‹እኔ እያለሁ ማንም ሰው ፆሙን አያድርም ›  ጋዜጠኛና የማስታወቂያ ባለሙያ ሳምሶን ማሞ

የዛሬ 25 ዓመት በወጣችው ቁም ነገር መፅሔት ቁጥር 1 ላይ ከወጡ 8 ታዋቂ ሰዎች መሀከል ሁለቱ ከዚህ ዓለም በሞት የተለዩ ናቸው፡፡/አንጋፋው ድምፃዊ ጥላሁንን ገሠሠና የድሆች አባት አለባቸው ተካ/ ስድስቱ ታዋቂ አርቲስቶችና ጋዜጠኞች በእግዚአብሔር ፈቃድ  በሰላምና በጤና በሙያቸው ላይ ይገኛሉ፡፡ በመሆኑም ከአምስቱ ባለሙያዎች ጋር (አርቲስት ሙሉዓለም ታደሰ፤ ጋዜጠኛ አለምነህ ዋሴ፤ ጋዜጠኛና የማስታወቂያ ባለሙያ ሳምሶን ማሞና ላፎንቴኖች ብርሃኑ ተዘራና ታደለ ሮባ)ከ25 ዓመታት በኋላ 25 ልዩ ጥያቄዎች አቅርበን አዝናኝ ምላሾችን ሰጥተውናል፤

‹እኔ እያለሁ ማንም ሰው ፆሙን አያድርም ›  ጋዜጠኛና የማስታወቂያ ባለሙያ ሳምሶን ማሞ

ቁም ነገር፡- የዛሬ 25 ዓመት ቁም ነገር መፅሔት ላይ የወጣው ቃለ ምልልስ የሰጠኸው የት ቦታ እንደሆነ ታስታውሳለህ ?

ሳምሶን፡- ቦታውን አላስታውሰውም በትክክል፤

ቁምነገር፡- ላስታውስህ?

ሳምሶን፡- ደስ ይለኛል፤

ቁም ነገር፤- የዛን ጊዜ የምትኖረው ሲኤምሲ የኪቤአድ መኖሪያ ቤቶች ውስጥ ስለነበር እዛ ነው፡፡

ቁም ነገር፡- ስለ ቁም ነገር መፅሔት ሲነሳ ቶሎ ብሎ ወደ አዕምሮህ የሚመጣው ነገር ምንድነው?

ሳምሶን፡- ቁም ነገር በወቅቱ ታላላቅ ሰዎችን ቃለ መጠይቅ አድርጎ የሚቀርብ ሚዛናዊ አዝናኝና ተነባቢ መፅሔት እንደሆነ ነው፡፡ በአንድ ጉዳይ ብቻ ሳይሆን በብዙ ጉዳዮች ላይ የበሰለ ጆርናሊስቲክ የሆነ ሚዛናዊ ስራ የሚወጣበት መፅሔት መሆኑን አስታውሳለሁ፡፡

ቁም ነገር፡- የዛሬ  25 ዓመት በነበረው ሳምሶን ማሞና በዛሬው ሳምሶን  መሀከል ምን ልዩነት አለ? በምን ጉዳይ?

ሳምሶን፡- ሳምሶን ማሞ ትላንት የነበረውን ሙያና ባህሪ ይዞ ያለ፤ ዛሬም በተመሳሳይ ሙያና ባህሪ ዕድሜ የቆጠረ ሰው ነው፡፡ በወጣትነት በጣም ብዙ ስሜታዊ የሚያደርጉ ገጠመኞች ይኖራሉ፡፡ ዕድሜ ሲገፋና ምራቅህን ዋጥ ስታደርግ ደግሞ ማስተዋል ማመዛዘን መረጋጋት ትማርበታለህ፡፡

ቁም ነገር፡- መርካቶ ውስጥ ቦምብ ተራ የሚባል ቦታ አለ፤ ምንድነው የሚሸጠው?

