሮኝ አይደለም። የፈጣሪ እርዳታ ነው” በማለት ሳሙኤል ለቢቢሲ በወቅቱ አስተያየቱን ተናግሯል።
ሳሙኤል በውድድሩ ላይ እንዴት እንደተሳተፈ ሲያስረዳ ”የዓለም ሪከርድን አሻሽላለሁ ብዬ አይደለም ወደ ስፍራው ያቀናሁት። ኔዘርላንድ እና ፈረንሳይ ለነበሩኝ ውድድሮች ላይ ለመሳተፍ ነው ወደ አውሮፓ ያቀናሁት። እኔ ሃሳቤ የነበረው የኔዘርላንድ እና ፈረንሳይ ውድድር ተሳትፌ ወደ ኢትዮጵያ መመለስ ነበር። ነገር ግን እንዳጋጣሚ ሆኖ ይህ ውድድርም አውሮፓ እያለሁኝ የሚካሄድ ስለነበረ በጣም በተጣበበ ሁኔታ ተወዳድሬ ነው ማሸነፍ የቻልኩት” ብሏል።
ሳሙኤል ያሻሻለው ሪከርድ እሱ ከመወለዱ በፊት የተያዘ ነበር። አትሌቱ ገና 19 ዓመት ወጣት ሲሆን ይህ ውድድር በማሸነፉ 3ሺህ ዶላር እንዲሁም ሪከርድ በመስበሩ 30ሺህ ዶላር ተሸላሚ ለመሆን በቅቷል። ከዚህ ቀደም ምንም አይነት የዓለም ሪከርዶችን አሻሽሎ እንደማያውቅ የሚያስረዳው ሳሙኤል ለመጀመሪያ ጊዜ ያሻሻለው ሪከርድ ለሌላ ስኬት እንደሚያነሳሳው እና ወደፊትም ጠንክሮ እንዲሰራ ብርታት እንደሚሆነው ይናገራል።
በዚህ ውድድር በሁለተኛ ደረጃ ያጠናቀቀው ዮሚፍ፤ ከሳምንት በፊት በኒው ዮርክ የአንድ ማይል ሩጫ ተይዞ የነበረውን ክብረ ወሰን በአንድ ማይክሮ ሰክንድ ዘግይቶ በመግባቱ ሳያሻሽል ቀርቷል። በዚህም ምክንያት ይህን ውድድር ያሸንፋል ተብሎ ከፍተኛ ግምት ተሰጥቶት የነበረው ዮሚፍ ቀጄልቻ ነበር። የሳሙኤልም ሃሳብ ይሄ ነበር።
“ለአንድ ማይክሮ ሰከንድ ሳያሻሽል መቅረቱ በጣም አሳዝኖኝ ነበር። በዚህም ውድድር ዮሚፍ ያሸንፋል የሚል ግምት ነበረኝ። እኔም የዮሚፍ ጥሩ ተፎካካሪ እንደምሆን እራሴን አሳምኜ ነበር የገባሁት” ብሎ ነበር ሳሙኤል።
ምዕራብ ሸዋ ሚዳ ቀኝ ወረዳ የተወለደው ሳሙኤል በ2007 ዓ.ም የ10 ኛ ክፍል ትምህርቱን በማቋረጥ ነው ፊቱን ወደ አትሌቲክስ ስፖርት ያዞረው፡፡ እናም በ2008 የኦሮሚያ እንስሳትና ደን ጥበቃ ክለብን ተቀላቀሎ በተለያዩ ውድድሮች መሳተፍ ጀመረ፡፡ በ2009 ኢትጵያን ወክሎ የአለም ሻምፒዮና ላይ ቢሳተፍም ውጤታማ ሳይሆን ቀርቷል፡፡ በ2010 የአለም የቤት ዉስጥ ሩጫ ውድድር ግን በ1500 ሜትር የወርቅ ተሸላሚ ሆኗል፡፡