“ጭር ሲል አልወድም”

በሰሎሞን ሹምዬ መኮንን /gebeyanu@gmail.com/

የእናና ዱባለን ዘፈን ግጥም ላስታውሳችሁ አይደለም:: ይሁን እንጂ በበኩሌ “ጭር ሲል አልወድም” የሚለውን ሀረግ መጠቀም የጀመርኩት የእርሷን ዘፈን ከሰማሁ በኋላ መሆኑን አልክድም:: አንዳንድ ሰው ጭር ሲል አይወድም:: በሆነ ምክንያት ያልሆነ ነገር አድርጎም ቢሆን የሰዎችን ትኩረት መሳብ እና መነጋገሪያ አጀንዳ መሆን ካልቻለ የኖረ አይመስለውም:: ይሄንኑ ትኩረት የማግኛ ስልት አንዳንድ አድራጊዎቹ ‹አቧራ ማስጨስ› ይሉታል::

አቧራ ማስጨስ በኪነ-ጥበቡ ዘርፍ ወይም በጋዜጠኝነት ሙያ ሲሆን አንዳንዴ አዋጭ መስሎ ይታያል:: ከእድሜያቸው ብዙውን ዘመን ለሙያው ሰጥተው ሲለፉ የህዝብን ትኩረት መሳብ ያልቻሉ አርቲስቶችና ጋዜጠኞች አንድ ቀን ለአንደኛው ማህበረሰብ አስደሳች፤ ለሌላው ደግሞ አስከፊ የሆነ ስራ ሲሰሩ “አቧራው ጨሶ” በአድናቆትና በውግዘት መነጋገሪያ ይሆኑና ስማቸው ይገናል:: ከዚያ በኋላ ነው “ጭር ሲል አልወድም” የሚል ስሜት የሚጀምረው:: እናም ያገኙትን ትኩረትና “ዝና” ላለማጣት በአቧራ ላይ አቧራ ማጨሱን ይያያዙታል::

የጭር ሲል አልወድም ስሜት ወደ ፖለቲካው ጎራ ሲመጣ ግን እንደ አርቲስቶቹና ጋዜጠኞቹ በቀላሉ የሚታለፍ አይሆንም:: ፖለቲከኞቹ የጭር ሲል አልወድም ስሜት ሲጠናወታቸው የሚያጨሱት አቧራ ትኩረት በመሳብ ብቻ ላያበቃ ይችላል:: ተከታዮቻቸው ጎራ ለይተው ወደ “በለው በለው” ቅስቀሳና ግጭት የሚገቡበት አጋጣሚ ብዙ ነው:: ወደ አገራችን ተጠባጭ ሁኔታ ስንመጣ ብዙ ምሳሌዎችን እያነሱ መነጋገር ይቻላል::

ላለፉት አስር ወራት ያክል ኢ.ህ.አ.ዲ.ግ. መራሹ መንግስት በሕዝባዊ አመፅ ተገዶ በተከተለው አስተዳደራዊ ለውጥ የተነሳ በስደት እና በእስር ላይ የነበሩ በርካታ ተቃዋሚ ፓርቲዎችና ግለሰቦች በነፃነት እንዲቀሳቀሱና ሃሳባቸውን እንዲያራምዱ የሚያስችላቸው ሁኔታ ተፈጥሯል:: ይህም ነፃነት ሰላማዊ እና ሰላማዊ መንገድን ብቻ እንደሚከተሉ ታሳቢ ያደረገ ነው:: ይሁን እንጂ ‘ጦር ጦር’ የሚለው የአንዳንዶቹ ተቃዋሚዎች መንፈስ እስከመቼም የሚለቃቸው አይመስልም:: በመንግስት በጎ ፈቃድ ከያሉበት እንደመጡ ዘንግተው አሁንም በአሸናፊና ተሸናፊ ስነልቦና ደጋፊዎቻቸውን ሳይቀር ያምሳሉ:: ሲገቡ ያሰሟቸው ከነበሩ የቅስቀሳ ዘፈኖች ጀምሮ የድል አድራጊ ሰራዊት ወይም አርበኝነት ወይም የነፃ አውጪነት ሃሳብ ሲያንፀባርቁ ማስተዋል የተለመደ ነው፡፡ ተከታዮቻቸውን በሃሳብ አነሳስተው ላልተገባ ግጭት ይዳርጋሉ:: አንዳንዶቹ እንደውም የፌዴራል መንግስቱን ህልውና ሳይቀር የዘነጉ ይመስላሉ::