ሳምሶን፡- ቦምብ ተራ የኢትዮጵያ የፍጆታ ምርቶች ሸቀጣ ሸቀጦች የሚከፋፈሉበት ቦታ ነው፡፡ እኛም የዕለት እንጀራችንን የምናገኘው ከቦምብ  ተራ ነው፡፡ የዛሬው የሀገራችን ቢሊየነሮችም የፈለቁት ከቦምብ ተራ ነው፡፡ ይህ ቦታ የኢትዮጵያ ህዝብ  ጦም የማያሳድር ታላቅ ውለታ የዋለ የንግድ ቦታ ነው፡፡

ቁም ነገር፡- ባለፉት 25 ዓመታት ያሳካኸው/ያላሳካኸው/ወደፊት የምታሳካው ነገር ምንድነው?

ሳምሶን፡- አሳካሁት ብዬ የምኮራበት ነገር የለም፡፡ እንደ እኔ ሃሳብ ሳይሞላልኝ የተውኩት ብዙ ጉዳይ አልፎአል፡፡ በወቅት መሠራት የነበረባቸው ብዙ ታላላቅ ህልሞቼ ቅዥት ሆኖ ቀርቷል፡፡ ባይቆጭም ያንገበግባል፡፡ እድሜ እየገፋ ሲሄድ ደግሞ ለሀገር የሆነ ቁም ነገር ሰርቶ ማለፍ ብቻ ጥሩ ነው ብዬ አስባለሁ፡፡

ቁም ነገር፡- ባለፉት 25 ዓመታት  ከመጡ የቴክኖሎጂ ውጤቶች መሀከል እንኳንም መጣ የምትለውና ባይመጣ ጥሩ ነበር የምትለው ነገር  ምንድነው?

ሳምሶን፡- ግሎባላይዤሽን ዓለምን አንድ እያደረገ ያለ ነው፡፡ ካፒታሊዝም በዓለም ላይ የሚፈጥራቸው ቴክኖሎጂዎች አንተ ሳትጠይቅ እነሱ አንተ ሀገር ይዘውልህ ይመጣሉ፡፡ የኤሌትሪክ መኪና አሁን  ሀገራችችንን ሲወር ብዙ ዓመታት አልተቆጠሩም፡፡ የሚፈጠር ቴክኖሎጂ በሚፈጠርበት ሀገር አይቆይም፡፡ ንግድ ነው፡፡ የዓለማችን ታላላቅ ብራንድ ያላቸው የቴክኖሎጂ ውጤቶች ከአውሮፖና ከአሜሪካ መጥተው አፍሪካ ለመድረስ ቀናት አይፈጅባቸውም፡፡ ስለዚህ አይገባም ብዬ የማስበው የቴክኖሎጂ ውጤት የለም፡፡ ሁሉም በጊዜው ይገባል፡፡

ቁም ነገር፡- ባለፉት 25 ዓመታት በሞት ካጣናቸው ሰዎች በጣም ያስደነገጠህ/ያሳዘነህ ማነው?

ሳምሶን፡- ሀገራችን በየሙያ ዘርፉ አንቱ የተባሉ ሙያተኞችን አጥታለች፡፡እኔ በጣም ከማከብራቸው ሰዎች መሀከል አንዱ በዓሉ ግርማ ነው፡፡ በጣም ያሳዝነኛል የበዓሉ ነገር፡፡ በቅርብ ከማውቃቸው ባለሙያዎች  መሀከል ደግሞ የሁላችንም የሙያ አባት ጋሽ ውብሸት ወርቃለማሁ ያሳዝነኛል፡፡ በራዲዮ ጋዜጠኝነት ሙያ እጅግ ከማከብራቸው ውስጥ

