ጎሳዬ ተስፋዬ፡- ‹በቅርቡ በሲዲ ምርቃት እንገናኛለን›

ሰሞኑን የወጣው የተወዳጁ አርቲስት ጎሳዬ ተስፋ ‹ሲያምሽ ያመኛል› የተሰኘው አልበም ከታክሲ እስከ ባጃጅ፤ ከቡና ቤት እስከ ካፌ፤ ከምግብ ቤት እስከ ሆቴል ከከተማ እስከ ገጠር፤ ከዚያም አልፎ እስከ ባህር ማዶ ድረስ እየተደመጠ ያለ አልበም ነው፡፡ ጎሳዬ ሁሌም አልበም ሲያወጣ አነጋገጋሪነቱ  እንዳለ ነው፡፡ የዛሬ 10 ዓመት ያወጣውን ‹ሳታመሃኝ ብላ› የተሰኘውን አልበም ይዞ ሲመጣ ፖስተሩላይ ወጣው  እጅግ ዘመናዊ በሚባል የፋሽን ልብስ ደምቆ አልነበረም፤ በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች ክልልና በኦሮሚያ ክልል ወጣቶች በስፋት የሚለብሱትን ቲሸርት አድርጎ ስለነበር ከሙዚቃው በተጨማሪ ልብሱ  ፋሽን እንደነበር እናስታውሳልን፡፡

የዘንድሮ አዲስ አልበሙም ይበልጥ ተወዳጅ ድምፁን ይዞ መጥቷል፡፡የጎሳዬ ድምፅ ወይን መሆኑን በጣዕሙ መለየት ይቻላል፡፡ የጎሳዬ ድምፅ  የተለየ ነው የሚሉ ብዙዎች ናቸው፡፡ ዛሬ ብቻ ሳይሆን ነገም የሚጥምና የአይረሴ ቅላጼ ነው ያለው፡፡ በዚህ አዲሱ አልበሙ ላይ የተለያዩ ስልቶችን ያቀነቀነው ጎሳዬ በተለየ የአዘፋፈን ስልታቸው የሚታወቁትን አቡሽ ዘለቀን እና ግዛቸው ተሾመን በፊቸሪን  በማዋሃድ አቀንቅኗ፡፡

ሙሉቀን መለሰ  ሙዚቃ አቁሞ  ኑሮውን መንፈሳዊ  ቢያደርግም ሙዚቀ አልፎ አልፎም ቢሆን ይሰማል፡፡ ከሚሰማቸው ወጣት ድምፃውያን መሀከል  ድምፃዊ ጎሳዬ ተስፋዬ አንዱ እንደሆነ ይናገራል፡፡ ሰሞኑንም አንድ  የሙሉቀን መለሰ አድናቂ የሆነ አድናቂ በፌስ ቡክ ገፁ ላይ ያሰፈረው ሀሳብ በሙሉቀን መለሰ ዘፈን ማቆም ይቆጭ   እንደነበር ይያመለክታል፡፡ ያም ሆኖ  አዲሱን የጎሳዬን አልበም ገዝቶ ሲሰማ ግን ‹ሙሉቀንን መለሰ ዘፈን አላቆመም አሰኝቶኛል፤ ጎሳዬን ተክቶልኛል፤ ሳይደግስ አይጣላም› ብሎ መፃፉ ታይቷል፡፡ በተለይም ‹ተረጋጋሽ ወይ› እና ‹ጭር ካለው ቦታ› የተሰኘውን ዜማ የሰሙ ሁሉ በዚህ ወጣት ሀሳብ ይስማማሉ፡፡