ከተቃዋሚ ብቻ ሳይሆን ከመንግስትም በኩል ጭር ሲል የማይወዱ ቢያንሰ በግለሰብ ባለስልጣናት ደረጃ ያሉ ይመስላል:: አንድም መደበኛውን ኃላፊነት በብቃት ለመወጣት አቅም ሲያጡ ከተጠያቂነት የሚያድን ሰበብ ፍለጋ፤ ሁለትም ህዝብን “መንግስት ምነው ትዕግስቱ በዛ?” አስብሎ ስልጣን ሊገዳደሩ የሚችሉ ተቃዋሚዎችን ከምርጫው በፊት ቢያስወግድ ርምጃው ተቀባይነት እንዲያገኝ፤ ሶስትም በሰላምና መረጋጋት አመካኝቶ የምርጫ /የስልጣን/ ጊዜን ለማራዘም፤ አራትም የተጀመረው ለውጥ ከብጥብጥ በቀር ያስገኘለት ትሩፋት እንደሌለ ተሰምቶት ህዝቡ በለውጥ ኃይሉ ላይ እምነት እንዲያጣና ለተቃውሞ እንዲነሳሳ ለማድረግ ይመስላል፡፡ እንዲያማ ባይሆን በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ አገላለፅ ተደምሮ አስር ሺህ የማይሞላውን የተቃዋሚዎች ጦር /አሁን ቢያንስ ግማሹ ተቀንሷል/ ትጥቅ ማስፈታትና ሌሎችንም የጥፋት ኃይሎች ስርዓት ማስያዝ ከባድ ባልሆነ ነበር::

ጭር ሲል የማይወዱ አክቲቪስት ነን ባዮችም አሉ:: በተለይ ፌስቡክን በመሰሉ ማህበራዊ ሚዲያ በህዝቡ ዘንድ የሚፈጠርን ፍርሃት፣ ጥርጣሬ፣ ግጭት እና አለመረጋጋት እንደ መልካም የገበያ አጋጣሚ ተጠቅመው፣ በሃሰት መረጃ ጥሬ ዕቃነት የሚፈበርኩትን ሃሳብና ትንታኔ በመሸቀጥ ጥላቻና ፍረጃን ያስፋፋሉ:: አንዱን አስከፍተው በሌላው ለመወደድ ይደክማሉ:: በሚያለያይ ፅሁፍ ወይም ንግግራቸው አንድነትን ይሰብካሉ:: የሆነ ቦታ ግጭት ተቀሰቀሰ ሲባል /እውነት ቢሆንም ባይሆንም/ ተሽቀዳድመው “ያበስራሉ”:: የኢ.ህ.አ.ዲ.ግም ይሁን የሌሎች ፓርቲዎች አባል ድርጅቶች ወይም ግለሰቦች የሃሳብ ልዩነት ወይም ግጭት በአገር ላይ ሊያስከትል የሚችለው አደጋ ከሚያሳስባቸው ይልቅ “በውስጥ አዋቂ ነኝ” ባይ የአሉባልታ ትንታኔያቸው ተማርኮና ወገን ለይቶ በሚከተላቸው የዋህ ብዛት ይደሰታሉ::

ለምሳሌ ሰሞኑን በመገናኛ ብዙሃን እንዳየነው የትግራይና የአማራ ክልል ፕሬዝዳንቶች ከጠቅላይ ሚንስትሩ ጋር በሰላም እጅ ለእጅ ተያይዘው ከሚታዩ ይልቅ በየክልላቸው ሆነው ከፌዴራሉ ወይም ከሌላው ክልል ጋር ግጭት ቀመስ ቃላት ቢወራወሩ ደስታቸው ነው:: እነ ጭር ሲል አልወድም የነዙት ፕሮፖጋንዳ ሰለባ የሆነው ሰላማዊ ዜጋ የደህንነት ስጋት ተሰምቶት የመከላከያ ሰራዊት ከአካባቢው እንዳይወጣ ሲከላከል ሰራዊቱ ‘ክብሩን ለማስጠበቅ’ ግምባር ግምባሩን ብሎ ያለማለፉን ፖለቲካዊ ስም ሰጥተው ያራግባሉ፡፡ የሰራዊቱን ህዝባዊነት ከማድነቅ ይልቅ ተቆርቋሪ መስለው ‘ለምን ተደፈረ’ በማለት ይጮሃሉ::