ታደሰ ሙሉነህና  ጌታቸው ኃይለማርያም ባይሞቱ ብዬ ከማስባቸው ሰዎች ውስጥ ናቸው፡፡ ፀጋዬ ገ/መድህንን የሚያህል ባለቅኔና የቴአትር ፀሐፊ ማለፉ የሚቆጭህ እንደ እርሱ አይነት ጠቢብና ሊቅ ድጋሚ አለማግኘታችንን ስታስብ  ነው፡፡ የቴአትር አዘጋጁን አባተ መኩሪያን የመሰለ ሰው ማጣት ካልተሰማህ እንደ ችግር ነው የማየው፡፡ ጊዜ አይበቃንም እንጂ ብዙ መሞት የማይገባቸው ሰዎችን አጥተናል፡፡

በግሌ ደግሞ በህይወቴ ዘላለሜን የማይረሳኝ ለልጆቹ ሟች የነበረውንና እዚህ ለመድረሴ ምሳሌ የሆነኝ ግን ደግሞ ምንም ያላደረኩለትን አባቴን ለዘላላም አስታውሰዋለሁ፡፡ የምኮራበት ጀግና የዋህ አባቴን ያለማሰብ ለእርሱ ድጋሚ ሞት ነው፡፡

ቁም ነገር፡- ባለፉት 25 ዓመታት በኢትዮጵያ ውስጥ መሆን ሲገባው ሳይሆን የቀረ/መሆን ሳይገባው ሆነ የምትለው ነገር ምንድነው?

ሳምሶን፡- ከድህነት የበለጠ ጠላት የለንም፡፡ ከድህነት የበለጠም ህመም የለም፡፡ እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ቢያንስ መሠረታዊ ፍላጎቱን ማሟላት የሚችልበት ኑሮ ቢኖረው ኖሮ በጣም ደስ ይለኝ ነበር፡፡

ቁም ነገር፡- ነገን የማወቅ ችሎታ ከሚሰጥህና የትላንትናውን ነገር መቀየር ብትችል የቱን ትመርጣለህ?ምን ታደርጋለህ?

ሳምሶን፡- ሊሆን አይችልም እንጂ እንደገና ከወጣትነት ልጀምር ብል ዕድሜዬን ሙሉ ያልቻልኩትንና ያላወኩትን ነገር፤ ጎደለኝ የምለውን በሙሉ እየሞላሁ የማልቆጭበትን ስራ እየሰራሁ ብኖር ደስ ይለኝ ነበር፡፡ ግን ፈጣሪ ካረጀህ በኋላ እንደገና ወደ ወጣትነት ሊመልስህ ስለማይችል እሱ እንደፍጥርጥሩ የፈቀደውን ብሆን ነው የምመርጠው፡፡

ቁም ነገር፡- ፆታህን መርጠህ የመወለድ እድል ቢሰጥህ አሁንም ወንድ/ሴት ሆነህ መወለድ ትመርጣለህ ለምን?

ሳምሶን፡- አይ በፈጣሪ ስራ መግባት አልፈልግም፤ መመራመርም አልፈልግም፡፡

ቁም ነገር፡- የዛሬ 25 ዓመት በዚህ ሙያ ውስጥ ባትገባ ኖሮ ምን ትሆን ነበር?

ሳምሶን፡- ኳስ ተጫዋች ነበር የምሆነው፡፡

ቁም ነገር፡- በመጀመሪያ ስራህ የተሰጠህ የማትረሳው አስደሳች/አሳዛኝ  አስተያየት ምንድነው?ማነው የሰጠኸ?

ሳምሶን፡- ኢትዮጵያ ራዲዮ ገና በወጣትነት ዕድሜዬ ወጣቶች ፕሮግራም ለመስራት ስጠይቅ ‹ይሄ የህፃናት መጫወቻ አይደለም!› ብሎ አንድ ሀላፊ ያባረረኝን አልረሳውም፡፡

ቁም ነገር፡- ዕድለኛ ሰው ነኝ/ዕድለ ቢስ ነኝ ብለህ ታስባለህ? ከእድል ጋር ተገናኝተህ ወይም ተሸዋውደህ ታውቃለህ?