አንጋፋው ጋዜጠኛ አለምነህ ዋሴ ደግሞ እንዲህ ሲል ስለ ጎሳዬ አልበም ምስክርነቱን ይሰጣል‹ከዜማው ቀረ፣ከግጥሙ አነሰ፣ከድምፁ ወረደ የማይሉት፤እንደ ንጉስ ግብር በባለሙያ እጅ፣ሀሳብና በሰፊው የተሰጠ የድምፅ ስጦታ ተሞናሙኖ የተከሸነ የኪነት ቡፌ!የማይጠገበው ልብ ሰርስሮ እርካታ የሚያመነጨው የድምፅ ፅዋ—ጎሳዬ ተስፋዬ–ገና ከአሁኑ ድባቡ አልባብ አልባብ- ጤና አዳም ጤና አዳም እውድ እያደርግን ላለው የገና በዓል ስጦታ ሆኖ ገበያ ቀርቧል!እንቅልፍ ትቼ ፃፍኩላችሁ።አዎ!ኦሪጅናል ሲዲውን ብቻ ግዙ ብዬ አፌን ሞልቼ ደረቴን ነፍቼ ጋበዝኳችሁ።ይሄ ማስታወቂያ አይደለም፤ምስክርነት ነው ወገኖቼ።11 ዓመት ጠበቅን፤እንኳንም ታገስን!ጠጣን፤ረካንም! ጎሳዬ ዘፍኗል!!አዲስ ጥዑመ ዜማ –ሲዲ ውን ወዲህ በሉማ!!!!!!!>

የዛሬ 15 ዓመት አሌክስና ጎሳዬ አቫንጋዲ በተሰኘው የጋራ አልበማቸውን ሲያወጡ ከልጅ እስከ አዋቂ ያንጎራጉረው ነበር፡፡ ከኦሎምፒያ ወደ ባምቢስ በሚወስደው መንገድ አጋማሽ ላይ በሚገኘው ናይት ክለባቸውም በሳምንት ለሶስት ቀናት ሲዘፍኑ ቤታቸው ጢም ይል ነበር፡፡ በወቅቱ  የምሽቱ ስራ እስከሚጀምር ድረስ ስንጨዋወት ነበር፤ ‹‹ግን ግን ጎሲ ለምታፈቅራት ሴት የምትሰጣት ስጦታ ምንድነው;› የሚል ጥያቄ ሰነዘርኩለት፡፡ ጎሲ እንዲህ አለ‹የማፈቅራት ሴት ም እንደምትወድ አውቃለሁ ብዬ አስባለሁ፡፡ የምትወደውን ነገር በግጥምና በዜማ አስውቤ በማቀንቀን መስጠትን እመርጣለሁ፤ ሰዓት ወይም ቀለበት አይደለም የእኔ ስጦታ፤ሰዓቱም ሊበላሽ ይችላል፤ ቀለበቱም ከጣት ላይ ወልቆ ሊጠፋ ይችላል፤ ዜማው ግን ዘላለማዊ ነው› ነበር ያለው፡፡ ለዚህም ይመስላል ከአዲሱ አልብም 15 ዘፈኖቹ መሀከል አራት ያህሉን ‹በተሳሳተ ስልክ፤ሲያምሽ ያመኛል፤ከእሁድ እስከ እሁድ እና ዳኛ ዳኛ› የተሰኙትን ዜማዎች መታሰቢያነቱን ለውድ ባለቤቱ ለወ/ሮ ገነት ያደረገው፡፡ የአልበሙ መሪ ርዕስ የሆነው ‹ ሲያምሽ ያመኛል› የሚለው ዜማ ደግሞ ግጥሙም ዜማውም የተሰራው በራሱ በጎሳዬ ነው፡፡

