ደግ ልብ ያላቸው ስፖርተኞች
ታዋቂ የስፖርት ሰዎች በተለያዩ የበጎ ፍቃድ ስራዎች ውስጥ ይሳተፋሉ፡፡ በግላቸው በሚያቋቁሟቸው ድርጅቶች አማካኝነት ወይም በሌሎች በጎ አድራጊዎች በተመሰረቱ ድርጅቶች በኩል የተቸገሩትን ይረዳሉ፡፡ ካካበቱት ሀብት ጥቂቱንም ቢሆን ያካፍላሉ፡፡ በእንዲህ አይነት በጎ ፍቃድ ስራዎች ውስጥ ከሚሳተፉ ደግ ልብ ያላቸው ስፖርተኞች መካከል የተወሰኑትን እንንገራችሁ፡፡
ክርስቲያኖ ሮናልዶ
‹‹አባቴ በልጅነቴ የሚነግረኝ ነገር ነበር፡፡ ሰዎችን ስትረዳ ፈጣሪ እጥፍ አድርጎ ይመልስልሀል ይለኝ ነበር፤ አሁን እያደረኩ ያለሁት እሱን ነው፡፡ በችግር ውስጥ ያሉ ሰዎችን ስረዳቸው ፈጣሪ ደግሞ እኔን ይረዳኛል›› በማለት ይናገራል፡፡ የአለማችን ኮከብ እግር ኳስ ተጫዋች ክርስቲያኖ ሮናልዶ ዶስ ሳንቶስ አቬሮ፡፡
በአንድ ወቅት Dosomething.org የተባለ ድረገጽ አንድ መረጃ ይዞ ወጥቶ ነበር፡፡ በአለማችን ላይ ከሚገኙ ታላላቅ የስፖርት ሰዎች መካከል በበጎ ፍቃድ ስራዎች የነቃ ተሳትፎ የሚያደርጉና ለብዙ ችግረኞች ህይወት የደረሡ ያላቸውን በቅደም ተከተል አስቀምጧል፡፡ በዝርዝር ካስቀመጣቸው 20 የስፖርት ኮከቦች መካከል በአንደኛ ደረጃ የተገኘው አሁን ለዩቬንቱስ የሚጫወተው ፖርቱጋላዊው ኮከብ ክርስቲያኖ ሮናልዶ ነው፡፡ ‹‹ሮናልዶ በተለያየ ጊዜ ባልታሰበ አደጋ ጉዳት ለደረሰባቸው ዜጎችና ለተለያዩ ግለሰቦች ከካዝናው ገንዘብ በማውጣትና ከሌሎችም ከማሰባሰብ ድጋፍ አድርጓል፡፡ ከሁለት ዓመት በፊት የአዕምሮ ቀዶ ጥገና ለተደረገለት የ10 አመት ህጻን 83 ሺህ ዶላር ወጭ አድርጓል፡፡ እናቱ ታክማ ለዳነችበትና በፖርቹጋል ለሚገኘው የካንሠር ማዕከል ደግሞ 165 ሺህ ዶላር አበርክቷል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ሮናልዶ ዝናውን በመጠቀም በተለይ በረሃብ፣ በድንገተኛ አደጋና በተለያዩ ችግሮች አደጋ ለሚደርስባቸው ሰዎች የበጎ ፍቃድ አምባሳደር በመሆን ስለነሱ ድምፁን ያሰማል›› ይላል ድረገፁ፡፡
ሮናልዶ እ.ኤ.አ በ2014 በኢንዶኔዥያ የተከሠተውን የሱናሜ አደጋ ተከትሎ ለድጋፍ ወደስፍራው ካቀኑ ሰዎች መካከል አንዱ ነው፡፡ በወቅቱ ክርስቲያኖ ሮናልዶ በአደጋው የተጎዱ ሠዎችን በቴሌቪዥን ሲመለከት ትኩረቱን የሳበው አንድ ምስል ነበር፡፡ የሱ ስምና ሰባት ቁጥር የተጻፈበት የፖርቹጋል ብሔራዊ ቡድን ማልያ የለበሰ ታዳጊ ልጅ የሱናሜ አደጋው ሰለባ ከሆኑት ሰዎች መካከል ይታያል፡፡ ያኔ ሮናልዶ ወሰነ፡፡ በኢንዶኔዥያ ተገኝቶ ድጋፍ አድርጎ ተመለሰ፡፡
ከአራት ዓመት በፊት በኔፓል በደረሠው ከፍተኛ ርዕደ መሬት ሳቢያ የተጎዱ የሃገሪቱን ዜጎችም በግላቸው ከረዱ ሰዎች መካከልም አንዱ ሮናልዶ ነው፡፡ የ34 ዓመቱ ኮከብ የ5 ሚሊዮን ፓውንድ ድጋፍ ለኔፓላውያን አበርክቷል፡፡
መረጃዎች እንደሚጠቁሙት ሮናልዶ በዩቬንቱስ ቤት በዓመት ከ30 ሚሊየን ፓውንድ በላይ ይከፈለዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ከስፖንሰርሺፕ፣ ከማስታወቂያ፣ ከንግድ ስራና ከሌሎችም መሰል እንቅስቃሴዎች ከፍተኛ ገንዘብ ያገኛል፡፡