ሳምሶን፡- በፈጣሪ የማምን ሰው ነኝ፡፡ ፈጣሪ የሰጠኝን የነፈገኝንም በፀጋ ተቀብዬ የምኖር ሰው ነኝ፤ አሁን ያለሁበት ደረጃ ወደድኩም ጠላሁም ፈጣሪ በፈቀደው መንገድ ነው፡፡ ከዚህ ውጭ ዕድለኛ መሆን ወይም አለመሆን ባንተ መልካም ፈቃድ የሚመጣ አይደለም፡፡ ላጣሁትም ላገኘሁትም ፈጣሪ ሰጠ ፈጣሪ ነሳ ብዬ ነው የማምነው፡፡

በነገርህ ላይ ኑሮዬን ከዕድል፤ አጋጣሚ፤ ከጥንቆላ ከፍልስፍና ወይም ከተለያዩ አስተሳሰብ ጋር ማገናኘት አልፈልግም፡፡ እምነቴ ኦርቶዶክስ ነው፤በእናትና ልጁ መልካም ፈቃድ ዛሬ የተሰጠኝን ወይም ያለሁበትን ከፍታም ሆነ ዝቅታ ኑሮ በፀጋ ተቀብዬ ለመኖር የተፈጠርኩ አድርጌ ነው የማስበው፤ሁሉ ነገር ለበጎ ነው፡፡

ቁም ነገር፡- ስራ ስትጀምር ሞዴል አድርገህ የምታሰበው ሰው ጋር መድረክ ላይ አብረህ የመስራት እድል ገጥሞሃል? ከማን ጋር?

ሳምሶን፡- አብሬያቸው እቆማለሁ ብዬ ከማላስባቸው ታላላቅ ሰዎች መሀከል አንዱ ጥላሁን ገሠሠ ነበር፤ ማህሙድ አሕመድ፤ አለማየሁ እሸቴ፤ ውብሸት ወርቃለማሁ፤ ደበበ እሸቱ ብዙ የማከብራቸው ሰዎች ጋር አንድ መድረክ ላይ ለመስራት ችያለሁ፡፡ ለራሴም ይገርመኛል፤ እንደ ትልቅ አጋጣሚም እወስደዋለሁ፡፡ ከፈለክ ከትቢያ ትነሳለህ፤ ህይወት እንደዛ ናት፤ ማንም ሰው ጥንካሬ ካለው ባለበት አይቆምም፤ የእኔ ፍልስፍና ዛሬ የተሰጠህን በጎም ይሁን ክፉ ማግኘትም ሆነ ማጣት በፀጋ መቀበል ብቻ ነው፡፡

ቁም ነገር፡- የዛሬ 25 ዓመት ሀገራችን ላይ ድህነት/የሰላም እጦት ነበረ፤ አሁንም ችግራችን ነው፤ ከዚህ ለመውጣት ሀሳብ አዋጣ ብትባል ምን ትላለህ?

ሳምሶን፡- ኖ ኮመንት፡፡

ቁም ነገር፡- ባንክ ያለህ ገንዘብ ተወርሷል ብትባል ምን ትላለህ?

ሳምሶን፡- ስፈጠር ጀምሮ ከባንክ ጋር አልተፈጠርኩም፡፡ እርቃኔን ነው ወደዚህ ዓለም የመጣሁት፡፡ የተቀላቀልኩት፡፡ ገንዘብን ሰርተህ የምታመጣው ነገር ነው፡፡ ያለህ ገንዘብ እንዳለ ቢወረስ እንደገና እየሰራህ መኖር ትጀምራለህ፡፡ ካገኘህ እሰየው ነው፤ ካላገኘህም እንደማንም ገንዘብ ባንክ ለማስቀመጥ እንዳልተፈቀደለት ሰው ድሃ መሆንህን በፀጋ ተቀብለህ መኖር ትጀምራለህ፡፡ ህይወት እንደዛ ነው፡፡ ለምሳሌ መኪና ከሌለህ በእግርህ ትሄዳለህ፡፡ ስጋ መግዛት ካልቻልክ በዳቦ ትውላለህ፡፡ ፎቅ መስራት ካልቻልክ በጎጆ ቤት ውስጥ ትኖራለህ፡፡ ህይወት እንደዚህ ናት ብዬ ነው የማስበው፡፡

