እናመሰግናለን!
እነሆ ቁም ነገር መፅሔት 25 ዓመት ሞላት ! የመጀመሪያዋ ዕትም ቁጥር 1 ቁም ነገር መፅሔት የወጣችው መስከረም 30 ቀን 1994 ዓ.ም ነበር፡፡ 25 ዓመት ደፍናለች፡፡ በመስከረም ወር 1994 ዓ.ም የመጀመሪያዋን ቁም ነገር መፅሔት ይዘን ስንቀርብ በእንግዶቿ ተወዳጅነት፤ በመፅሔቷ አቀራረብና ይዘት ጠዋት 4 ሰዓት ላይ ነበር ከገበያ ላይ የጠፋችውና በድጋሚ ህትመት ያስገባናት፤ እናም ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ላልተለዩን አንባቢዎቻችን እንመሰግናለን!!
በመጀመሪያዋ ዕትም ቁም ነገር መፅሔት ላይ የወጣው ርዕሰ አንቀፅ እንዲህ የሚል አርፍተ ነገር ይዞ ነበር፤‹‹ዛሬ እጃችሁ የገባችው ቁም ነገር መፅሔት ዓላማ የኪነ ጥበብና የመዝናኛ መፅሔት እንድትሆን ነው፤ መፅሔቷ እንደ ስሟ ቁም ነገር ሰንቃ በኪነጥበብና በማህበራዊ ጉዳይ ዙሪያ ነፃና ግልጽ ውይይት እንዲኖር መድረክ መፍጠር ነው፡፡የያኔዋ ቁም ነገር መፅሔት ትዘጋጅ የነበረው በዛሬዎቹ አንጋፋ የጥበብ ሰዎች በአርቲስት ደበብ እሸቱና በደራሲ ስብሃት ገ/እግዚአብሔር ነበር፡፡ የዛሬዋ ቁም ነገር መፅሔት በእጃችሁ የገባችው ደግሞ ነገ አንጋፋ የመባል ፅኑ ፍላጎት ባላቸው ወጣት ጋዜጠኞች ነው ›; ብለን ነበር፡፡ ምን ያህል ተሳክቶልን ይሆን? ግን በእግዚአብሔር ፈቃድ፤ በዝግጅት ክፍሉ ባልደረቦች ጥረትና ትጋት እነሆ ሩብ ክፍለ ዘመን ተሻግራ ዛሬ ላይ ደርሳለች፡፡
የመፅሔታችን ኤዲቶሪያል ቦርድ ባለፉት 25 ዓመታት አብረውን ለሰሩ ከኮምፒዩተር ተያቢዎች ጀምሮ፤ ለአስተዳደር ሰራተኞች፤ ጋዜጠኞች፤ ለማተሚያ ቤቶች ፤ ማስታወቂያቸውን ላስነገሩ የንግድ ተቋማት፤ለህትመት ክትትልና የስርጭት ባለሙያዎች፤ ከሁሉም በላይ ሃሳባቸውን በተለያ መልኩ ላካፈሉን ከ2440 በላይ እንግዶቻችንና ከ450 ቅፅ በላይ በሆነው ህትመታችን ላይ በልዩ ልዩ ጉዳዮች ላይ ፅሁፋቸውን ላበረከቱልን ፀሐፍት ከወንበራችን ተነስተን፤ ባርኔጣችንን ከፍ አድርገን ልዩ ምስጋና እናቀርባለን፡፡
25ኛ ዓመት የብር ኢዮቤልዩ ክብረ በዓላችንን ምክንያት በማድረግ ያዘጋጀነው ልዩ ዕትም መፅሔት እነሆ እጃችሁ ገብቷል፡፡ ምናልባትም የስንብት ህትመት እንዳይሆን ለንባብ ግድ የሚላቸው ስፖንሰሮችንና አንባቢያንን አለኝታነትን እንሻለን፡፡ በበኩሌ መፅሔቷን ለማስቀጠል ሙሉ ዕውቀቴን፤ ግዜዬን፤ ጉልበቴንና ሃብቴን ጭምር ኢንቨስት አድርጌያለሁ፡፡
መፅሔታችንን የህትመት ዋጋ መናርና የዲጂታል ሚዲያ ፈጣን እድገት ፈታኝ ሁኔታ ውስጥ ከቷታል፡፡ በመሆኑም ከዘመኑ የቴክኖሎጂ ውጤት ጋር ራስን በማስታረቅ በሁሉም የዲጂታል ሚዲያ አማራጮች መጥተናል፤
ውድ የቁም ነገር መፅሔት አንባቢያን፤ በፅሑፎቻችን የታነፃችሁ፤ በካርቱን ስዕሎቻችን የተዝናናችሁ፤ በቃለ ምልልሶቻችን የተደሰታችሁ/የተናደዳችሁ፤ በእንግዶቻችን ታሪክ የተደመማችሁ፤ ምርትና አገልግሎታችሁን ያስተዋወቃችሁ፤ወዘተ አብራችሁን ስለተጓዛችሁ እናመሰግናለን!!
እናም በመጪዎቹ ጊዜያት የመልካም ምኞት መልዕክታችሁን እንቀበላለን፤አስተያየታችሁን እንጠብቃለን፡፡ ከታላቅ አክብሮትና ምስጋና ጋር!
ታምራት ኃይሉ/አሳታሚና ዋና አዘጋጅ
(የቁም ነገር መፅሔት ራዕሰ አንቀዕ)