ለህጻናት የተለየ ፍቅር እንዳለው የሚነገርለትና የአራት ልጆች አባት የሆነው ክርስቲያኖ ሮናልዶ የደግ ልብ ባለቤት መሆኑን በተደጋጋሚ አሳይቷል፡፡ ከአራት ዓመታት በፊት በሪያል ማድሪድ ቤት ሳለ ሳያንቲያጎ በርናባው ስታድየም ላይ ያደረገውን አንድ የበጎነት ስራ እናስታውስ፡፡ ሮናልዶ ቤርናባው ስታዲየም ላይ ከአንድ የሶስት አመት ህጻን ጋር ተገናኝቶ ነበር፡፡ ህጻኑ ሃይደር ይባላል፡፡ ሊባኖሳዊ ነው፡፡ በጊዜው ሊባኖስ ዋና ከተማ ቤይሩት ውስጥ በተከሰተ የአጥፍቶ ጠፊዎች ጥቃት ህጻኑ ሀይደር እናትና አባቱን በሞት ተነጥቋል፡፡ የእግር ኳስ ፍቅር ያለውና በተለይ ክርስቲያኖ ሮናልዶን በቴሌቪዥን ሲመለከት በደስታ የሚፈነጥዘው ሀይደርን ታሪክ ራና ሃርቢ የተባለች ሊባኖሳዊት ጋዜጠኛ አቅርባው የሪያል ማድሪድ ክለብ አመራሮች ከተመለከቱት በኋላ ነው ነገሮችን ያመቻቹት፡፡ በክለቡ ፕሬዚዳንት ፍሎረንቲኖ ፔሬዝ ትዕዛዝ ወደበርናባው ያቀናው ህጻኑ ሀይደር ሮናልዶን አግኝቶ በደስታ ተሞልቷል ሲፈነድቅ አይተነዋል፡፡
ጆን ሴና
ታዋቂው አሜሪካዊ የነጻ ትግል ተፋላሚና የፊልም ተዋናይ ጆን ሴና በግሉ በተለያዩ የበጎ ፍቃድ ስራዎች ከመሳተፉም በተጨማሪ በርካታ የበጎ ፍቃድ ድርጅቶችን ያግዛል፡፡ እ.ኤ.አ በ2012 ብቻ ከሌሎች ጓደኞቹ ጋር በመሆን በጡት ካንሠር የተጠቁ ሰዎችን ለመርዳት የሚውል 1.5 ሚሊዮን ዶላር ማሰባሰብ ችሏል፡፡
ሴሬና ዊሊያምስ
በስሟ የተቋቋመ ፋውንዴሽን አላት፡፡ በተጨማሪም የዩኒሴፍ የበጎ ፍቃድ አምባሳደር ሆና ታገለግላለች፡፡ ተወዳጇ የሜዳ ቴኒስ ስፖርተኛ አሜሪካዊቷ ሴሬና ዊሊያምስ በተለያዩ የበጎ ፍቃድ ስራዎች ላይ ከመሳተፍ ባለፈ ከካዝናዋ ገንዘብ በማውጣት የተቸገሩትን ትረዳለች፡፡ ሴሬና በተለያየ ጊዜ ዩኒሴፍ ለተማሪዎች የሚሆኑ ቁሳቁሶችን የማሰባሰብ ዘመቻ ቀዳሚ ተሰላፊ መሆን ግልጋሎቷን አበርክታለች፡፡
ዩና ኪም
ደቡብ ኮርያዊቷ ዩና ኪም ታዋቂ የስኬተር ስፖርተኛ ነች፡፡ የዩኒሴፍ የበጎ ፍቃድ አምባሳደሯ ኪም የተቸገሩ ሰዎችን ለመርዳት በምታደርገው እንቅስቃሴ ትወደሳለች፡፡ Dosomething.org የተባለው ድረገጽ ዝናቸውን ለበጎ ፍቃድ አውለዋል ካላቸው ስፖርተኞች መካከል በአራተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጣለች፡፡
ኔይማር
ብራዚላዊው የፒኤስጂ ተጫዋች ኔይማር ዳሲልቫ በጎ አድራጊ ተብለው ከተወደሱት መካከል 5ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል፡፡ በምዕራብ አፍሪካ ሃገራት የተከሠተውን የኢቦላ ቫይረስ ተከትሎ ፊፋ ባዘጋጀው የበጎ ፍቃድ ዘመቻ ከተሳተፉ እግር ኳስ ተጫዋቾች አንዱ መሆኑ ለዚህ ክብር አብቅቶታል፡፡ ኔይማር ከዚህ በተጨማሪ በግሉ የተቸገሩ ሰዎችን ይረዳል፡፡ በበጎ ፍቃድ ላይ ከሚሠሩ ድርጅቶች ጋር ይተባበራል፡፡ ለበጎ ፍቃድ ስራዎች የገቢ ማሰባሰቢያ የሚሆኑ የተለያዩ ጨዋታዎችን በማዘጋጀትም ይታወቃል፡፡ በደቡብ አሜሪካ የሚኖሩ ህጻናት የሚያስፈልጓቸው የትምህርት ቁሰቁሶችና የመሠረታዊ ፍላጎቶች እንዲሟሉ ጥረት ያደርጋል፡፡