ቁም ነገር፡- ባለፉት 25 ዓመት ውስጥ በጣም ከባድና አስጨናቂ/አስደሳች  ጊዜ ባንተ ህይወት ውስጥ የቱ ነው?

ሳምሶን፡- እኔ በህይወቴ የሚገጥመኝን ፈተናም ሆነ ምቾት በጥንቃቄ ነው የማየው፡፡ በፈተና ቅስሜ የሚሰበር ሰው አይደለሁም፡፡ በስኬትም አልሰክርም፡፡ ሁሉንም እንደአመጣጡ የማስተናገድ አቅም ያለኝ ሰው ነኝ፤እኔ በገጠሙኝ ፈተናዎች ምክንያት ጎንበስ ብዬ ሄጄ አላውቅም፡፡ በህይወቴ በማንም ሰው ላይ ክፉ ነገር ለመስራት የማስብ ሰው አይደለሁም፡፡ለሚወዱኝም ሆነ ለሚጠሉኝ(የሚጠላኝ ሰው ካለ)  በጎ ነገር ነው የማስበው፡፡ ታዲያ ቀና ብዬ ለመሄድ ምን ያንሰኛል?

ቁም ነገር፡- በተለምዶ የሴት/የወንድ ከሚባሉ የቤት ውስጥ ስራዎች ምን ይዋጣልሃል?

ሳምሶን፡- በነገርህ ላይ ቤት ውስጥ ብዙ አይነት ምግቦችን እሰራለሁ፡፡በሀገር  ያሉም ይሁን በውጭ ሀገር ያሉ ሼፎች ከሚሰሩት የምግብ አሰራር በመማር ባህላዊም ሆነ ፈረንጃዊ ምግቦችን መስራት እችላለሁ፡፡ እኛ ቤት አንዳንድ ጊዜ ምግብ እየሰራሁ ሰርፕራይዝ አደርጋቸዋለሁ፡፡ በእርግጠኝነት የምነግርህ ብቻዬንም ሆንኩ ከሰው ጋር ሆንኩ ምግብ መስራት ግዴታ ከሆነ እኔ እያለሁ ማንም ሰው ፆሙን አያድርም፡፡

ቁም ነገር፡- የዛሬ 25 ዓመት ለቁም ነገር መፅሔት በሰጠኸው ቃለ ምልልስ ላይ የሚከተለውን መልሰህ ነበር፤

(ቁም ነገር፡- ለገንዘብ ያለህ አመለካከት እንዴት ነው? ለሚለው ጥያቄ የሰጠኸው መልስ ‹ ለገንዘብ አክብሮት የለኝም፤› የሚል ነበር፡፡ አሁንስ?)

ሳምሶን፡- አሁም ገንዘብን ማኔጅ ማድረግ አልችልም፡፡ ደካማ ነኝ፡፡በአቅሜ የምኖር ሰው አይደለሁም፡፡ ከስህተቴም ብዙ አልማርም፡፡ ከሰዎች ጋር ተካፍሎ የመኖር ፖሊሲ ነው ያለኝ፡፡ በዚህ የተነሳ እንደ ሰው ትቸገራለህ፡፡ ረሃብን የመፍራት ስነ ልቦና ግን የለኝም፡፡

ቁም ነገር፡- እስከዛሬ ሰምተህ ለማመን የተቸገርከው ዜና/ወሬ ምንድነው?