እነ ጭር ሲል አልወድም ወንጀለኛን እንደ ወንጀለኛ በግል ከማውገዝ ይልቅ ከዚህ ወይም ከዚያኛው ብሔር አነካክተው በሰላም አብሮ የኖረውን ሕዝብ ለመጠላላትና ለመበቃቀል ያነሳሳሉ:: ከዘረፋ ጀምሮ እስከ ሰብአዊ መብት ጥሰት በሕዝብ ላይ ግፍና በደል ሲፈፅሙ የቆዩት ይብዛም ይነስም ከሁሉም ብሔር የወጡ ሰዎች እንደሆኑ ልቦናቸው እያወቀ ጣታቸውን በአንድ ብሔር ላይ ይቀስራሉ፡፡ ጧት ማታ በሚያሰራጩት ያልተጨበጠ አሉባልታና ስሞታም በየአካባቢው ረብሻ ሲነሳ ከመደንገጥ እና ለችግሩ ተጠቂዎች ከማዘን ይልቅ ይበልጥ እንዲስፋፋ የጥላቻ ቤንዚን በተቆርቋሪነት ስም ያርከፈክፋሉ:: ዞር ብለው ደግሞ አሁን ባለው ያልተረጋጋ ሁኔታ ምርጫ መካሄድ እንደሌለበት በመወትወት ሌላ የብጥብጥ ድግስ ይጠነስሳሉ:: ምርጫው በጊዜው ባይካሄድ ከፖለቲከኞቹ የሃሳብ ውዝግብ በተጨማሪ መንግስትን ሕጋዊ ከለላ የሚያሳጣው መሆኑ፤ ለሌላም ጊዜ መንግስት አምባገነንና ስርአት አልበኛ መሆን ሲፈልግ ተጠቃሽ የቀደመ ልምድ ሆኖ ሊያገለግል እንደሚችል ጠፍቷቸው ሳይሆን ነገሮች በሕግና በመግባባት ካለቁ እነሱ ትኩረት የሚያገኙበት ምክንያት ስለሚያሳጣቸው ነው:: -ጭር ሲል ስለማይወዱ::

በነገራችን ላይ እኔም ጭር ሲል አልወድም:: እኔ ጭር ሲል የማልወድበት ሁኔታ ግን ይለያል፡፡  /እንደማንኛውም ሰላም ወዳድ ሰው/ ዜጎች በአምባገነን መንግስት ነፃነታቸው ታፍኖ እጃቸውን አፋቸው ላይ በጫኑበት ሁኔታ ጭር ሲል ደስ አይለኝም:: ሕዝብ በፍርሃት ተሸብቦ ግፍና መከራን እየተቀበለ ዝም ሲል፣ በየትኛውም ቦታ ሰላምና ፀጥታ ደፍርሶ ሰው ከመኖሪያው ወጥቶ መንቀሳቀስ ሲያቅተው፣ በፍትህ አካላት ላይ እምነት አጥቶ ከወንጀለኛ ተደራድሮ መኖር ሲጀምር ወይም ወንጀለኛን በስሙ ጠርቶ ማውገዝ ሲሳነው፣ ገበያ መሐል ሻጭ “ምን ይዘሃል?” ብሎ የሚጠይቀው ገዥ ሲያጣ ወይንም ገዥ ረብጣ ብሩን ይዞ የፍላጎቱን የሚሸጥለት አንድ እንኳን ነጋዴ ሲያጣ፤ ያን ጊዜ እፈራለሁ:: -ጭር ሲል አልወድም:: ነፃነት፣ ፍትህ እና እኩልነት ሰፍኖ ሁላችንም ከ “ጭር ሲል አልወድም” ስሜት እንድንወጣ ምኞቴ ነው:: -ሰላም

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትስስር ይፍጠሩ

325,851FansLike
49,039FollowersFollow
13,194SubscribersSubscribe