አሉ የተባሉ የሙዚቃ ባለሙያዎች  የተሳተፉበት የጎሳዬ   አልበም ላይ  በግጥምና በዜማ ራሱን ጎሳዬን ጭምሮ አለማየሁ ደመቀ፤ ሀብታሙ ቦጋለ፤አማኑኤል ይልማ፤አለምፀሐይ ወዳጆ፤ይልማ ገ/አብ፤መኮንን ለማ፤ቢኒያም መስፍንና መሰለ ጌታሁንን አካቷል፡፡ የሙዚቃ ቅንብሩን ወጣቶቹ ሙዚቀኞች አቤል ጳውሎስ፤ሚካኤል ሀይሉ፤ካሙዙ ካሳ፤ሱልጣን ኑሪ፤መኮንን ለማ እና አንጋፋውን ሙዚቀኛ አበጋዝ ክብረወርቅ ሺወታ ተጠበውበታል፡፡ በሙሉ ባንድ  ሙዚቀኞችን አሳትፎ ለጆሮ ጣዕም ያለው ሙዚቃ የሰራው ጎሳዬ አልበሙ በወጣ በጥቂት ቀናት ውስጥ  በብዙ ሺ ኮፒ መሸጥ የቻለ ይሁን እንጂ በዘመን አመጣሹ የኢንተርኔት ሙዚቃ ቀሻቢዎች ቅር መሰኘቱን ለቁም ነገር መፅሔት አልሸሸገም፡፡‹እንደዚህ ደክሜ የሰራሁት አልበም በብዙዎች ዘንድ ተቀባይነት ማግኘቱ ቢያስደስተኝም በዩቲዩብ ላይ ግን ያለ እኔ ፈቃድ ህገወጦች ዘፈኖቹን በማቅረብ ህገ ወጥ ስራ መስራታቸው ተገቢ አይደለም› ይልል የኮፒ ራይት ችግሩን አሳሳቢነት  ሲገልጥ፤ በአሜሪካና በአውሮፖ ለገበያ የቀረበው የጎሳዬ አዲሱ አልበም በሀገር ውስጥ ከወጣ ከአንድ ሳምንት በኋላ መሆኑን አንደ አጋጣሚ የተጠቀሙበት ህገወጦች ለሀገር ውስጥ የቀረበውን አልበም በዩቲዩብ ላይ በህገ ወጥ መንገድ በመጫን ገቢ እያገኙበት ስለመሆኑ ገሳዬ በቅሬታ ይጠቅሳል፡፡ ያም ሆኖ ግን በዩቲዩብ ላይ ህጋዊ የሆነውን የጎሳዬን ሙዚቃ ለማግኘት የሚፈልጉ ሰዎች ‹ጎሳዬ ተስፋዬ ኦፊሻል› በሚለው ህጋዊ አድራሻ በመግባት መግዛት እንደሚችሉ አስታውቋል፡፡

ጎሳዬ በመድረክ ላይ ሲያቀነቅን ለመመልከት የብዙዎች ፍላጎት ነው፡፡ እንኳ አዲስ አልበም አውጥቶ ይቅርና ሳያወጣም ጎሳዬን መድረክ ላይ ማየት ያጓጓል የሚሉ ብዙዎች ናቸው፡፡ ‹እንደ እግዚአብሔር ፍቃድ  አልበሙ በደንብ ይሰማና ለዳግማ ትንሳይ  ኮንሰርት ለመስራት አስባለሁ፤› ይላል የአድናቂዎቹን ተደጋጋሚ ጥያቄ ለመመለስ በማሰብ፡፡ ከእዛ በፊት ግን ‹በቅርቡ  በሲዲ ምረቃ ስነ ስርዓት እንገናኛለን› ይላል፡፡

ጎሳዬ በዘፈኖቹ ልዩ ልዩ ማህበራዊ ጉዳዮች ላይ አተኩሮ በማቀንቀን ብቻ አይደለም የሚታወቀው፡፡ በተለያዩ ሰብዓዊ ተግባራት ላይም የራሱን ተሳትፎ ያደርጋል፡፡ በአዲሱ አልበሙ ላይ ‹ከዚህ የሙዚቃ አልበም ኦሪጂናል ሲዲ ሽያጭ እኔና ቤተሰቤ በምንተምነው የገንዘብ መጠን እምነት ይጣልባቸዋል ብለን ላሰብናቸው በጎ አድራጊ ድርጅቶች እንደ ፈጣሪ ፈቃድ በእኔ፤ በቤተሰቤና በእናንተ በአድናቂዎቼ ስም ለማበርከት በማሰብ በጥቂቱም ቢሆን የኢትዮጵያዊነት ግዴታችንን በጋራ እንደምንወጣ ስገልፅ በታላቅ ደስታና የታማኝነት ስሜት ነው › በማለት አስታውቋል፡፡ ይህንኑ መሠረት በማድረግም በቀጣዩ ሳምንት መጀመሪያ ላይ ወደ ደብረ ብርሃን በማምራት ለአንድ የበጎ አድራጎት ድርጅት እጁን ይዘረጋል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትስስር ይፍጠሩ

325,851FansLike
49,039FollowersFollow
13,194SubscribersSubscribe