ሳምሶን፡- በእኔ ላይ የሚሰሩ ልብ ወለድ ዜናዎች ብዙ ጊዜ ያስገርሙኛል፡፡የውሸት ዜና የሚፈበርኩ ሰዎች ጋዜጠኛ ያልሆኑ ሰዎች አሉ፡፡ ፀሐፊዎችም አሉ፡፡ እንደዚህ አይነት የውሸት ዜና እየሰራ ጥሩ እንቅልፍ የሚተኛ ሰው ካለ ይሄ ሰው በሽተኛ ነው፤ ወይም በሰው ሀዘን የሚደሰት ሳዲስት መሆን አለበት፡፡

ቁም ነገር፡- ከ25 ዓመታት ጉዞህን የህይወት ታሪክህን በመፅሐፍ/በፊልም የምትፅፍ ይመስልሃል?/ ሰዎች ከእኔ ታሪክ ይማራሉ የምትለው ነገር ምንድነው?

ሳምሶን፡- ስለ ራሴ ማውራትም መፃፍም ፍላጎቱ የለኝም፡፡ ነገ ሃሳቤን ልቀይር እችል ይሆናል፡፡ አላውቀውም፡፡ ላንተ ይህንን ቃለ ምልልስ ለመስጠት እንዴት እንዳሰቃየኸኝ አንተ ታውቃለህ፡፡ ብዙ የሰራሁት ታሪክ ስለሌለ አይመቸኝም፡፡

ቁም ነገር፡- ብሳተፍ ይዋጣልኛል የምትለው የስፖርት አይነት/የምትወደው ሊሆን ይችላል?

ሳምሶን፡- እግር ኳስ ተጫዋች ነበርኩ፡፡ ከስነ ፅሑፍ ፍላጎቴ ባላነሰ የልጅነት ዕድሜዬን ያሳለፍኩት ኳስ በመጫወት ነው፡፡ ትልቅ ተስፋ ነበረኝ፡፡ የደርግ መንግስት ሲመጣ ሁሉም ነገር ጠፋ እንጂ፡፡

ቁም ነገር፡- በአሁኑ ወቅት የዓለማችንን አነጋጋሪ ፕሬዚዳንት የሆኑት ዶናልድ ትራምፕን ጠዋት ከቤትህ ስትወጣ ድንገት በርህ ላይ ብታገኛቸውም ምን ትላቸዋለህ?

ሳምሶን፡- ዶናልድ ትራምፕ ሴንሴሽናል ነገር የሚወዱ በህዝብ ፊት ለሚያደርጉት ንግግር የማይጨነቁ አድቫንቴጂ መስራት የሚወዱ ስሜታዊ ሰው ናቸው፡፡ እንደ ክሊንተንና ኦባማ አይነት ተናጋሪ ወይም ኦራተር ሰው አይደሉም፡፡ እንኳን በሌላው ዓለም በራሳቸው በአሜሪካ ዜጎችና ስደተኞች ላይ ያላቸው ጥላቻ የዘረኝነት ስሜትና የሚወስኑት ውሳኔ አሜሪካውያንን ስጋት ላይ ጥሏል፡፡ እኔ እስከማውቀው የዶናልድ ትራምፕን የእብደት ውሳኔ በመቃወም በተለያየ ስቴት የተካሄደባቸውን የተቃውሞ ሰልፍ ማንነታቸውን ያሳያል፡፡ ብታገኛቸው ምን ታደርጋለህ? ላልከው አላውቅም ምን እንደማደርግ፡፡ ዘግቼው ልሄድ እችላለሁ፡፡

ቁም ነገር፡- ለእግዚአብሔር ሁለት ጥያቄ ጠይቅ ብትባል ምን ትጠይቃለህ?

ሳምሶን፡- ሠላም ፍቅርትና ጤንነት ይሰጠን ዘንድ እለምናለሁ፡፡

ቁም ነገር፡- አመሰግናለሁ፡፡

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትስስር ይፍጠሩ

325,851FansLike
49,039FollowersFollow
13,194SubscribersSubscribe